ፈልግ

የፓናማ ወጣቶች በወጣቶች በዓል የመስቀል መንገድ ጸሎት ላይ፣ የፓናማ ወጣቶች በወጣቶች በዓል የመስቀል መንገድ ጸሎት ላይ፣ 

ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል አጀማመርና ዓላማ (የወጣቶች ዓለም ክፍል 1)

የፍቅር ምልክት የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ወደ ዓለም በሙሉ በመውሰድ፣ ፍቅሩን፣ ሞቱንና ትንሳኤውን፣ እንዲሁም ድነት ማስገኘቱን መስክሩ

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል እንዲከበር መነሻ የሆነው እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር 1985 ዓ. ም. በቫቲካን ከተማ አንድ ልዩ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ይካሄድ ነበርና በጊዜው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወጣቶችን የሚያቀራርብ አንድ መድረክ ቢዘጋጅ በማለት ሃሳባቸውን ወደ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ዘንድ አቀረቡ። ይህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሃሳብ በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ሙሉ ተቀባይነትን አግኝቶ፣ ወጣቶች በየአገሮቻቸው፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ወደ ኢየሩሳሌም በገባበት በበዓለ ሆሳዕና ዕለት እንዲያከብሩት፣ ከዚያም በመቀጠል እንደየአመቺነቱ በየሁለት ወይም በየሦስት ዓመቱ፣ የመላው ዓለም ወጣቶች ከአገራቸው ወጥተው ወደ ተለያዩ አገሮች ሄደው የሚገናኙበት አጋጣሚ ተመቻቸ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ በቅዱስ የምሕረት ዓመት ኢዮቤልዩ መዚጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ፣ ወጣቶች ለሰው ዘር በሙሉ የፍቅር ምልክት የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ወደ ዓለም በሙሉ በመውሰድ፣ ፍቅሩን፣ ሞቱንና ትንሳኤውን፣ እንዲሁም ድነት ማስገኘቱን መስክሩ በማለት፣ በጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 22 ቀን 1984 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተገኙት በርካታ ወጣቶች መናገራቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ በወቅቱ ባሰሙት ንግግር ለወጣቶች ያስረከቡት ቅዱስ መስቀል፣ የወንጌል ምስክርነት የሚገለጥበትና የዓለም ወጣቶችን ለማገናኘት ጥሩ አጋጣሚን የሚፈጥር መሆኑን ማስረዳታቸው ይታወሳል። በዚህም መሠረት እስካሁን በ11 የዓለም ታላላቅ ከተሞች ላይ የተከበረ ሲሆን ዘንድሮ በመካከለኛው የላቲን አሜርካ አገር በሆነችው ፓናማ ከጥር 14 እስከ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ. ም. ለማከበር ዝግጅቱ መጠናቀቁ ታውቋል።           

ይህ ታላቅ ዓለም አቀፍ በዓል ለወጣቶች የሚሰጠው ትርጉምና መልዕክት ምንድነው ብለን ስንጠይቅ ለዚህ ጥያቄ ቀዳሚ መልስ የሚሆነን፣ የመላው ዓለም ወጣቶች ምንም እንኳን በአገር፣ በባሕልና በቋንቋ ቢለያዩ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሠረታት ቤተክርስቲያን ውስጥ አንድ መሆናቸውን ተገንዝበው በሕብረት በመሆን በጋራ ለመጸልይ፣ በበዓሉ ወቅት የሚሰጣቸውን የተስፋ እና የፍቅር መልዕክት ተቀብለው ለሌሎች እንዲያስተላልፉ ለማድረግ ነው። ይህ በሚሆንበት ጊዜ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትም ከወጣቶቹ ጋር በመሆን የበዓሉን ውበት ይመለከታሉ፣ በአባታዊ ምክራቸውና አስተምህሮአቸው አማካይነት ወጣቶችን ያስተምራሉ፣ ያጽናናሉ፣ ያበረታታሉ።

01 February 2019, 17:20