ፈልግ

ክቡር አባ ሀጎስ ሐይሽ ክቡር አባ ሀጎስ ሐይሽ  

የቅዱስ ሉቃስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሆስፒታል የላቀ አገልግሎት ጥራት ተሸላሚ ሆኖ

በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚተዳደረው እና በእንድብር አገረ ስብከት ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ሉቃስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሆስፒታል የኢትዮጲያ የሕክምና ማኅበር 2011 ዓ.ም የላቀ አገልግሎት ጥራት ተሸላሚ ሆኖ መመረጡ ተገለጸ።  የቅዱስ ሉቃስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሆስፒታል እና የነርሶች እና አዋላጆች ማሰልጠኛ ኮሌጅ በወሊሶ ከተማ የሚገኝ ሲሆን 200 ሰዎችን በአንድ ጊዜ ልያስተናግዱ የሚችሉ አልጋዎች ያሉት እና በቀን ከ 400 በላይ ለሚሆኑ ተመላላሽ ታካሚዎች የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደ ሚገኝ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን በአመት ውስጥ ብቻ ከ8000 በላይ ቀላል፣ መለስተኛ እና ከባድ የቀዶ ጥገና አገልግሎት ለሕብረተሰቡ በመስጠት ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ለሕዝቡ ተደራሽ በማድረግ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጲያ እያከናወነች የምትገኘውን ሁለንተናዊ (መንፈሳዊ እና ሰብዓዊ) አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ በመደገፍ ላይ የሚገኝ የሕክማና መስጫ ተቋም እንደ ሆነም ይታወቃል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ቅዱስ ሉቃስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሆስፒታል እና የነርሶች እና አዋላጆች ማሰልጠኛ ኮሌጅ የሕክምና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ብቃት ያላቸውን ነርሶች እና አዋላጆችን በተገቢው ሁኔታ በማሰልጠን ብቁ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎችን በማፍራት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለአገራችን ለኢትዮጲያ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠንክራ ትቀጥል ዘንድ የበኩሉን አስተዋጾ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሆስፒታል ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከአንድ መቶ በላይ ነርሶች እና አዋላጆች በኮሌጁ የሕክምና ሙያ እያጠኑ/እየሰለጠኑ እንደ ሚገኙ በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋና ጽሕፈት ቤት ቃል አቃባይ የሆነቺው ማክዳ ዮሐንስ በተለይ ለቫቲካን ዜና ካደረሰችው መረጃ ለመረዳት ተችሉዋል።

ቅዱስ ሉቃስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሆስፒታል እና የነርሶች እና አዋላጆች ማሰልጠኛ ኮሌጅ የኢትዮጲያ የሕክምና ማኅበር ባዘጋጀው የ2011 ዓ.ም የላቀ አገልግሎት ጥራት ተሸላሚ ለመሆን የበቃው በተለይም ደግሞ በአሁኑ ወቅት ጥራቱን እና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በተለይም ደግሞ ድሃ ለሚባሉ እና ከገጠራማ አከባቢዎች ለሚመጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች እያደርገ ለሚገኘው ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እውቅና ተሰጥቶት ለመሸለም መብቃቱ የተገለጸ ሲሆን የኢትዮጲያ የሕክምና ማኅበር በየካቲት 15/2011 ዓ.ም ባደረገው 55ኛው አመታዊ ጉባሄ ላይ ይህ የቅዱስ ሉቃስ ካቶሊክ ሆስፒታል እና የነርሶች እና የአዋላጆች ማሰልጠኛ ኮሌጅ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጾ በእለቱ የክብር እንግዳ ሆነው በተጋበዙት እና የኢትዮጲያ የጤና ምንስቴር ሚንስትር በሆኑት በዶክተር አሚር አማን አማካይነት የላቀ አገልግሎት ጥራት ሽልማ በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ሐጎስ ሐይሽ በተገኙበ እና እንዲሁም የሆስፒታሉ ጠቅላይ አስተዳዳሪ ለሆኑት ሲስተር ክላራ ሮዝሊን ሽልማቱ መበርከቱን ከደረሰን ዜና ለመረዳት ተችሉዋል።

በኢትዮጲያ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ የሆኑት ክቡር አባ ሐጎስ ሐይሽ በወቅቱ ባደርጉት ንግግር እንደ ገለጹት የኢትዮጲያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመላው አገሪቱ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ 86 የሕክምና አገልግሎት መስጫዎች እና የማገገሚያ ተቋማት እንደ ሚገኙ ጠቅሰው እነዚህ የሕክምና መስጫ ተቋማት በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱትን የክርስቶስ አስተምህሮዎችን በመከተል የአገሪቷ ሕዝቦች ጤናቸው የተጠበቀ ይሆን ዘንድ የበኩላቸውን አስተዋጾ እያበረከቱ እንደ ሆነ ገልጸው አሁን የኢትዮጲያ የሕክምና ማኅበር ለሆስፒታሉ ስላበረከተው የላቀ አገልግሎት ጥራት ሽልማት አመስግነዋል።

የቅዱስ ሉቃስ ካቶሊክ ሆስፒታል እና የነርሶች እና የአዋላጆች ማሰልጠኛ ኮሌጅ ጠቅላይ አስተዳዳሪ የሆኑት ሲስተር ካላራ በበኩላቸው እንደ ገለጹት “ይህ ሆስፒታል እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ እውቅና እንዲያገኝ እና ተሸላሚ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጾ ያደርጉት የኢትዮጲያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና አጋር ድርጅቶች ባበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጾ ምክንያት እንደ ሆነ ገልጸው፣ ሆስፒታሉ ከዚህ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ባለድርሻ አካላት እይደርጉት የሚገኙውን ከፍተኛ ድጋፍ አጠናክረው ይቀጥሉ” ዘንድ ጥሪ ማድረጋቸውን ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ተችሉዋል።

ምንጭ፥ የኢትዮጲያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጽሕፈት ቤት የፌስ ቡክ ገጽ ላይ በየካቲት 16/2011 ዓ.ም የተወሰደ።

(www.facebook.com/Ethiopian-Catholic-Secretariat-1636937599857740/) 

 

25 February 2019, 15:55