ፈልግ

የየካቲት 17/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘመርዓዊ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

“እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም”

በእለቱ የተነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች
1. ሮሜ 9፡1-16
2. 1ጴጥሮስ፡ 2፡20-25
3. ዮሐንስ 4፡1-26

በእለቱ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል

ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትገኘው ሲካር ወደ ምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ። በዚያም የያዕቆብ የውሃ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ የተነሳ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ። ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም “ውኃ አጠጪኝ!” አላት፤ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። 
ይህችም ሳምራዊት ሴት ኢየሱስን “አንተ የይሁዳ አገር ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከሆንኩት ከእኔ ውሃ እንዴት ትጠይቃለህ?” አለችው። አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። ኢየሱስ መልሶ “የእግዚአብሔርን ስጦታና ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ ኖሮ አንቺው ራስሽ ትለምኚው ነበር፣ እርሱም የሕይወትን ውኃ ይሰጥሽ ነበር” አላት። 
ሴቲቱ “ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል” አለችው። ኢየሱስም መልሶ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት። ሴቲቱ ጌታ ሆይ፥ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ አለችው። ኢየሱስም ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነይ አላት። ሴቲቱ መልሳ ባል የለኝም አለችው። ኢየሱስ ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ፤ አምስት ባሎች ነበሩሽና፥ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነት ተናገርሽ አላት። ሴቲቱ ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አሁን አወኩኝ። አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ሴቲቱ ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው። ኢየሱስ የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት። (ዮሐንስ 4፡5-26)

የእለቱ ቃለ እግዚኣብሔር አስተንትኖ

በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!
ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር ዘመርዓዊ ወይንም ዘጥምቀት-አስተርዬ 6ኛ የሚለውን ሰንበት እናከብራለን፡፡ በዚህም እለት የእግዚአብሔር ቃል ሊያስተምረን የሕይወትን መንገድ ሊያመላክተን በተነበቡት ምንባባት አማካኝነት ወደ እያንዳንዳችን መጥቶ የልባችንን በር ያንኳኳል፡፡
ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መልእክቱ ልቡ በታላቅ ሃዘንና ጭንቀት ላይ እንዳለ ይነግረናል፡፡ ምክንያቱም አይሁዳውያን በመጀመሪያ የመዳን መብትና የእግዚአብሔር ልጅነትን መንፈስ እንዲቀበሉ ዕድል ቢሰጣቸውም ይህንን ባለመቀበላቸው ምክንያት የደህንነትን ጊዜ በከንቱ አሳለፉ፣ ይህ ደግሞ ለቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ መንፈሱን በጣም እረብሾት ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ በተፈጠረው ሁኔታ ወንጌል ለአረማውያን እንዲሰበክ ዕድል ተከፈተ፡፡ በእድሉም በመጠቀም እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች ወንጌልን ተቀበሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሥም ተጠመቁ፡፡
ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱ አይሁዳዊ ነው፣ ሆኖም እነዚህ ወንድሞቹና እህቶቹ አይሁዳውያን ከድህንነት መንገድ በመራቃቸው ምክንያት ልቡ በጣም ያዝን ነበር፡፡ ምን አልባትም እነርሱ ወንጌልን ተቀብለው ቢጸኑና እርሱ ግን በእርሱ ምትክ የዘለዓለምን ደህነነት ቢያጣ ይመኝ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ ለሌሎች ካለው ፍቅርና ዘለዓለማዊ ደህንነትነ እንዲያገኙ ካለው ጉጉት የተነሣ ነው፡፡
እግዚአብሔር አይሁዳውያንን የራሱ ምርጥ ሕዝቦች እንዲሆኑ መርጧቸው ነበር። የእርሱም ልጅነትን መብት ሰጥቷቸው ነበር፣ ክርስቶስ የሚባል አዳኝ እንደሚልክላቸውም ቃል ገብቶላቸው ነበር፣ እነርሱ ግን ይህንን ምክንያት እልተቀበሉም፡፡ “አብርሃም በእምነቱ ምክንያት ፃድቅ ተብሎ እንደተጠራ ሁሉ” (ዘፍ.15፡6) ምን አልባት አይሁዳውያንም እምነታቸውን በክርስቶስ ቢያፀኑ ኖሮ እነርሱም ፃድቅ ተብለው በተጠሩ ነበር፡፡
በእርግጥ ከአይሁዳውያንም የክርስቶስን ነቢይነት የተቀበሉ አሉ እነዚህ እውነተኛ አይሁዳውያን ናቸው፡፡ እይሁዳውያን ሁሉ “የአብርሃም ዘር ነን” ቢሉም እንደ እሱ እንደ አብርሃም እምነት የሌላቸው ሁሉ እውነተኛ አይሁዳዊ አይደሉም፡፡ እውነተኛ አይሁዳውያን ልክ እንደ አብርሃም ይሰሐቅ ያዕቀብ እምነታቸው በእግዚአብሔር የፀናና የእርሱን የተስፋ ቃሉ ያመኑት ብቻ ናቸው፡፡ ሮሜ.2፡28 እንዲህ ይላል፡፡ “አንድ ሰው ለይምሰል በውጫዊ ብቻ አይሁድ ልሁን ቢል አይሁዳዊ አይሆንም ዳሩ ግን አንድ ሰው አይሁዳዊ የሚሆነው በውስጣዊ ማንነቱ እይሁድ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ በተመሣሣይ መልኩ አንድ ክርስቲያን እኔ የክርስቶስ ተከታይ ነኝ ስላለ ብቻ የክርስቶስ ተከታይ አይሆንም። ክርስቶስን ለመከተል እርሱ እንዳዘዘን በየዕለቱ መስቀሉን ተሽክሞ መከተል ያስፈልጋል፡፡ “ሊከተለኝ የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” (ማቴ. 16፡24) ይላል። ስለዚህ የክርስቶስ ተከታይ ነኝ ብለን ለመናገር አካሄዳችንን አኗኗራችንን ተግባራችን መልስ ብለን ልንመለከተው ይገባል፣ አካሄዳችን አኗኗራችን ተግባራችን ራሱ በሕሊናችን አማካኝነት የክርስቶስ ተከታይ መሆን አለመሆናችንን ይነግረናል፡፡ 
በዛሬው 2ኛ ንባባ ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ኃጢአትን ሳያደርግ በአፉ ክፉ ሳይናገር ሲሰድቡት መልሶ ሳይሳደብ መከራ ሲያደርሱበት በእነርሱ ላይ ሳይዘት በመስቀል ተሰቅሎ እንዳዳነን ይናገራል፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣውን ክፉ ሁሉ በመልካም እንዲሸነፍ ይናገራል ስለዚህ እውነተኛ የክርስቶስ ተከታይ የሆነ ሁሉ ይህንን የክርስቶስን አብነት መከተል ግድ ነው፡፡ ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ ክፉ ሰርተን ብንቀጣ ወይንም ብንታገሥም ምንም ምሥጋና ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደማናገኝ ይናገራል፡፡ በአንፃሩ መልካም ሰርተን በምላሹ መከራ ብንሸለምና ብንታገሥ ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከት እንደሚያስገኝ ያስተምረናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ስለ ራሳችን ሕይወት መለስ ብለን ስናስተነትን ትንሽ ለሠራናት ነገር ትልቅ ምሥጋናን እንሻለን የሚደርስብንን ትንሽ ክፉ ነገር እኛ እጥፍ ድርብ አድርገን ለመመለስ እናሴራለን፡፡ በአንፃሩ መልካም ሰርተን በምላሸ መከራን በንሽለምና ብንታገሥ ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከት እንደሚያስገኝ ያስተምረናል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ስለ ራሳችን ሕይዋት መለስ ብለን ስናስተነትን ትንሽ ለሠራናት ነገር ትልቅ ምሥጋናን እንሻለን የሚደርስብንን ትንሽ ክፉ ነገር እኛ እጥፉ ድርብ አድርገን ለመመለስ እናሴራልን፡፡ ይህ ግን እንከተለዋለን ከምንለው ከክርስቶስ መንገድ የራቀ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ሕይወታችንን የምንመራ ከሆንን ቅዱስ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደሚለው ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንኖራለን ሳይሆን ለኃጢአት ኖረን ለጽድቅ እንሞታለን ይሆናል፡፡
በዛሬው በዮሐንስ ወንጌል በምዕራፍ 4 ስለ ሳምራዊቷ ሴት ይናገራል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማርያ ያዕቆብ ለልጁ ለዩሴፍ በሰጠው ቦታ አጠገብ ሲካር ወደምትባል ከተማ መጣ በዛም ደክሞት ስለነበር በያዕቆብ የውሃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ፡፡ በዚህ ጊዜ ነው አንድ ሳምራዊት ውሃ እንድታጠጣው የጠየቃት እሷም በመገረም አንተ አይሁዳዊ ሆነህ እኔን ሳምራዊቷን እንዴት ውሃ አጠጪኝ ብለህ ትጠይቀኛለህ አለችው፡፡ ሳምራዊቷ ይህን ማለቷ ተገቢ ነበር ምክንያቱም አይሁዳዊያንና ሳምራዊያን እይዋደዱም ምክንየቱም ሳምራዊያን በፊት አይሁዳውያን ነበሩ በኃላ ግን በአሦራዊያን ከተሸነፉ በኃላ አሦራውየን ብዙ ባዕዳንን አምጥተው በሳምራዊያን ምድር አሰፈሩ ከዛም አብዛኞቹ ከሳምራውያን ጋር ተጋቡ የእነርሱንም የባዕድ አምላክ ተከተሉ (2ነገሥት 17፡22-33) በዚህም ምክንያት እንደ ሙሉ አይሁዳውያን አይቆጠሩም በአይሁዳውያን ቤተመቅደስም ገብተው መጸለይ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ ከብዙ ቆይታ በኃላ የራሳቸው ቤተ መቅደስ ቢሰሩም አይሁዳውያን አቃጠሉባቸው በዚህም የተነሣ በመካከላቸው ትልቅ ጥላቻ አለ በዚህ ምክንያት ነው አንተ አይሁዳዊ ሆነህ እኔን ሳምራዊቷን ውሃ አጠጭኝ ብለህ ትጠይቀኛለህ ያለችው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን “ውሃ አጠጭኝ ያለሽ ማን መሆኑን ብታውቂ ኖሮ አንቺ ራስሽ በጠየቅሽኝ ነበር እርሱም የሕይወት ውኃ ይሰጥሽ ነበር” አላት፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረው የሕይወት ውሃ ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ አዲስ መንፈሳዊ ሕይወት ምንጭ ስለሆነው ስለ ራሱ ነበር፡፡ ሳምራዊቷ ይህ ጌታችን ኢየሱስ ክረስቶስ የሚናገረውን ቃል አልተረዳችም ለዚህ ነው አንተ ይህንን ጉድጓድ ከሰጠን ከያዕቀብ ትበልጣለህን ያለችው፡፡ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ መለሰላት ከዚህ ውሃ የሚጠጣ ሁሉ እንደገና ይጠማል እኔ ከምሰጠው ውሃ የሚጠጣ ግን ከቶ አይጠማም አላት፡፡ 
እውነት ነው አንድ ሰው የዘለዓለም ሕይወት ከሆነው ከጌታችን ኢየሲስ ክርስቶስ ጋር ጥሩ ሕብረት ካለው በምንም ዓይነት መልኩ ሊጠማም ሊራብም አይችልም ምክንያቱም በውስዩ የዘለዓለም ሕይወት ምንጭ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዟልና ነው፡፡ስለዚህ ሁላችን በእውነተኛ ክርስቲያናዊ መንፈስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን መንፈሳዊ የሕይወት ምንጭ የሆነውን ውኃ እንዲሰጠን ዘወትር እንድንለምንና አብረን እንድሆን ያስፈልጋል፡፡
በማቴ.5፡6 ላይ እንደሚናገረው ዘወትር ጽድቅን እንድንራብ እደንጠማ ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ጠንካሮች እንድንሆን ዘወትር የሕይወት ምንጭ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መፈለግ እርሱን መራብ እርሱን መጠማት ያስፈልገናል፡፡ ይህንንም ለማድረግ እንድንችል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርየም ከልጇ ይህንን ጸጋና በረከት ታማልደን፡፡ 
ምንጭ፡ ሬዲዮ ቫቲካን የአማርኛ ክፍል

21 February 2019, 15:11