ፈልግ

የካዛ ብላንካ ከተማ ከሩቅ ሲታይ  የካዛ ብላንካ ከተማ ከሩቅ ሲታይ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት በተስፋ የሚጠበቅ መሆኑ ተገለጸ።

ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ክርስቶባር ሎፔዝ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በተመለከተ የግል አስተያየታቸውን ሲገልጹ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ የሚመጡት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገለጥበት መሣሪያ በመሆን፣ የኢየሱስን ክርስቶስን መልካም ዜና ለማብሰር ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሞሮኮ ዋና ከተማ ራባት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ክርስቶባል ሎፔዝ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት አስመክተው ባደረጉት ገለጻ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት በተስፋ እንደሚጠበቅ ገልጸው በሙስሊም እና ክርስቲያን መካከል ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ሎፔዝ በሞሮኮ ከ1995 ዓ. ም. ጀምሮ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በማበርከት ላይ መሆናቸው ሲታወቅ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የራባት ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ሆነው በማገልገል ላይ መሆናቸው ታውቋል። በሞሮኮ ወደ 50, 000 የሚጠጉ ካቶሊካዊ ምእመናን እንደሚገኙ ሲገመት ከእነዚህም መካከል አብዛኛው አውሮጳዊያን መሆናቸው ታውቋል።

የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ትርጉም ያለው ነው፣

ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ክርስቶባል ሎፔዝ በንግግራቸው እንደገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ሞሮኮ ይሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከፍተኛ ትርጉም ያለው እንደሆነ ገልጸው በሁለት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው፣ ሁለቱን ከተሞች ማለትም ራባትን እና ካዛ ብላንካን እንደሚጎበኙ አስታውቀዋል። በእነዚህ ቀናት ውስጥ በካሪታስ ካቶሊካዊ የእርዳታ አድራጊ ድርጅት የሚታገዘውን የስደተኞች መጠለያ ማእከልን የሚጎበኙ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ቀጥለውም መሐመድ አምስተኛ የእስልምና እምነት መምህራን ማሰልጠኛ ማዕከልን፣ ከሞሮኮ ንጉሥ መሐመድ 6ኛ እና ከሞሮኮ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር እንደሚገናኙ ገልጸዋል።  

የሞሮኮ ካቶሊካዊ ማሕበረሰብ፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀዳሚ ተልዕኮ፣ ሊቀ ጳጳሳት ክርስቶባር ሎፔዝ እንደገለጹት፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀዳሚ ተልዕኮ፣ በእምነታችን ሊያበረታቱን ነው ብለው፣ ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስነታቸው በሞሮኮ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን ለማወቅ፣ ሕይወቷንም ለመጋራት፣ ሊያበረታቷት፣ ከምዕመናኑ ጋር አብረው ለመጸለይ እና ሊባርኩን ነው ብለዋል። ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ክርስቶባር ሎፔዝ፣ በሞሮኮ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ሕብረት እንዲያድግ ትልቅ ፍላጎት መኖሩን ገልጸው እንደዚሁም ከሌሎች እምነቶችም ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ግንኙነት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን አስረድተዋል።

የሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ክርስቶባል ሎፔዝ የግል አስተያየት፣

ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ክርስቶባር ሎፔዝ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በተመለከተ የግል አስተያየታቸውን ሲገልጹ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ የሚመጡት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገለጥበት መሣሪያ በመሆን፣ የኢየሱስን ክርስቶስ መልካም ዜና የሆነውን ቅዱስ ወንጌልን ለማብሰር ነው ብለዋል። በመሆኑም ከምዕመናኑ ይሁን ከሕዝቡ የሚጠበቀው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚያስተላልፉትን መልዕክት፣ በቃል ሆነ በአካል የሚያቀርቡትን ምስክርነት በሚገባ ለማዳመጥ መዘጋጀት ነው ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ሞሮኮ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት መጋቢት 21 እና 22፣ 2011 ዓ. ም. እንደሆነ የጉዞአቸው መርሃ ግብር ያስረዳል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!

 

28 February 2019, 15:59