ፈልግ

የገብርኤል ብሥራት ጸሎት ታሪካዊ አመጣጥ የገብርኤል ብሥራት ጸሎት ታሪካዊ አመጣጥ 

የገብርኤል ብሥራት ጸሎት ታሪካዊ አመጣጥ

የገብርኤል ብሥራት ጸሎት ታሪካዊ አመጣጡ ጥንታዊ የሆነ ይዘት ያለው ጸሎት ሲሆን “በመጀመሪያው ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ » (ዮሐንስ 1፡1) እንደ ሚለው ይህ ቃል የነበረው “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተጸንሶ ከድንግል ማርያም ተወለደ” የእግዚኣብሄር ልጅ ሰው ሆነ በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ ጸሎት ነው። በተለይም ደግሞ በሉቃስ ወንጌል 1፡29- እንደ ተጠቀሰው መልኣኩ ገብርኤል ማርያምን “ደስ ይበልሽ ጸጋ የተሞላብሽ ሆይ፣ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ […] ማርያም ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ።  እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፥ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” (ሉቃስ 1፡28-31) ብሎ በተናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ መሰረቱን ያደርገ ጸሎት ነው።

የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ-ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በኒቅያ ጸሎተ ሃይማኖት ውስጥ “ለእኛ ለሰዎችና ለመዳናችን ከሰማይ ወረደ፣ በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ከድንግል ማርያም በሥጋ ተወለደ፣ሰው ሆነ” በማለትም እምነታችንን እንገልጻለን። “ከሚወደን እና አንድ ልጁን ለኃጢኣታችን ማስተሰሪያ ከላከልን” ከእግዚኣብሔር ጋር ሊያስታርቀንና ሊያድነን ቃል ሥጋ ሆነ። “አብ የዓለም አዳኝ አድርጎ ወልድን ልኳል […] የተገለጠውም የሰዎችን ኃጢኣት ለመደምሰስ ነበር” (1ዮሐንስ 4፡10)።

የኒስያው ቅዱስ ግሪጎሪዮስ ይህንን በተመለከተ እንዲህ ይል ነበር . . .

ባሕሪያችን መፈወስን፣ ወድቋልና መነሳትን፣ ሞቱዋልና ትንሳኤን ጠየቀ። መልካሙን ሁሉ አተናልና፣ ለእኛ ተመልሶ መሰጠቱ ግድ ሆነ። በጨለማ ነበርንና እርዳታ፣ ባሮች ነበርንና ነጻ አውጪ እንሻ ነበር። እነዚህ ነገሮች ኢምንት ወይም ከቁጥር የማይገቡ ነገሮች ናቸውን? የሰው ዘር እንዲህ ባለ አስከፊና አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ስለነበር እነዚህ ነገሮች እግዚኣብሔርን አራርተው ሰብዓዊ ባሕርይ እንዲላበስና ወርዶ እንዲጎበኘው አላደረጉትምን?

የእግዚኣብሔርን ፍቅር እንዲህ እናውቅ ዘንድ ቃል ሥጋ ሆነ። “በልጁ አማካይነት ሕይወት እንድናገኝ እግዚእብሔር አንዲያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል፣ በዚህም የእግዚኣብሔር ፍቅር ምን ያህል እንደ ሆነ ለእኛ ተገልጹዋል” (1ዮሐንስ 4፡9) በማለት እግዚኣብሔር ለእኛ ያለውን ከፍተኛ ፍቅር ይገልጻል። “እግዚኣብሔር ዓለምን እጅግ ስለወደደ አንዲያ ልጁን ሰጠን፣ ስለዚህ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወት ይኖረዋል እንጂ አይጠፋም” (ዮሐንስ 3፡16) በማለት ምንም እንኳን እግዚኣብሔር እኛን ቢወደንም እኛ ደግሞ ለእዚህ የእግዚኣብሔር ፍቅር በእምነት ምላሽ መስጠት ይኖርብናል ማለት ነው።

ስለዚህ በእግዚኣብሔር ልጅ ሰው መሆኑን ማመን የክርስትና ሕይወት ልዩ ምልክት ነው። “የእግዚኣብሔርን መንፈስ ለይታችሁ የምታውቁት በዚሁ ነው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ መሥጋ መገለጡን የሚመሰክር መንፈስ ሁሉ የእግዚኣብሔር መንፈስ ነው” (1ዮሐንስ 4፡2) በማለት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ “ትልቁ የሃማኖት ምስጢር” የሆነውን “እርሱ በሥጋ ተገለጠ” የሚለውን ዝማሬ የምታሰማው የቤተ ክርስቲያን አስደሳች እምነት እንዲህ ያለው ነው።

እንግዲህ ከላይ ለመጠቅስ እንደ ተሞከረው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት በዚህ ከላይ በተጠቀሱት ጭብቶች ዙሪያ ላይ የሚያጠነጥን ጸሎት ነው።

የገብርኤል ብሥራት ጸሎት ጥንታዊ መሠርት ያለውና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን በማስታወስ በቀን ሦስት ጊዜ ማለትም በንጋት (በአስራሁለት ሰዓት) በቀትር (በስድስት ሰዓት) እንዲሁም በማታ (በአስራ ሁለት ሰዓት) የሚደገም የጸሎት ዓይነት ሲሆን ጸሎቱ በሚደገምበት ሰዓት ቤተ ክርስቲያንም የመልኣከ እግዚኣብሔርን ደወል በዚሁ ሰዓት ትደውላለች። ይህ ጸሎት “የመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት” የሚለውን ስያሜ ያገኝው በጸሎቱ የመጀመሪያ ስንኝ ላይ “የእግዚኣብሔር መልኣከ ማርያምን አበሠራት” ተብሎ ከተገለጸው ስንኝ የተወሰደ ሲሆን ጸሎቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰው መሆኑን የሚናገር ጸሎት ነው። ጸሎቱ በሦስት የተከፈሉ አጫጭር ስንኞች ሲኖሩት በእነኚህ በሦስት አጫጭር ስንኞች መካከል “ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ” የሚለው የማርያም ጸሎት ይደገማል። ይህ ጸሎት በሰንበትና በባዓላት ዕለት ልክ በእኩለ ቀን ላይ በዕለቱ ወንጌል ላይ ትንሽ አስተምሮና ገለፃ ከሰጡ በኋላ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ጴጥሮስ ኣደባባይ ላይ ይህንን ጸሎት ይመራሉ። በመቀጠልም በአደባባዩ ላይ የተገኝው ከተለያየ ቦታ ለንግደት የመጣውን ሕዝብ ሰላምታ ይሰጣሉ። በየትኛውም ጊዜ ከበዓለ ፋሲካ እስከ በዓለ ጰራቅሊጦስ በመልኣከ እግዚኣብሔር ጸሎት ፈንታ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤን የሚዘክረው “የሰማይ ንግሥት ሆይ ደስ ይበልሽ” የሚለው ጸሎት የሚደገም ሲሆን በመሓል በመሓሉ “ጸጋን የተሞላሽ ማርያም ሆይ” የሚለው ጸሎት ይታከልበታል።

 

የገብርኤል ብሥራት ጸሎት

የእግዚኣብሔር መልአክ ማርያምን አበሰራት

እርሷም በመንፈስ ቅዱስ ጸነስች

ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ……

እነሆኝ የእግዚኣብሔር አገልጋይ

እንዳልከኝ ይሁንልኝ

ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ……

ቃል ሥጋ ሆነ

በኛም አደረ

ጸጋ የሞላሽ ማርያም ሆይ…….

ቅድስት የአምላክ እናት ሆይ ለምኝልን

ክርስቶስ ለሰጠን ተስፋ የተገባን እንድንሆን

 

እንጸልይ

እግዚኣብሔር ሆይ በመላኩ ምሥራች የልጅህን የእየሱስ ክርስቶስን ሰው መሆን እንዳወቅን በሕማሙና በመስቀሉ ወደ ትንሣኤ ክብር እንድንደርስ ጸጋህን ስጠን ብለን በጌታችን እየሱስ ክርስቶስ እንለምንሃለን።

አሜን !

07 February 2019, 14:26