ፈልግ

የጅማ-ቦንጋ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረ መድሕን የጅማ-ቦንጋ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረ መድሕን  

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ሙሉ እውቅናን ማግኘቷ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ለምስራቅ አፍሪቃ ብጹዓን ጳጳሳት እና ስብሰባውን ለተካፈሉት ሌሎች የውጭ አገር እንግዶች በሙሉ ያደረገው ደማቅ አቀባበል፣ በቤተ መንግሥት ውስጥም ያዘጋጀው የእራት ግብዣ፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በምስራቅ አፍሪቃ አገሮች፣ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ለምታበረክተው መንፈሳዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎቶች ያለውን አድናቆት ከምስጋና ጋር የገለጸበት ነው ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች ስብሰብን ለመካፈል በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ላይ የተገኙት የጅማ ቦንጋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረ መድሕን ለጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ድረ ገጽ የዜና አውታር እንዳስታወቁት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሙሉ የመግሥትን ዕውቅና ለማግኘት መብቃቷን ገልጸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋርም ያላት ግንኙነት ማደጉን አስረድተዋል። ከዚህ በፊት ከውጭ አገር ለሚመጡት የወንጌል መልዕክተኞች ወይም ሚሲዮናዊያን ይሰጥ የነበረ የአንድ ዓመት የአገልግሎት ፈቃድ አሁን በየአምስት ዓመት እንዲታደስ መደረጉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላት ግንኙነት ማደጉን እንደሚያመልከት የጅማ ቦንጋ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረ መድሕን አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጥ የወንጌል ስርጭት አገልግሎት እያበረከቱ ለረጅም ዓመታት የኖሩ የውጭ አገር ሚሲዮናዊያን ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ እንደሚሰጣቸው ገልጸው ነገር ግን ይህ ማለት የዜግነት መብትን ያገኛሉ ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረ መድሕን በማከልም ያለፈው ዓመት ዘጠኙ የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ላይ ከሐምሌ 6 እስከ ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ. ም. ድረስ ያካሄዱት ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በምዕመናኖቿ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ ያላትን እውቅና ከፍ እንዳደረገው፣ አንድነቷን በመጠበቅ፣ በራስ የምትተማመን ቤተክርስቲያን እንዳደረጋት ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረ መድሕን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ባሁኑ ጊዜ የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች ያስተላለፉትን ውሳኔዎች ተግባራዊ ለማድረግ በመሥራት ላይ እንደምትገኝ ገልጸው ይህም ምእመናኖቿን በተለይም ወጣቶችን በእምነታቸው ብርታትን እንዲጨምሩ አድርጓቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ካቶሊካዊ ምእመናን የገንዘብ አቅማቸውን በማስተባበር፣ የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮችን ስብሰባ ለማስተናገድ ያደረገው ተሳትፎ የሚያስመሰግን እንደነበር የገለጹት ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረ መድሕን፣ ይህ ብቻም ሳይሆን በርካታ ምእመናን ከየሀገረ ስብከቶቻቸው ተነስተው ስብሰባው ወደሚካሄድበት አዲስ አበባ መምጣታቸው የስብሰባውን ልዩ ትዝታ ፈጥሯል ብለው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው ታላቁ የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች መደበኛ ስብሰባ ለኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክስቲያን ትልቅ ዕድል እና እሴት መሆኑን ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረ መድሕን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ሪፓብሊክ መንግሥት ለምስራቅ አፍሪቃ ብጹዓን ጳጳሳት እና ስብሰባውን ለተካፈሉት ሌሎች የውጭ አገር እንግዶች በሙሉ ያደረገው ደማቅ አቀባበል፣ በቤተ መንግሥት ውስጥም ያዘጋጀው የእራት ግብዣ፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በምስራቅ አፍሪቃ አገሮች፣ በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ ለምታበረክተው መንፈሳዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎቶች ያለውን አድናቆት ከምስጋና ጋር የገለጸበት ነው ብለዋል።

የጅማ ቦንጋ ሀገረስ ብከት ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ገብረ መድሕን ለምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች ዋና ጽሕፈት ቤት እንደገለጹት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ዝቅተኛ የምዕመናን ቁጥር ቢኖራትም የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አካል መሆኗን ገልጸው፣ ቤተክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እያበረከተች ያለችው፣ ጥራትን የጠበቀ ከፍተኛ የትምሕርት፣ የጤና እና የማሕበራዊ አገልግሎት አቅርቦት፣ አገልግሎቷን በማግኘት ላይ በሚገኘ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ አድናቆትን፣ ክብርን እና ምስጋናን አስገኝቶላታል ብለዋል። ባለፈው ዓመት ከሐምሌ 6 እስከ ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ. ም. ድረስ በአዲስ አበባ የተካሄደው የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች ስብሰባ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ የወንጌል ስርጭት አገልግሎቷን፣ እምነቷን የምትገልጽበት ስርዓተ አምልኮዋንም ጭምር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ አድርጓል ብለዋል።

የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አገሮች ዘጠኝ ሲሆኑ እነርሱም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ማላዊ ሲሆኑ ተባባሪ አባል አገሮችም ጂቡቲ እና ሶማሊያ መሆናቸው ይታወቃል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 February 2019, 16:12