ፈልግ

የሕንድ የጦር አውሮፕላን የሕንድ የጦር አውሮፕላን  

የፓክስታን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በሕንድ እና በፓክስታን መካከል ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ተማጸኑ።

ብጹዕ አቡነ ሳምሶን በማከልም የሁለቱም አገሮች የፖለቲካ መሪዎች በመካከላቸው ያሉትን ችግሮች ለማቃለል ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲቀርቡ በማለት የፓክስታን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት መማጸናቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሕንድ እና በፓክስታን መካከል ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው የፓክስታን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በሁለቱ አገሮች መካከል የሰላም ውይይት እንዲደረግ ጠይቀዋል። በሌላ ወገን ማክሰኞ የካቲት 19 ቀን 2011 ዓ. ም. የሕንድ የጦር አውሮፕላን የፓክስታንን የአየር ክልል ዘልቆ በመግባት ጥቃት ማካሄዱን የሕንድ መንግሥት አስታውቋል። ጥቃቱን ያካሄደው በያይሽ ኢ መሀመድ በተባለ እስላማዊ ታጣቂዎች ማሰልጠኛ ካምፕ ላይ እንደሆነ ገልጾ በጥቃቱም በርካታ ታጣቂዎች መገደላቸውን አስታውቋል። የፓክስታን መንግሥት በበኩሉ የሕንድ መንግሥት አደረስኩ ያለውን ጥቃት አስተባብሎ፣ የሕንድን ወረራ አውግዞ ወታደራዊ ምላሽ እንደሚሰጥ መዛቱ ታውቋል።

በሕንድ እና በፓክስታን መካከል በድንገት ለተቀሰቀሰው ጥላቻ ምክንያቱ የካቲት 7 ቀን 2011 ዓ. ም. በካሽሚር ግዛት ውስጥ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ቢያንስ 40 በሚሆኑ የሕንድ ፖሊሶች ላይ የሞት አደጋን በማስከተሉ ነው ተብሏል። በሕንድ ፖሊሶች ላይ ደረሰ ለተባለው ጥቃት፣ መሸሸጊያውን በፓክስታን ውስጥ ያደረገ ያይሽ እስላማዊ ታጣቂ ግንባር ሃላፊነት መውሰዱን አስታውቋል።

በካሽሚር የተፈጸመውን የአሸባሪነት ተግባር እንዲሁም የጦር መሣሪያ ጥቃቶችን አጥብቀን እናወግዛለን ያሉት በፓክስታን የሃይደራባድ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሳምሶን ሹካርዲን፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ወደ ጦርነት የሚመሩ ተግባራት እንዳፈጸሙ፣ እግዚአብሔር የሰዎችን ልብ እንዲለውጠው እንጸልያለን ብለዋል። ብጹዕ አቡነ ሳምሶን በማከልም በጥቃቱ ለሞቱት በሙሉ እንዲሁም በሕንድ እና በፓክስታን መካከል ሰላም ይወርድ ዘንድ እንጸልይ በማለት ፊደስ ለተባለ የቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

የአሸባሪ ቡድኖችን ማስተናገድ፣

የሕንድ መንሥት ፓክስታን በግዛቷ ውስጥ ለአሸባሪ ቡድኖች መሸሸጊያን ታዘጋጃለች በማለት ስሞታን ስታቀርብ መቆየቷ ሲነገር፣ በካሽሚር ግዛት ውስጥ በተገደሉት ቢያንስ አርባ ለሚሆኑ የሕንድ ፖሊሶች ሞት የፓክስታን የደህንነት አባላት እጅ አለበት በማለት ክስ ማቅረቧ ታውቋል። በሕዳር ወር 1994 ዓ. ም. የያይሽ ኢ መሐመድ አሸባሪ ታጣቂ ቡድን በፓክስታን ከሚገኝ ላሽካር ኢ ጣይባ ከተባለ ሌላ አሸባሪ ቡድን ጋር በመወገን በሕንድ ፓርላማ ላይ ጥቃት ማድረሱ ሲታወስ ይህም በሁለቱ አገሮች መካከል አራተኛ ዙር ጦርነት ሊቀሰቅስ እንደነበር ይታወሳል። የካሽሚር ግዛት አብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚገኙበት እና ለበርካታ ዓመታት ያሕል በሕንድ እና በፓክስታን መካከል ለሚከሰቱት ግጭቶች ምንጭ እንደሆነ ሲታወቅ ሁለቱም አገሮች በገሚስ ከሚያስተዳድሩት የካሽሚር ጋዛት ባሻገር ሙሉ የካሽሚር ግዛት ይገባኛል የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወቃል። የፓክስታን መንግሥት በበኩሉ በግዛቱ አሉ ለተባሉ አሸባሪ ቡድኖች መሸሸጊያ እንደማትሰጥ ማሳወቋ ታውቋል።                

ግጭት እየተስፋፋ መምጣቱ ይነገራል፣

የሕንድ መንግሥት ያለፈው ማክሰኞ የካቲት 19 ቀን 2011 ዓ. ም. የወሰደችው የአየር ጥቃት፣ ያይሽ ኢ መሀመድ የተባለ እስላማዊ ታጣቂዎች በግዛቷ ጥቃትን ለመፈጸም እያቀደ ስለ መሆኑ መረጃዎች ስለደረሱኝ ነው ብላለች። ከዚህም በተጨማሪ የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋና ጸሐፊ አቶ ቪያይ ጎካለ፣ የከፋ አደጋ ይከሰታል ተብሎ በሚታሰብበት ጊዜ የሚወሰድ የማስጠንቀቂያ ምልክት ማሳየት አስፈላጊ እንደሆነ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በፓክስታን ውስጥ የሚገኘው ብዛት ያለው የስልጠና መሣሪያ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልጣኞች መኖራቸውን የፓክስታን መንግሥት አያውቀውም ማለት ይከብዳል ብለዋል።  የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ናደንድራ ሞዲ በበኩላቸው አገራቸውን ለጥቃት አሳልፈን አንሰጥም ብለዋል።

የፓክስታን ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኢራን ካን፣ ሕንድ አደረስኩ ያለችውን የአየር ላይ ጥቃት አውግዘው ፓክስታን ከሕንድ ለተሰነዘረባት ጥቃት በምትፈልገው ጊዜና ስፍራ የአጸፋ ጥቃት ልታካሂድ እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።

አንዱ ሌላውን ጥፋተኛ ከማድረግ ይልቅ የሁለቱም አገሮች መሪዎች ለሰላም ቅድሚያን በመስጠት በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ፣ በፓክስታን የሃይደራባድ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሳምሶን ሹካርዲን አሳስበዋል። ብጹዕ አቡነ ሳምሶን በማከልም የሁለቱም አገሮች የፖለቲካ መሪዎች በመካከላቸው ያሉትን ችግሮች ለማቃለል ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መቅረብ እንደሚያስፈልግ የፓክስታን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት ይጠይቃሉ ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
28 February 2019, 16:19