ፈልግ

የጥር 12/2011 ዓ.ም ዘጥምቀት-አስተርዮ 1ኛ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የጥር 12/2011 ዓ.ም ዘጥምቀት-አስተርዮ 1ኛ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የጥር 12/2011 ዓ.ም ዘጥምቀት-አስተርዮ 1ኛ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

"የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል።" ኢሳ. 6ዐ፡14

ኢየሱስ በቃና ዘገሊላ ሠርግ ግብዣ ላይ

በእለቱ የተነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት የተወሰዱት
1. ዕብራዊያን 2፡1-10
2. 1ዮሐ. 5፡1-12
3. ሐዋ. 10፡34-38
4. ዮሐ. 2፡1-12

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ክፍለ ሀገር በምትገኘው ቃና በሚባል ከተማ ሰርግ ነበረ፣ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች። ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ተጠርተው ነበር። በሰረጉ ግብዣ ላይ የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት ኢየሱስን “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው። ኢየሱስም አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ውሃ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው።
አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን ያቀርባል፣ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል” አለው። ኢየሱስ ይህን የተአምራት ሁሉ መጀመሪያ የሆነውን ተአምር በቃነ ዘገሊላ አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ። ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፥ በዚያም ጥቂት ቀን ኖሩ።

የእግዚኣብሔር ቃል አስተንትኖ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፍቃድ ያላችሁ ሕዝቦች ሁሉ እንደ መልካም ሥራችን ሳይሆን በምህረቱ ደግፎንና ጠብቆን ለዛሬው ቀን ያደረሰን እግዚአብሔር አምላካችን ቅዱስ ስሙ የተመሰገነ ይሁን።
በዛሬው እለተ ሰንበት ትኩረት የምናደርግባቸው የእግዚአብሔር ቃላት የተወሰዱት ወደ ዕብራዊያን የተላከ መልዕክት 2፡1-10፣ የሓዋሪያት ሥራ 10፡34-38 እና በመጨረሻም ከዩሓንስ ወንጌል 2፣1-13 ኢያሱስ በቃና ዘገሊላ ውሃን የወይን ጠጅ እንዳደረገ በሚያመልክተውን የእግዚአብሔር ቃል ዙሪያ ላይ ይሆናል።
የእግዚአብሔር ቃል ለኛ የሚነበበው፣ የሚሰበከው እና የምፀለየው የሕይወታችን መርህ እንዲሆን፣ አካሄዳችን ሁል ጊዜ በመልካም ጎዳና ልይ ብቻ እንዲሆን፣ እግዚአብሔር እንዲረዳን ሰዎች በመሆናችን ምክንያት ለተለያዩ ዓይነት ፈተናዎች የተጋለጥን በመሆናች የተነሳ ያለ እግዚአብሔር እርዳታ በራሳችን ችሎታ ላይ ብቻ ተመስርተን ሕይወታችንን መምራት ሰለሚያዳግተን ልክ ዳዊት (በመዝ.119፣105) “ ሕግህ ለእግሬ መብራት፥ ለመንገዴ ብርሃን ነው” እንዳለው፣ እኛም በተሰማራንበትን የሕይወት መንገድ እግዚአብሔር በብርሃኑ እየመራን እርሱ ወደ ሚፈልግበት ቦታ እንዲያደርሰን አስፈላጊ በመሆኑ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ቃል ሳንሰልች መስማት ብቻ ሳይሆን ማዳመጥ፣ ማሰላሰልና መፀለይ ለሕይወታችን በረከትን ስለሚያስገኝ ሳንታክት በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረት ሕይወት እንዲኖረን ይጋብዘናል።
ወደ ዛሬው የመጀመርያ ምንባብ ስንመልስ ወደ ዕብራዊያን የተላከ መልዕክተ እናገኛለን።
“ስለዚህ ከሰማነው ነገር ስተን እንዳንወድቅ፥ ለሰማነው ነግር አጥብቀን ልንጠነቀቅ ይገባናል” ይላል የመጀመሪያው ምንባብ። ይህ የሰማነው ነገር ምን ይሆን? ምን ይሆን አጥበቀን እንዲንይዝ የዚህ መጻሓፍ ጸሓፊ አደራ የሚለን? የምሉትን ጥያቀዎች መመለስ አግባብ የመስለኛል ወደ ሚቀጥለው ክፍል ከማለፋችን በፊት…
የሰማነው ነገር በዚሁ የመፃፍ ቅዱስ ክፍል (ዕብ. 1፣1-3) ላይ እንደተጠቀሰው “እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በተለያየ ጊዜና በልዩ ልዩ መንገድ በነቢያት በኩል ለአባቶቻችን ተናግሮ፥ በዚህ መጨረሻ ዘመን ደግሞ ወራሽ ባደርገውና ዓለምን በፈጠረበት በልጁ እኛን ተናገረን። እርሱ የእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅና የባሕሪዩ ተክክለኛ ምሳሌ ሆኖ፥ በኋያል ቃሉ ሁሉን ደግፎ ይዞአል፣ የኃጢኣት መንጻት ካስገኘ በኋላ በስማይ በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” ይለናል።
እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ ለአባቶቻችን ሲናገር ሰንብቱኣል…ነገር ግን በብዙ መልኩ የሰው ልጆች የእግዚአብሔርን ቃል ማደመጥና በእለታዊ ኑሮኣቸው ውስጥ አስገብተው መጓዝ ግን ስያዳግታቸው እንደነበረ አሁንም በኛ ዘመን የሚታይ ሀቅ ነው።
የእግዚአብሔርን ቃል በጥንቃቄ አለመያዝ ከፍተኛ ዋጋ እንድምያስከፍለን ነው ከዛሬ ምንባብ የምንረዳው። ይህ እግዚአብሔር የሰጠንና ጥንቃቄ እንድናደርግለት ያሳሰበን ቃል የቱ ነው? እግዚኣብሔር ከኦሪት ጀመሮ እንድንተዳደርበት የሰጠን ሕግ አንድ እና አንድ፣ በዘመን መለወጥ የማይሻር ዘፍጥረት (5፡ 1-21) ውስጥ የተጠቀሱት ዐሥርቱ ትዕዛዛት ሲሆን በአዲስ ኪዳን ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እዚህ ምድር መጥቶ ደሙን ጭምር በማፍሰስ የመሰከርልንና ዐሥርቱን ትዕዛዛት በፍቅር ላይ መሰረት በማደረግ ወደ ሁለት “አንተም በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹም አሳብህ ፣ በፍጹም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ” የምትለው እና ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚሉትን ከእነዚህ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም” (ማርቆስ 12፡30-31) በማለት ይገልጻል።
እንግዲህ እንድናከብረው እና እንድንተገብረው አደራ የተሰጠን የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። መሰረቱንም ያደረግው በፍቅር ላይ ነው። ይህንን ቃል በተግባር በመለውጥ እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ ክርስቶስ ፍቅር ምን መሆኑንም ጭምር በመስቀል ላይ እስከ መስቀል ድረስ ያደረስው ፍቅር መሆኑን በተግባር ስላሳየን ይህንን ምሳሌ ተቀብለን እኛም በእለታዊ ኑሮዋችን ልንተገብረው ያስፈልጋል።
እርስ በእርሳችን እንድንዋደድ የሚያደርገን ነገር ምንድነው? ብለን ራሳችንን ስንጠይቅ ተገቢው መልስ ሊሆነን የሚችለው ር.ሊ.ጳ ፍራንቸኮስ የተናገሩትን ቃል ማስታወስ ተገቢ ነው። “ቅናት እና ምቀኝነት የክርስቲያን ማህበረሰብ እና በአጠቃላይ በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የሚንፀባረቁ ክፉ ባህሪያት መሆናቸውን” ገልፀው “ቅናት እና ምቀኝነት እንደ አረም በውስጣችን የሚያድጉ ክፉ የኋጢኣት መንሰሄዎች ናቸው” ማለታቸው ይታወሳል።
መጻሓፈ ሳሙኤል (18.6-9፣19.1-7) ውስጥ እንደተጠቀሰው የእስራኤል ንጉስ የነበረው ንጉስ ሳኦል፣ ዳዊት ማንኛውንም ዓይነት ተልዕኮ በሚገባ የሚፈፅም መሆኑን በተረዳ ጊዜ የጦር ሰርዊቱ አዛዥ እንዲሆን እንደሾመው እና ዳዊትም በብዙ ሺ የሚቆጠር የፍለስጤማዊያንን ጦር በመደምሰሱ ሕዝቡ “ሳኦል ሺ ገደለ ዳዊት አስር ሺ ገደለ” ብለው በደስታ በዘመሩበት ወቅት በቅናት በዳዊት ላይ እንደተነሳ የሚያወሳ መሆኑን አውስተዋል።
ቅናት ምቀኝነትን መቀኝነት ደግሞ ፍቅርን ያጠፋል…
ስለዚህ የመጀመረያው ምንባብ እንደሚያሳስበን የእግዚአብሔርን ቃል ማክበር ማለት ሰዎችን እንደ እራሳችን መውደድ ማለት በመሆኑ በሕይወት ጉዞ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል።
ወደ ዛሬው ቅዱስ ወንጌል ስንመለስ ደግሞ የጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ ሠርግ ላይ ተገኝቶ ከቅድስት እናቱ ጋር የተወያየበትንና አማላጅነቷን ያሣየችበት አንዱ አንቀፅ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የአምላክ እናት የሆነችው /የፈጣሪ እናት/ ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር የሰጣትን የምልጃ ስራዋን ስታከናውን ትታያለች፡፡ እናታችን ከዚህም ከ2ዐዐዐ ሺህ ዓመት በኃላም እስከ ዛሬ ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ ክርስቲያኖች በፍፁም በጸሎት ትጋት ከጌታ ጋር እንዲታረቁ ከማድረጓም በላይ እንዲፈወሱና እንዲድኑ ታደርጋለች፡፡
እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዘመናችን ሁሉ ለተለያዩ ቅዱሳን በመገለጥ የተያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ ላይ ትገኛለች ከነዚህም ውስጥ በሚክሲኮ ገደሎፒ በደቡብ ምዕራብ ፈረንሳይ በሎርቶ፣ በሎሬቶ ጣሊያን፣ በፋጢማ ፖርቹጋል፣ በማድሪድ በመሳሰሉት እንዲሁም ሜጂጎሪ ተገልፃለች፡፡ ጸበል አፍልቃ ቤተክርስቲያን በዚህ ቦታ ስሪልኝ ያለቻትና እስካሁን ድረስ ንግደት የሚኬድበት ብዙ ሺህ በሽተኞች የሚፈወሱበት ቦታ ነው፡፡
"የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእግዚአብሔርም ከተማ፥ የእስራኤል ቅዱስ የሆንሽ ጽዮን ይሉሻል።" ኢሳ. 6ዐ፡14
 

19 January 2019, 17:07