ፈልግ

በናይጄሪያ የአቡጃ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦ. ኦናየካን፣ በናይጄሪያ የአቡጃ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦ. ኦናየካን፣  

ካርዲናል ኦናየካን በናይጄሪያ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንዲዘገይ መደረጉ መልካም አለመሆኑ ገለጹ።

ከምርጫ ኮሚሽኑ በኩል የሚወጡ እና ምርጫው ስለመራዘሙ የሚገልጹ ምክንያቶች ግልጽ እና አሳማኝ እንዳልሆኑ ካርዲናል ኦናየካን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በናይጄሪያ የአቡጃ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ጆን ኦ. ኦናየካን፣ በናይጄሪያ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ፕሬዚደንታዊ እና የፓርላማ ተውካዮች ምርጫ ለአንድ ሳምንት እንዲዘገይ መደረጉ መልካም ዜና እንዳልሆነ ተናግረዋል።

 የናይጄሪያ ምርጫ ኮሚሽን፣ ያለፈው ቅዳሜ በአገሪቱ ሊካሄድ የነበረውን ፕሬዚደንታዊ እና የፓርላማ ተወካዮች ምርጫ፣ አምስት ሰዓት ሲቀረው ወደ ቅዳሜ የካቲት 16 ንቀን 2011 ዓ. ም. ማራዘሙ ታውቋል። ምርጫ ኮሚሽኑ ዕለቱን ያራዘመበት ምክንያት፣ ለምርጫ ድምጽ መስጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች በሃገሪቱ በሚገኙ አንዳንድ የምርጫ ድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በጊዜ መድረስ ባለመቻላቸው ነው ብሏል።

በምርጫው የሚሳተፉ አስሩ ግንባር ቀደም ተወዳዳሪዎች የምርጫ ኮሚሽን ውሳኔን አውግዘው፣ አንዱ ሌላውን ተጠያቂ በማድረግ የአፍሪቃ ትልቋን የዲሞክራሲ አገር፣ የናይጄሪያ ሕዝብ እንዲረጋጋ ጥሪ አቅርበዋል።

በናይጀሪያ ለፕሬዚደት መሐመድ ቡሃሪ አስተዳደር ጠንካራ ትችቶችን በማቅረብ የሚታወቅ የአቲኩ አቡበከር ፓርቲ፣ የድምጽ መስጫ ቀን እንዲራዘም በምርጫ ኮሚሽኑ የተወሰደው እርምጃ ሆን ተብሎ የተደረገ እና በቁጥር አነስተኛ የሆነ ድምጽ ሰጭ እንዲወጣ ለማድረግ ታስቦ የተደረገ ዘዴ ነው ብሏል። ፕሬዚደንት መሐመድ ቡሃሪ በበኩላቸው አስተዳደራቸው በምርጫ ኮሚሽኑ ውሳኔ ጣልቃ እንደማይገባ ገልጸው፣ በናይጀሪያ የዲሞክራሲ ሥርዓት በማደግ ላይ እንዳለ በማስረዳት ሕዝቡ እንዲረጋጋ አሳስበዋል።

በናይጄሪያ የአቡጃ ከተማ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ኦናየካን፣ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፣ የናይጄሪያ ምርጫ ኮሚሽን ውሳኔ እራሳቸውንም ሆነ የናይጄሪያን ሕዝብ እጅጉን እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። ከምርጫ ኮሚሽኑ በኩል የሚወጡ እና ምርጫው ስለመራዘሙ የሚገልጹ ምክንያቶች ግልጽ እና አሳማኝ እንዳልሆኑ ካርዲናል ኦናየካን ገልጸዋል። የምርጫ ኮሚሽኑን ውሳኔ ለመስማት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙት እና ድምጻቸውን ለመስጠት ብለው ሩቅ መንገድን የተጓዙት በርካታ ሰዎች በሁኔታው በጣም መቆጣታቸውን ካርዲናል ኦናየካን ገልጸዋል።

ለናይጄሪያ መጥፎ ዜና ነው፣ 

ለምርጫ ድምጽ መስጫ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች በጊዜ በሃገሪቱ በሚገኙ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች አለመድረሳቸውን እና በአገሪቱ ውስጥ በተለይም በሰሜናዊ ግዛቶች በቦኮ ሃራም በኩል የሚሰነዘሩ ጥቃቶች የጸጥታውን ሁኔታ አደጋ ላይ እንደጣለው ብጹዕ ካርዲናል ኦናየካን ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ኦናየካን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት የሰጡትን ገለጻ በመቀጠል የጸጥታ ችግር መኖሩን የናይጄሪያ መንግሥት ከአራት አመት ጀምሮ እንደሚያውቀው፣ በእነዚህ ዓመታት ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና ማስተካከል ይቻል እንደነበር ገልጸዋል። የምርጫ ኮሚሽኑ፣ በናይጄሪያ ሊደረግ የታቀደውን ፕሬዚደንታዊ እና የፓርላማ ተወካዮች ምርጫ ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን   ለዓለም አቀፉ የምርጫ ታዛቢ ቡድን፣ በጋዜጣዊ መግለጫ በኩል ማረጋገጡን ብጹዕ ካርዲናል ኦናየካን ገልጸው የተከሰተው ገጠመኝ ለናይጄሪያ ሕዝብ መልካም ዜና ሊሆን አይችልም ብለዋል።

በናይጄሪያ የሰው ሕይወት መጥፋት እንግዳ ነገር አይደለም፣

ዝርዝር መረጃዎች እስካሁን ባይገኙም በናይጄሪያ ውስጥ በካዱና ግዛት ያለፈው አርብ 66 ሰዎች መገደላቸውን ዜናዎች ያመለክታሉ ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ኦናየካን፣ የናይጄሪያ ትልቁ ችግር በናይጄሪያ የሰው ሕይወት መጥፋት የተለመደ እንጂ እንግዳ ነገር አለመሆኑ ነው ብለዋል። ለዚህም ማረጋገጫ የናይጄሪያ መንግሥት ራሱ በዜናው አለመደንገጡ፣ ነገር ግን ጥቃቱን ያደረሱት ወደ ፊት ይፋ ይሆናሉ ብቻ ማለቱን ብጹዕ ካርዲናል ኦናየካን ተናግረዋል።

ባለፉት ሦስት እና አራት አመታት ውስጥ በናይጄሪያ የካዱና ግዛት በርካታ ችግሮች የተከሰቱበት መሆኑን ገልጸው የችግሮቹ ምክንያት በክርስትና እና በእስልምና እምነቶች መካከል በሚታዩት ውጥረቶች አለመሆኑንም አስረድተዋል። ምንም እንኳን በግዛቱ ነዋሪዎች መካከል ክርስቲያኖች ቢገኙም አብዛኛው የእስልምና እምነት ተከታዮች የሆኑት የሃውሳ ፉላኒ ጎሳዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። በናይጄሪያ ውስጥ ትልቁ ችግር በክርስቲያን እና በምስሊም ማሕበረሰብ መካከል አለመግባባት ቢፈጠር የተፈጠረው ችግር ሃይማኖታዊ ችግር እንደሆነ መወሰዱ ነው ብለው በሁለቱ የእምነት ተከታዮች መካከል የሚፈጠሩ ችግሮች ሃይማኖርታዊ ሳይሆኑ ማሕበራዊ እና የጎሳ ግጭቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
18 February 2019, 15:17