ፈልግ

ፓትሪያርክ ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ 1ኛ፣ ፓትሪያርክ ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ 1ኛ፣  

በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለሚታዩት ግጭቶች የምዕራቡ ዓለም ሃላፊነት አለበት።

የምዕራቡ ዓለም ሃይል በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የነዋሪውን ሕዝብ መብት የሚያስጠብቅ እና ሕግን የሚያስከብር ራስ ገዝ መንግሥት እንዲቋቋም ወይም እንዲመሠረት የሚል ድጋፍ አድርጎ አያውቅም

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች የሚታየውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ሲወያይ የቆየው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ስብጥር በ55ኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ለሚታዩት ግጭቶች የምዕራቡ ዓለም ሃላፊነት እንዳለበት አስታወቁ። እስከ ትናንት የካቲት 12 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ በጀርመን ሙኒክ ከተማ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከመካከለኛው የምስራቅ አገሮች የተወጣጡ የአብያተክርስቲያናት ታላላቅ መሪዎች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በኢራቅ የባቢሎን ካልዲያ ስርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ 1ኛ እና በሶርያ የአንጾኪያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ኢኛሲዮ ኤፍሬም ሁለተኛ መገኘታቸው ታውቋል።

ፊደስ በተሰኘ የዜና ማዕከል ዘገባ መሠረት በዚህ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ የተገኙት ሁለቱ ፓትሪያርኮች ከዚህ በፊት በሌሎች አካባቢዎች በተካሄዱት ስብሰባዎች ላይ፣ ከተለያዩ የፖለቲካ መሪዎች ጋር ለመገናኘት እድል ያገኙ መሆናቸውን ገልጿል። የካቲት 9 ቀን 2011 ዓ. ም. የሃንስ ሴይደል ፋውንዴሽን ባዘጋጀው የእምነት ተወካዮች እና መሪዎች ስብሰባ ላይ፣ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ የሚካሄዱ ጦርነቶችንን እና አለመረጋጋቶችን በማስመልከት ወይይቶች መደረጋቸውን ፊደስ የዜና ማዕከል አክሎ ገልጿል።  

የምዕራቡ ዓለም በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ራስ ገዝ መንግሥት ምስረታን ደግፎ አያውቅም፣

በኢራቅ የባቢሎን ካልዲያ ስርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ 1ኛ ለስብሰባው ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር ባለፉት መቶ ዓመታት ውስጥ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የክርስትያን ማኅበረሰብ ሁኔታ በግልጽ እንዳይታወቅ ጥረት ተደርጓል ብለው ከኦቶማን ዘመነ መንግሥት ወዲህ አካባቢውን የተቆጣጠረው የምዕራቡ ዓለም ሃይል በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የነዋሪውን ሕዝብ መብት የሚያስጠብቅ እና ሕግን የሚያስከብር ራስ ገዝ መንግሥት እንዲቋቋም ወይም እንዲመሠረት የሚል ድጋፍ አድርጎ አያውቅም ብለዋል።

የምዕራቡ ዓለም ፖለቲካ ለመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ግጭቶችን ድጋፍ አድርጓል፣

የኢራቅን ታሪክ ያስታወሱት ፓትሪያርክ ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ 1ኛ፣ በ1995 ዓ. ም. ከሳዳም ሁሴን አገዛዝ ውድቀት ወዲህ በኢራቅ አለ የሚባል ተቋማዊ የፖለቲካ እንዳልተመሠረተ ገልጸው ይባስ ብሎ የተለያዩ አማጺ የፖለቲካ አንጃዎች ተነስተው ወይም አድገው ለአመጽ እና ለሙስና በር ከፍተዋል ብለዋል። ፓትሪያርክ ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ 1ኛ በማከልም የምዕራቡ ዓለም ፖለቲካ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ግጭቶች እንዲበራከቱ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል። የምዕራቡ ዓለም በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ያራመደው የፖለቲካ አቋም ኤኮኖሚያዊ እንጂ ፖለቲካዊ አይደለም ብለው ለዚህም ዋና ማስረጃ የሚሆነው በአካባቢ አገሮች የነዳጅ ምርትን ጨምሮ በሌሎች  የተፈጥሮ ሃብቶች ላይ ያደረገውን የበላይነት መጥቀስ ይቻላል ብለዋል። በመሆኑም በአካባቢ አገሮች መሠረታዊ የሰው ልጆች መብቶች እና የእምነት ነጻነቶች አልተከበሩም ብለዋል።

የባግዳድ መንግሥት የተሰደዱትን ለመመለስ ጥረት አላደረገም፣

በጦርነት እና በአመጽ ምክንያት በኢራቅ ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉትን እና የተሰደዱትን ለመለስ የሚያግዝ ጥረት ከባግዳድ መንግሥት በኩል እንዳልተደረገ የገለጹት ብጹዕ ፓትሪያርክ ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ 1ኛ መንግሥት ይባስ ብሎ ለመኖሪያ ቤቶች እድሳት  የገንዘብ ድጋፍን እንዲያደርጉ በማለት ተፈናቃዮች እንደጠየቀ ገልጸዋል። የመካከለኛው ምስራቅ አገሮችን ከባድ ስቃይ እና መከራ ደርሶባቸዋል ያሉት፣ በኢራቅ የባቢሎን ካልዲያ ስርዓተ አምልኮን የምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ 1ኛ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች አሁን ከሚገኙበት መከራ ሊወጡ የሚችሉት በአካባቢ አገሮች የሚገኙ ዜጎች የእኩልነት መብት ሲረጋገጥ በዜጎች ላይ የሚደረግ ልዩነት ሲወገድ እና የጽንፈኝነት ርዕዮተ ዓለም ሲወገድ ነው ብለዋል። ብጹዕ ፓትሪያርክ ሉዊስ ሩፋኤል ሳኮ 1ኛ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ወደ ባሕረ ሰላጤ አገር ወደ ሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያደረጉትን 27ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት አስታውሰው በጉብኝታቸው ወቅት ከአል አዛር ታላቁ ኢማም ከሆኑት ከአል ጣይብ ጋር ሰብዓዊ ወንድማማችነት የሚል ሰነድ መፈራረማቸውን አስታውሰዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
20 February 2019, 14:56