ፈልግ

የየካቲት 03/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተስርእዮ 4ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የየካቲት 03/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተስርእዮ 4ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የየካቲት 03/2011 ዓ.ም ሰንበት ዘአስተስርእዮ 4ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

እናቱ ማርያምም ልጄ ሆይ፣ ለምን እንዲህ አደረግህን? አባትህና እኔ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር አለችው።

በእለቱ የተነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች

1.         ገላቲያ 4፡21-31

2.       1 ጴጥሮስ 2፡1-8

3.       ሐዋ 5፡ 17-28

4.       ሉቃስ 2፡41-52

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ዮሴፍና ማርያም በያመቱ በፋሲካ በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ይሄዱ ነበር።  ኢየሱስ አሥራ ሁለት ዓመት በሆነውም ጊዜ እንደ ተለመደው በዓሉን ለማክበር ሄዱ። በዓሉ ከተፈጸመ በኋላ እነርሱ ወደ ቤት ሲመለሱ በኢየሩሳሌም ቀረ፣ ዮሴፍና ማርያም ግን እዚያ መቅረቱን አላወቁም ነበር። ከመንገደኞች ጋር የነበረ ስለ መሰላቸው የአንድ ቀን መንገድ ሄዱ፥ ከዘመዶቻቸውም ከሚያውቋቸውም ዘንድ ፈለጉት፤ ባጡትም ጊዜ እየፈለጉት ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

ከሦስት ቀንም በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቅደስ አገኙት፤  የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ።  ባዩትም ጊዜ ተገረሙ፥ እናቱም። ልጄ ሆይ፥ ለምን እንዲህ አደረግህብን? እነሆ፥ አባትህና እኔ እየተጨነቅን ስንፈልግህ ነበርን አለችው።  እርሱም ስለ ምን ፈለጋችሁኝ? በአባቴ ቤት እሆን ዘንድ እንደ ሚገባኝ አላወቃችሁምን? አላቸው።

እነርሱም የተናገራቸውን ነገር አላስተዋሉም።  ከእነርሱም ጋር ወርዶ ወደ ናዝሬት መጣ፥ ይታዘዝላቸውም ነበር። እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።  ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ያድግ ነበር።

የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

“ቤተሰብ በጣም ጠቃሚ የሆነ እሴት ያለው በመሆኑ የተነሳ ትኩረትን በመስጠት መንከባከብ ያስፈልጋል”

በዛሬው ስርዓተ አምልኮ ስርዓታችን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇ ኢየሱስ ክርስቶስና ከቅዱስ ዮሴፍ ጋር ሆነው በታላቅ ፍቅር በመታገዝ የኖሩትን ሕይወት እንድናሰላስል ትጠይቀናለች። በተጨማሪም ይህ ቤተሰብ በእግዚአብሔር ላይ ባደረጉት እምነት አማካይነት ሕይወቱን እንደመራ እንመለከታለን። በሉቃ. 2. 41-52 የተነበበው የዕለቱ ንባብ፣ ይህ የናዝሬት ከተማ ነዋሪ የሆነው ቤተሰብ ማለትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስና ቅዱስ ዮሴፍ የፋሲካን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ያደረጉትን የጉዞ ሁኔታ ያብራራል። ከበዓሉ መልስ ወደ ቤታቸው በሚመለሱበት ሰዓት የአስራ ሁለት ዕድሜ ልጃቸው ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው አለመሆኑን ያስተውላሉ። በዚህም ምክንያት እጅግ በመጨነቅ ለሦስት ቀናት ያህል ሲፈልጉት ከቆዩ በኋላ በቤተመቅደስ ውስጥ በመምሕራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸው እና ጥያቄን ሲያቀርብላቸው ባገኙት ጊዜ ተገረሙ። እናቱ ማርያምም ልጄ ሆይ፣ ለምን እንዲህ አደረግህን? አባትህና እኔ ተጨንቀን ስንፈልግህ ነበር አለችው።

በዚህ የወንጌል ክፍል በተገለጸውና ይህን ቤተሰብ ባጋጠመው ሁለት ክስተቶች፣ እነዚህም የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ማርያምና የቅዱስ ዮሴፍ መገረም እና መጨነቅ ላይ ማስተነተን እንደሚገባ ማሳሰብ እወዳለሁ።

የናዝሬት ከተማ ነዋሪ በሆነው በዚህ ቤተሰብ ማለትም በቅድስት ድንግል ማርያም፣ በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስና በቅዱስ ዮሴፍ ሕይወት መካከል የልጃቸው መሰወር እና አልፎ ተርፎም በመምህራን መካከል ተቀምጦ በመወያየት ላይ እያለ ሲያገኙት የተሰማቸው ዓይነት ግርምት ከዚህ በፊት ፈጽሞ አላጋጠማቸውም ነበር። ይህ መገረም የታየው በኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ኢየሱስን ሲሰሙት የነበሩ መምህራን ሁሉ በማስተዋል ችሎታው በጥበቡና በመልሱ ይደነቁ ነበር። ለመሆኑ አድናቆት መስጠት ማለት ምን ማለት ነው? አድናቆትንስ እንድንሰጥ የሚያደርገን ምንድነው?  አንድን ነገር ማድነቅና በአንድ ነገር ላይ መገረም ማለት፣ ለምናየው ወይም ለምንሰማው ነገር ትልቅ ዋስን በመስጠት፣ የራሳችንን የተሳሳተ ግምት ወይም የምንሰጠውን ዝቅተኛ ትርጉም ማስወገድ ማለት ነው። እንደመሰለው የራሱን መንገድ በመከተል ብቻ ትርጉም ወይም የተሳሳተ ተርጉም የሚሰጥ ሰው የአድናቆትና  የግርምትን ትክክለኛ ትርጉም ሊያውቅ አይችልም። አድናቆትን መስጠት ማለት ሌሎች ሰዎች የሚፈጽሙትን ተግባር ለመመልከት ወይም ለማጤን ራስን ሙሉ በሙሉ ክፍት ማድረግ ማለት ነው። ይህ ደግሞ በሰዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ወይም ለማሳደግ እጅግ አስፈላጊ ነው። በተለይም ደግሞ የቤተሰብን ይሕወት የወሰድን እንደሆነ በቤተሰብ መካከል የሚከሰቱትን ቅራኔዎች ወይም አለመስማማቶችን ለማስወገድ እጅግ ጠቃሚ መንገድ ነው። በቤተሰብ መካከል ችግሮች ሲከሰቱ ልባችንን በማደንደን፣ ትክክለኛው እኔ ብቻ ነኝ ማለትን በማስወገድ የሌላውንም ሰው መልካም ጎኑን ማስታወስ ወይም ባሰብ ያስፈልጋል። ለመልካም ጎኑ፣ ለመልካም ሥራው፣ ለመልካም አስተሳሰቡ፣ ለመልካም ባሕሪው አድናቆትን መስጠት ይስፈልጋል። ይህን የመሰለ አካሄድ በቤተሰብ መካከል ፍቅርን በመጨመር አንድነታቸውንም ይሳድጋል። በቤተሰቦቻችሁም መካከል ችግር ወይም ቅራኔ ቢከሰት ያ የቤተሰብ ወገን የሚያበረክተውን መልካም ተግባር ወይም መልካም ጎኑን በማስታወስ ለመልካም ተግባሩ አድናቆትን ማሳየት ያስፈልጋል። ይህም በቤተሰብ መካከል የተፈጠረውን ቁስል ለመጠገን፣ ቅራኔንም ለማስወገድ ያግዛል።

በሉቃስ ወንጌል በምዕ. 2 ላይ የተጠቀሰው ሌላው በልጃቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ከመካከላቸው መጥፋት ምክንያት በማርያምና በዮሴፍ ላይ የደረሰው ድንጋጤ ያስከተለው ጭንቀት ነው። ይህ በማርያምና በዮሴፍ መካከል የተፈጠረው ከባድ ጭንቀት ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቅዱስ ቤተሰብ መካከል ትልቅ ስፍራ እንዳለው ያስገነዝባል። ድንግል ማርያምና ዮሴፍም በሕብረት ሆነው ልጃቸው በጥበብና በማስተዋል፣ በመልካም ሁኔታ እንዲያድግ የበኩላቸውን ጥረት ያደርጉ ነበር። ልጃቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ እድሜውም እየጨመረ በሄደ ቁጥር በጥበብና በጸጋ ስጦታዎች እየተሞላ ማደጉን ይመለከቱ ነበር። ይህንን በልባቸው ውስጥ በመያዝ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸው ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጣ። የናዝሬቱ ቤተሰብም ቅዱስ የተባለበት ምክንያትም ይህ ነው። ሕይወታቸውን ለኢየሱስ ፍቅር ስላዋሉትና ሙሉ ትኩረታቸውን በኢየሱስ ላይ በማድረጋቸው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከመካከላቸው ጠፍቶባቸው  ያሳለፏቸው ሦስቱ አስጨናቂ ቀናት፣ እኛም ከኢየሱስ ክርስቶስ ተለይተን እንደምናሳልፋቸው፣ ከእርሱ ተለይተን እንደምንቆይባቸው ቀናት ማሰብ ይኖርብናል። ለሦስት ቀናት ያህል ኢየሱስ ክርስቶስን ዘንግተን ብቻችን መቆየት፣ ወደ እርሱ ጸሎት ሳናደርስ መዋል፣ ቅዱሳት መጽሕፍትን ሳናነብ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ጥበቃና ወዳጅነት ሲቀርብን የሚያጋጥመን ጭንቀት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ብዙን ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስን በልቤ ሳላስብ ቀናት ያልፋሉ። ይህ ደግሞ መልካም አይደለም። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ጭንቀት ሊሰማን ይገባል።  ለሦስት ቀናት ያህል ሲፈልጉት ከቆዩ በኋላ ልጃቸው በቤተመቅደስ ውስጥ በመምሕራን መካከል ተቀምጦ ሲያዳምጣቸውና ጥያቄ ሲያቀርብላቸው፣ ሲያስተምራቸውም እንዳገኙት ሁሉ እኛም በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ሆነን መለኮታዊው አምላካችንን ማግኘት፣ የእርሱን የድነት ቃልን ማዳመጥ ይኖርብናል። በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎታችን በኩል ኢየሱስ ክርስቶስን በአካል እናገኘዋለን። በዚህም ወቅት እርሱ በቃሉን በኩል ይናገረናል። ለመንገዳችንም ብርሃን ይሆነናል። በምስጢራቱ አማካይነት ቅዱስ ስጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል በየቀኑ ይሚያጋጥሙንን ፈተናዎችንና እንቅፋቶችን እንድናልፍ ሃይል ይሆነናል።

ዛሬ እነዚህን ሁለቱን ቃላት ማለትም መገረምንና ጭንቀትን ይዘን ወደየመጣንበት እንመለስ። በተጨማሪም በቤተስብ መካከል ሌሎቹ ሰዎች የሚያከናውኑትን መልካም ተግባር ስመለከት በእውነት በመገረም ለእነርሱ ያለኝን አድናቆት አሳያቸዋልሁ? ይህን በማድረግ በቤተሰብ መካከል የሚፈጠሩትን ችግሮች ለማቃለል እሞክራለሁ? ከኢየሱስ ክርስቶስ በርቅሁ ጊዜስ ጭንቀት ይሰማኛል ወይ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል። ለዓለም ቤተሰብ በሙሉ፣ በተለይም በተለያዩ ምክንያቶች ፍቅርንና ሰላምን ላጡት በሙሉ እንጸልይ። ለእነዚህ ቤተሰቦች የናዝሬቱ ቅዱስ ቤተሰብ ጥበቃ እንዳይለያቸው ጸሎታችንን እናቅርብ”።

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በታኅሳስ 21/2011 ዓ.ም የቅድስት ቤተሰብ (ኢየሱስ፣ማርያም እና ዮሴፍ) ዓመታዊ በዓል በተከበረበት ወቅት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኝዎች ካሰሙት ስብከት የተወሰደ።

09 February 2019, 09:45