ፈልግ

በዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ፣               በዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ፣  

ለወጣቶች የሚሰጥ የትምህርት እና የስልጠና ዕድል (የወጣቶች ዓለም ክፍል 3)

ወጣቱን ትውልድ ወደ መልካም የኑሮ ደረጃ ለማድረስ ከተፈለገ ከሁሉ አስቀድሞ የማንበብ እና የመጻፍ ችሎታ እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ከወላጅ ቤተሰብ በተጨማሪ በእውቀት የታገዘ እና መልካም ስነ ምግባርን የተከተለ አስተዳደጋቸውን የሚከታተሉ ማሕበራዊ ተቋማትን ማደራጀት እና ማስደግ ያስፈልጋል።

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በርካታ አገሮች የወጣችን ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ ፖለቲካዊ እና ማሕላዊ ሕይወትንም ጭምር ወደ ተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ የተለያዩ እቅዶችን አውጥተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። በወጣቶች ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እን ኣባሕላዊ ሕይወት ላይ የተደቀኑ ችግሮች ብዙ ቢሆኑም እንደየአገሮቻቸው የዕድገት ደረጃ ሊለያዩ ይችላሉ። በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ወጣቶች መካከል የሚታዩ ችግሮች ባደጉት አገሮች ዘንድ ምናልባት በመጠን ይለያዩ ይሆናል እንጂ ሙሉ በሙሉ ተወግደዋል ለማለት ያስቸግራል። ብሁሉም አገሮች የሚገኙ ወጣቶች እንዲቃለልላቸው የሚፈልጉት ማሕበራዊ፣ ኤኮኖሚያ፣ ፖለቲካዊ እና ባሕላዊ ባሕላዊ ችግሮች አሏቸው። የትምህርት እና የስልጠና ዕድልን በበቂ ሁኔታ አለማግኘት፣ ሥራ አጥነት፣ ድህነት፣ በቂ የሆነ የጤና እንክብካቤን አለማግኘት፣ የአደንዛዥ ዕጽ ሱሰኝነት፣ በተለያየ ደርጃ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። እነዚህን እና ሌሎች በወጣቶች ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመቀነስ፣ ወጣቶች በሚኖሩበት አካባቢ የሚገኙ ማህበራዊ ተቋማት የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ወጣቱን ትውልድ ወደ መልካም የኑሮ ደረጃ ለማድረስ ከተፈለገ ከሁሉ አስቀድሞ የማንበብ እና የመጻፍ ችሎታ እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ከወላጅ ቤተሰብ በተጨማሪ በእውቀት የታገዘ እና መልካም ስነ ምግባርን የተከተለ አስተዳደጋቸውን የሚከታተሉ ማሕበራዊ ተቋማትን ማደራጀት እና ማስደግ ያስፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን እና የስልጠና ማዕከላትን ጥራት ማሻሻል ያስፈልጋል። የትምህርት እና የስልጠና ዕድልን ለወጣቶች ማመቻቸት ይስፈልጋል ሲባል በተለይ ወጣት ሴቶችን ከትምህርት እና ከስልጠና ዕድል የሚገቱ ማሕበራዊ እና ባሕላዊ እንቅፋቶችን በማስወገድ ከወንዶች ጋር እኩል እድል እንዲኖራቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ለወጣት ሴቶች የሚሰጥ የትምህርት እና የስልጠና ዕድል በዝቅተኛ ደረጃ ብቻ ተወስኖ የሚቀር መሆን የልበትም።

የእያንዳንዱ ወጣት አስተዳደግ ከመደበኛ ትምህርት እና ስልጠና በተጨማሪ የሚኖርበትን አካባቢ ባሕል ወግ እና ሥርዓትን የተከተለ እና ያከበረ መሆን ይኖርበታል። ወጣቶች የሚኖሩበትን አካባቢ ወግ፣ ባሕል እና ሥርዓት በሚገባ ማወቅ ይኖርባቸዋል ሲባል ዋናው ምክንያት ባሕል በሰዎች መካከል የሚደረጉ ማህበራዊ ግንኙነቶች ለማሕበራዊ ሕይወት በሚስማማ መልኩ ወደ ተፈለገው አቅጣጫ ለመምራት የሚያስችል መንገድ በመሆኑ ነው። ስለዚህ ወጣቶች የየአገሮቻቸውን መልካም ባሕላዊ እሴቶችን ለይተው በማወቅ በተግባር የሚያሳዩ መሆን ያስፈልጋል።

የጾታ ልዩነትን ያልተከተለ የትምህርት እና የስልጠና ዕድል ያስፈለገበት ምክንያት ወጣቶች የፈጠራ እና የሥራ ችሎታቸውን በመጠቀም የኑሮ ደረጃቸውን ከማሻሻል በተጨማሪ የሕይወት ትርጉምን እና ማንነታቸውን ለይተው ማወቅ የሚችሉት ከሕይወት ስኬታማነት ተነስተው እንደሆነ የተላያኡ ጥናቶች ያመለክታሉ። የተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ እና የሞያ ዓይነት የማንነት ጥያቄአቸውን ለመመለስ ስለሚያስችላቸው ነው።

በወጣቶች የትምህርት እና የስልጠና ዕድል መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ እውቀትን ለመቅሰም የሚያግዝ የመረጃ አሰባሰብ መንገድን ማወቅ ነው። ምክንያቱም መረጃን ማሰባሰብ መንገድን ማወቅ ከርቀት ትምህርት እና ስልጠና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው ነው። መረጃን የማሰባሰብ እውቀትን ለማሳደግ በቅድሚያ የመረጃ ምንጮችን እና አገልግሎታቸውን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል። የመረጃ እና የእውቀት ምንጮ የሚባሉት የብዙሃን መገናኛዎች እነርሱም ቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ እና ጋዜጣ ሲሆኑ እነዚህ ሦስቱ ቀዳሚ የብዙሃን መገናኛዎች አንድ ላይ በመሆን ዘመኑ ባመጣው በኢንተርኔት ቴክኖሎጂ በመታገዝ ወደ እያንዳንዱ የሕብረተሰብ ክፍል እንዲደርሱ ተደርገዋል።  ከዚህ የተነሳ የኢንተኔት ቲክኖሎጂ ፈጣን የመረጃ ምንጭ ከመሆን በተጨማሪ ለእውቀት እና ለባሕል ልውውጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖን በማበርከት ላይ ይገኛል።                

14 February 2019, 17:37