ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ወደ ኢየሩሳሌም ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ወደ ኢየሩሳሌም ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ጊዜ 

ቅዱሳንና ብጹዓን ከእግዚአብሔር የተሰጡን የፍቅር ስጦታ መሆናቸውን ቤተክርስቲያን አስገነዘበች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ቅድስናቸውንና ብጽዕናቸውን ለዓለም ምዕምናን ይፋ ያደረገችላቸው የቤተክርስቲያን ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጡን የፍቅር ስጦታ መሆናቸውን ቤተክርስቲያን አስገነዘበች። ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. ቤተክርስቲያንን አገልግለው ላረፉት 19 የቤተክርስቲያን ልጆች ብጽዕናን፣ ለ7ቱ ደግሞ የቅድስናን ማዕረግ መስጠቷ ታውቋል። እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያኑ ባቀረበው የፍቅር ስጦታዎች መካከል አንድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናትና ደናግል፣ ምዕመናንም የሚገኙበት ሲሆን ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደስ ይበላችሁ፣ ሐሴትንም አድርጉ በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፣ ሁላችንም ለቅድስና መጠራታችንን ያረጋግጣል። ቅዱስነታቸው በዚህ ቃለ ምዕዳናቸው እንደገለጹት፣

ልጆቻቸውን በታላቅ ፍቅር በሚያሳድጉት ቤተስብ መካከል፣ በሥራ በሚደክሙ ወንዶችና ሴቶች መካከል፣ በታማሚዎች መካከል፣ የዕድሜ ባለጸጋ በሆኑት ደናግል ላይ በሚታይ የደስታ ምልክት፣ በሁሉም የእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ቅድስናን መመልከት ደስታን ይሰጠኛል። ይህም በየቀኑ በማደርገው ጉዞ  የቤተክርስቲያንን ቅድስና እመለከታለሁ። በተጨማሪም ቅድስናን የምንመለከተው ወደ ሩቅ ሄደን ሳይሆን እግዚአብሔር በመካከላችን እንደሚገኝ በሚመሰክሩና በአካባቢያችን በምናገኛቸው ሰዎች አማካይነት ነው”

ማለታቸው ይታወሳል። በመሆኑም የእነዚህን መልካም ሰዎች ፈለግ በመከተል፣ ለስጦታዎቹ በሙሉ እግዚአብሔርንም እያመሰገንን፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በማስታወስ በአዲሱ ዓመት በሕብረት መጓዝ ያስፈልጋል

የጦር ሜዳ ሰማዕት፣ ከጥላቻ መካከል ፍቅር ሲገኝ፣

“ቅዱስ እስጢፋኖስ የሰማዕትነትን መንገድ እንድንከተል የሚያግዘን መለኮታዊ ምሳሌ ነው። እንደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “የነፍሴን አደራ ተቀበላት” በማለት ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ፣ ለሚያሰቃዩትም “ጌታ ሆይ ይህን ሐጢአት አትቁጠርባቸው” (ሐዋ. 7.59) በማለት ምሕረትን የለመነ ቀዳሚ ሰማዕት ነው። የቅዱስ አስጢፋኖስ ጸሎት፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ “አባት ሆይ መንፈሴን በእጅህ እሰጣለሁ” (ሉቃ. 23.46) ብሎ በታላቅ ድምጽ ከጮሄው ጋር ተመሳሳይነት አለው። የኢየሱስ ክርስቶስን መንገድ የተከተለው የቅዱስ እስጢፋኖስ የመታመን ጸሎት፣ እግዚአብሔር የሚሰጠንን ማንኛውንም ዓይነት ሕይወት ከእጁ በእምነት እንድንቀበል ይጋብዘናል”

(ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅ. እስጢፋኖስ ቀዳሚ ሰማዕት ዓመታዊ ክብረ በዓል ዕለት ካሰሙት ንግግር የተወሰደ)።

የጎርጎሮስዊያኑ 2018 ዓ. ም. የተጀመረው በለፈው ዓመት ጥር 26 ቀን ይፋ በሆነው የተሬሲዮ ኦሊቨሊ የብጽዕና አዋጅ እንደነበር ይታወሳል። ተረሲዮ የተገደለው በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በናዚዎች እጅ በሄርስቡርግ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ እያለ ነበር። ይህ ሰው በወቅቱ በወገኖቹ መካከል ሆኖ መንፈሳዊ አገልግሎትን በማበርከት ላይ እያለ ነበር። በመንፈሳዊ አገልግሎቱ ጊዜ “ጌታ ሆይ ከዚህ ስቃይ ነጻ አውጣን” የሚል ጸሎት ጽፎ ኣንደነበር ይታወሳል። ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጽዕናቸው ከታወጀላቸው መካከል ሉቺያኖ ቦቶቫሶ ይገኛል። ይህ ብጹዕ ሰው በማዳጋስካር በተካሄደው አብዮት የተገደለ የፍራንችስካዊያን ሦስተኛ ማህበር አባል ነበር። ሉቺያኖ ቦቶቫሶ በወቅቱ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንን በማገልገል ላይ በነበሩት ፈረንሳዊ ሚሲዮናዊያን ከባድ ስቃይ ሲደርስባቸው ከመካከላቸው መለየት ባለመፈለጉ ለሞት ተዳረገ። የሃንጋሪ ካህን የነበሩ አባ ያኖስ ብረነርም ባለፈው ዓመት ብጽዕናቸው ከታወጀላቸው መካከል አንዱ ሲሆኑ ብጽዕናቸው ይፋ የሆነው በጎርጎሮሳዊያኑ ሚያዚያ 1 ቀን 2018 ዓ. ም. ነበር። የተገደሉትም ሐዋርያዊ አገልግሎት በሚያበረክቱበት አካባቢ በበሽታ ለሚሰቃይ ታማሚ ቅዱስ ቁርባንን ለመስጠት ጉዞ ላይ እያሉ በኮሚኒስቶች እጅ ነበር።

ቀጥሎም ባለፈው ጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. በህዳር 10 ቀን በስፔን፣ ባርሴሎና ከተማ ቴዎዶር ለተባለ እና ከእርሱም ጋር የቅዱስ ጴጥሮስ የካህናት ማሕበር አባላትንና በስፔን በተካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት የተሳተፉና ከምዕመናን ወገን የሆኑ የሠራዊት አባላትን ጨምሮ ለ15 ጓደኞቹ ብጽዕናቸው ይፋ መሆኑ ይታወሳል። ባለፈው የጎርጎራሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. ብጽዕናቸው ከታወጀላቸው መካከል የኦራን ጳጳስ የነበሩ ብጹዕ አቡነ ፔትሮ ካልቨሬ ከሌሎች 18 ጓደኞቻቸው ጋር በአልጀሪያ ውስጥ በእስላማዊ አክራሪዎች እጅ የተገደሉ እንደሆነ ይታወሳል። ለግድያ ያበቃቸውም የሚያገለግሉትን ሕዝብ ትተው ወደ መጡበት መመለስ ባለመፈለጋቸው እንደሆነ ይታወቃል።

ሚሲዮናዊያንም እንደ ሐዋርያት ወደ ዓለም ዳርቻ የተላኩ ናቸው።

ሚሲዮናዊያን ወይም የወንጌል ልኡካን በሕዝቦች መካከል፣ በተለያዩ ባሕሎች መካከል የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ለመስበክ፣ በዓለም ዳርቻዎች ሁሉ የቤተክርስቲያንን ምስጢራት ለማደል ተሰማርተው ይገኛሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም ዳርቻ የላካቸው ሐዋርያት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ዘወትር ከእነርሱ ጋር እንደሆነ በማመን በድፍረት እንደሄዱ ሁሉ ሚሲዮናዊያንም በሰዎች መካከል የሚታዩ የእምነት ልዩነቶችን ሳይቆጥሩ፣ የሚደርስባቸውን የጠላት ጥቃት በመቋቋም ለተመሳሳይ ዓላማ ወደ ዓለም ዳርቻዎች ተሰማርተው ይገኛሉ ”(ዓለም አቀፍ ሚሲዮናዊያን ቀን ግንቦት 20 2018ዓ. ም.)።

በጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጽዕናቸው ያወጀችላት ሚሲዮናዊ እህት ሌዎኔላ ስጎርባቲ ናት። እህት ሌዎኔላ፣ በሶማሊያ መዲና ሞቃድሾ ለበርካታ ዓመታት የኖሩ ብቸኛ ሚሲዮናዊ ነበረች። በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እያሉ በመሣሪያ ታጣቂዎች የተገደሉ ሲሆን እህት ሌዎኔላ በዕለቱ ለገዳዮቻቸው ምሕረትን ከእግዚአብሔር ዘንድ በመለምን ለሰማዕትነት በቅተዋል። በቦሊቪያ ለረጅም ዓመት የኖረች ሚሲዮናዊ እህት ሳንታ ናዛሪያ ኢኛሲያ ማርክ ሜሳ ስትሆን ሕይወቷን በሙሉ ለካሕናትና ለደናግል ሐዋርያዊ አገልግሎት ስኬታማነት በመጸለይ ተግታ የኖረች ነበረች። ህዳር 27 2018 ዓ. ም. ብጽዕናቸው የታወጀላቸው የላቲን አሜርካ ተወላጅ የሆኑት አባ ቱሊዮ ማሩዞ እና ለምዕመናን ትምህርተ ክርስቶስን በማተማር የተባበሩት ሉዊስ ኦብዱሊዮ ናቸው። የተገደሉትም አገራቸውን ከስፔን ቅኝ ግዛት ነጻ ለማውጣት በተነሳው አመጽ ምክንያት ነበር።

ለሕሙማን የሚደረግ የሕክምና አገልግሎት የእግዚአብሔር ርሕራሄ የሚገለጥበት ነው።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጎርጎሮሳዊያኑ 2017 ዓ. ም. በዓለም አቀፍ የሕሙማን ቀን ባስተላለፉት መልዕክታቸው ለታማሚ ቤተሰብ የሚደረግ የሕክምና አገልግሎት የእግዚአብሔር ርሕራሄ የሚገለጥበት አገልግሎት በመሆኑ በፖለቲካ ዘርፍም ቢሆን እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል። በፖላንድ አገር ከቤት ወደ ቤት እየተዘዋወረች የሕክምና አገልግሎት በማበርከት ላይ እያለች የተገደለችው የአና ክርዛቪኖስካ ብጽዕና የታወጀው ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ ዓመት እንደነበር ይታወሳል። በተመሳሳይ ዓመት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የብጽዕናን አዋጅ ይፋ ያደረገችላት ካርመን ረንዲለዝ ማርቲነዝ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ልጆች ደናግል ማሕበር መስራች ናት። ሳን ፍራንችስኮ ስፒነልሊ በእግዚአብሔር ምህረት የተነሳ ከነበረበት የጀርባ አከርካሪ አጥንት ሕመም ለብዙ ዓመታት ሲሰቃይ ቆይቶ ዕለት በዕለት በሚያቀርበው ጸሎት አማካይነት የተፈወሰና በኋላም ለብጽዕና የበቃ ሰው ነው።

ለንጽሕናቸው ሲሉ ደማቸውን ያፈሰሱ ሰማዕት፣

ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓመተ ምሕረት ብጽዕናቸው የታወጀላቸው የስሎቫኪያ ተወላጅ አና ኮለሳሮቫ መሆኗ ይታወሳል። ይህች ላጅገረድ የተገደለችው በቤተሰቦቿ ፊት ሊደፍራት በተነሳው በአንድ አንባ ገነናዊ መንግስት ሰራዊት እጅ እንደነበር ይታወሳል። ሌላዋ የሮማኒያ ዜጋ እህት ቨሮኒካ አንታል ስትሆን በተመሳሳይ መልኩ ሊደፍራት በተነሳ ግለሰብ የተገደለች ሲሆን በነበረችበት የደናግል ማሕበር ዝናን ያተረፈችና ባሁኑ ጊዜ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን እና በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የምትወደስ ብጽዕት ናት።

ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተገናኙ ካህናት፣

ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ 2018 ዓ. ም. ለቅድስና የበቁ የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ የነበሩ ብጹዕ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ ጳውሎስ ስድስተኛ ናቸው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ ጳውሎስ ስድስተኛ በጽንስ ደረጃ የሚገኝ የሰው ልጅ ሕይወት እንዳይገደል በማለት ጽኑ አቋማቸውን የገለጹና የተከላከሉ ነበሩ። የድሆች አባትና ሰላም ወዳድ የሆኑት የላቲን አሜርካ ተወላጅ፣ ሞንሲኞር ኦስካር አርኖልፍ ሮመሮ ጋልዳሜዝ ባለፈው የጎርጎሮሳዊያኑ ዓመት ለቅድስና የበቁ ናቸው። በዚሁ ዓመት ሌሎችም ሳን ቪንቼንዞ ሮማኖ፣ ዣን ባቲስት ፎክ፣ እና ቲቡርሲዮ አርናዝ ሙኞዝ ብጽዕናቸው በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የታወጀላቸው የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው።       

03 January 2019, 16:06