ፈልግ

ካርዲናል ብርሃነየሱስ  ካርዲናል ብርሃነየሱስ  

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ለ2011 ዓ.ም. የገና በዓል ያስተላለፉት መልእክት

"በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን።” (ሉቃስ 2፡14)

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት በመላው ክርስቲያኖች ዘንድ የሚከበረውን የ2011 ዓ.ም. የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል በማስመልክት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
"በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን።” (ሉቃስ 2፡14)

ብፁዐን ጳጳሳት
ክቡራን ካህናት፤ ገዳማውያንና/ዊያት
ክቡራትና ክቡራን ምዕመናትና ምዕመናን
መላው ሕዝበ እግዚአብሔር
በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ
ከሁሉ አስቀድሜ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በራሴ ስም እንኳን ለ2011 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቴን አቀርብላችኃለሁ።
በእግዚአብሔር የምናምን የእርሱ ወዳጆችና ተከታዮቹ የሆንን ሁሉ ክርስቶስ በእግዚአብሔር እንደተወደደና እርሱ ልጁን እንደወደደና እኛም እንደምንወደው በየዕለቱ እየመሰከርንና እየኖርን በበለጠ በልደቱ ቀን ደግሞ በታላቅ መንፈሣዊ ደስታና ስሜት እናከብረዋለን። በዚህም ከሥጋችን ይልቅ ለነፍሳችን ጥቅም እንዲሆንልን እግዚአብሔር አባት ፈቅዶ አንድ ልጁን ለኛ ለሰዎች እንዲወለድል በማድረግ ሕይወቱን እንዲሰጠን አድርጎአል። ይህም ለኛ ለሰዎች የተሰጠን ታላቅ ስጦታ ነው።
“ኢየሱስ መሲህ መሆኑን የሚያምን ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ነው አባቱን የሚወድ ሁሉ ልጁንም ይወዳል” (1ዩሐ 5፡1)
ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሲስ ክርስቶስ ያምናል ማመን ብቻም ሳይሆን እርሱ የሚያስተምረውንና የሚፈልገውን መልካም ነገር ሁሉ ይፈጽማል። ፈቃዱንም ለእግዚአብሔር ያስገዛል። በእርሱም ይመላለሳል ሕይወቱንም ይመራል አላስፈላጊ ከሆኑ ነገሮችም ለመራቅ ይጣጣራል። ይህም ማለት ራሱን ለዓለም ነገሮች ብቻ ሳይሆን ዘለዓለማዊ ለሆኑ መንፈሣዊ ነገሮች ይሠራል።
እኛም ዘውትር አምላካችንን በመውደድ ወዳጆቻችንን እንድንወድና ማንኛውም የሰው ዘር የሆነውንና በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠረውን ሁሉ ልንወድና ልናፈቅር ይገባናል። ምክንያቱም ሰዎችን ሁሉ መውደድ እግዚአብሔርን መውደድ ማለት ነውና። ይህን ስንፈጽም እግዚአብሔር ይወደናል ከምድር ሃብትና ደስታ ይልቅ ልባችንን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ከፍተን በሰማይ ሐብት ላይ እናተኩር። ሁላችንም አምላካችን በፈቀደ ቀን ምድራዊ ነገሮችን ትተን መሰናበታችን ስለማይቀር የጌታን ልደት በጋለ መንፈስ ተቀብለን ስናከብር የእጁን ድንቅ ሥራ የሆኑቱን በመመልከት ለዚች ዕለት ያደረሰንን አምላካችንን ከልብ እናመስግነው።
ውድ ምዕመናን እንደሚታወቀው ሰላም ለመንፈሣዊም ሆነ ለሥጋዊ ሕይወት አኗኗራችን ዋንኛ ዋስትና መሆንዋ የታወቀ ነው። ይህም ከግለሰብ ፣ ከቤተሰብ ተነስቶ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ ከሰፈር እስከ ቀበሌና ክልሎች ድረስ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት አሁን እጅግ ከሚያስፈልጉን ነገሮች በበለጠ ሰላም እጅግ አንገብጋቢ ነገር እየሆነ መጥቶአል።
”ከክፉ ሽሽ፣ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን ውደዳት ተከተላትም።" (መዝ 33/34፡ 14)
ዛሬ በአንዳንድ ቦታ እንደሚታየው ክርስቶስ ለአገራችን የሰጣትን ሰላም ዘንግተው የጥልና የብጥብጥ አገር እንድትሆንና በተለያየ አጓጉል ምክንያቶች ሰላምን በማመንመን ህዝቦች እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ፣ ተስፋ እንዲቆርጡ ብሎም በዜጎች መብት ዘለው እየገቡ በመታየታቸው ክርስቲያኖች ይህንን ሊቃወሙትና ለሰላም ሊጸልዩ ይገባል ምክንያቱም ምንጊዜም ቢሆን ሰላም ከእግዚአብሔር ሲሆን እኛም ሰላምን ለማግኘት በፍቅር፣ በትዕግስት፣ በቁምነገረኝነት እርስ በርስ በመዋደድና በመከባበር ብሎም በመከባበር መንፈስ ስንመራ ነው። ስለሆነም ሰላማችንን ሳናሳድደው እንጠብቀው።
መንግስት በአሁኑ ጊዜ እያደረገ ያለውን የሰላም ሥራ የሁሉም መስተዳደሮች ዞኖችና ከተሞች ጭምር በሙሉ ቁርጠኝነት የህግ ልዑላዊነት ከማስከበር አንጻር አጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ እየጠየቅን መላው የአገራችን ሕዝቦችም የአገራችንን ዕድል ብሩህ አድርገን በማየት በህብረትና በአንድነት በመቆም ሁላችንም እንድንሠራ በቤተክርስቲያናችን ስም ማሳሰብ እንወዳለን።
ካቶሊካውያን ምዕመናን እንዲሁም ቤተሰቦች በእምነታችሁ በርትታችሁ ዘረኝነትን ተጠይፋችሁ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ስለሆናችሁ በአይሁዳዊና በግሪካዊ በአገልጋይና በጌታ በወንድና በሴት መካከል ምንም ልዩነት የለም" (ገላ 3፡28) የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት አንግባችሁ ያለልዩነት ሁሉንም የሰው ልጅ በፍቅር እንድታቅፉና የቅዱስ ፍራንሲስኮስን ጸሎት ቀንና ማታ እንድትጸልዩ እንጠይቃን፡፡ ካቶሊካውያን ቤተሰቦች በቤታችሁ ለልጆቻችሁ ዘረኝነትን ሳይሆን ፍቅርን፣ አንድነትንና መከባበርን አስተምሩ፡፡"
"እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና (ሉቃስ 2፡10-11)፡፡
ወጣቶች እምቅ ኃይል ያላቸው፣ ነገሮችን የመፍጠርም ሆነ የመለወጥ፣ እንዲሁም የማደስ፣ የሀገርም ተስፋ በመሆናቸው ብቃታቸውንና ችሎታቸውን ኃይላቸውንና ጥበባቸውን ተጠቅመው የሀገርን ልማት በጥልቀትና በስፋት የሚያሳድጉ የሕብረተሰብ ክፍል በመሆናቸው ይበልጥ ለሀገራቸው፣ ለወገናቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና እንዲሁም ለራሳቸው ትልቅ ሚና ስለሚኖራቸው ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ስጦታ እንዲያሳድጉ፣ እንዲያበለጽጉ እንዲሁም እንዲኖሩበት ልንረዳቸው ይገባል፡፡
ወጣቶች ትኩስ ኃይል ስለሆናችሁ በተለያየ ስሜት ውስጥ ልትነዱ አይገባም፡፡ የነገሮችን አመጣጥና ሁኔታ በሰከነና በተረጋጋ መንፈስ በማጤንና በማስተዋል ልትተረጉሙት ይገባል፡፡ እንዲሁም ከአሉታዊ የባሕል ወረርሽኝ ማለትም ከአደንዛዥ እጾች፣ ከልዩ ልዩ ሱሶችና አጉል ልማዶች ልትቆጠቡ ይገባል ምክንያቱም እነዚህ አጉል ልማዶች እራሳችሁንም ሆነ ሀገርን የሚጎዶ ስለሆኑ ከነዚህ አላስፈላጊ ድርጊቶች በመቆጠብ መልካም ዜጋ እንድትሆኑ አባታዊ ምክሬን እለግሳችኋሁ፡፡ እንድትመረቁ ወላጆቻችሁንና ሽማግሌዎችን አክብሩ፡፡
የተወደዳችሁ ምዕመናን በእግዚአብሔር ጸጋ ተሞልተን ይህን ክብረ በዓል ስናከብር ደሆችንና አቅመ ደካሞችን ህሙማንና ረዳት የሌላቸውን ሰዎች በማስታወስ እርሱ ከሰጠን በረከት በማካፈል በዓሉን የደስታና የፍሰሐ አድርጋችሁ እንድታከብሩት አደራ ማለት እወዳለሁ።
በመጨረሻም በየሆስፒታሉና በየቤቱ የምትገኙ ህሙማን፣ በሥራና በተለያዩ ምክንያቶች ከአገር ውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት አነዲሁም ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ የአገርን ድንበር ለማስከበር በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ሰላም ለማስፈን የተሰማራችሁ የአገር መከላከያ አባላት፣ በየማረሚያ ቤቶች የምትገኙ የህግ ታራሚዎች በሙሉ እንኳን ለ2011 ዓ.ም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት የደስታ መልዕክቴን አቀርብላችኃለሁ። በዓሉም የሰላምና የደስታ ይሁንልን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክልን ይጠብቅልን !!
† ካርዲናል ብርሃነየሱስ
ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት

 

08 January 2019, 08:32