ፈልግ

የፓናማው ፕሬዚደንት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለመቀበል መዘጋጀታቸውን ገለጹ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለም አቀፍ የወጣቶችን በዓል ለማክበር ወደ ፓናማ የሚመጡትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ለመቀበል አገራቸው ዝግጅቷን ማጠናቀቋን የፓናማው ፕሬዚደንት፣ ክቡር አቶ ዩዋን ካርሎስ ቫሬላ ሮድሪገስ ገልጸዋል። ፕሬዚደንት ካርሎስ ቫሬላ ሮድሪገስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል የሚከበርበትን አገር ፓናማ እንዲሆን በመምረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ምስጋናቸውንም አቅርበውላቸዋል። ከጥር 15 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ ፓናማ የመላው ዓለም ወጣቶች የሚገናኙበትና የርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ መልዕክትም ወደ መላው ዓለም የሚሰራጭበት ስፍራ ትሆናለች ብለዋል።

ከባለቤታቸው ከሎሬና ካስቲሎ ደ ቫሬላ እና ከልጆቻቸው ጋር ከዚህ በፊት በተደረገው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ የተገኙት ፕሬዚደንት ዩዋን ካርሎስ ቫሬላ ሮድሪገስ፣ በአገራቸው የሚደረገውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ዝግጅትን በቅርብ ሆነው ሲያስተባብሩ ሲያግዙ መቆየታቸው ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ተቀብሎ ማስተናገድ ለፓናማ ሕዝብ ከፍተኛ ደስታን የሚሰጥ እንደሆነ የገለጹት የፓናማው ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ዩዋን ካርሎስ ቫሬላ፣ በሥራ ታታሪ፣ በእምነቱ ጠንካራ፣ በተስፋ በተሞላ በፓናማ ሕዝብ ዘንድ በዓሉ እንዲከበር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያደረጉት ውስኔ ለፓናማ ሕዝብ ትልቅ ሃላፊነትና ኩራት እንደሆነ ገልጸዋል።

በአገራቸው የመጀመሪያ  የሆነው፣ ላ አንቲጓ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሃገረስብከት የተመሠረተበትን 500ኛ ዓመት ለማክበር ከ2001 ዓ. ም. ጀምሮ ዝግጅት ላይ የሚገኝ የፓናማ ሕዝብ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ጉብኝት ይመኝ እንደነበር ፕሬዚደንት ዩዋን ካርሎስ ገልጸዋል። ምኞቱ የሠመረ እንዲሆን ሕዝቡ ባደረገው ጥረት ዛሬ እነሆ ምኞታችን እውን ሆኗል ብለዋል።

ከላቲን አሜርካ የመጀመሪያ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሆኑትን ፍራንችስኮስን በተወለዱበት አህጉር ተቀብሎ ማስተናገድ፣ በሐዋርያዊ ግብኝታቸው ብቻ ሳይሆን በብዙ ሽህዎች የሚቆጠሩ የዓለም ወጣቶችን በፓናማ እንዲሰበሰቡ ማድረጋቸው ለፓናማ ሕዝብ መባረክ ነው ብለው፣ አገራቸው ፓናማ ለአገሮች እርቅና ሰላም፣ ባሕሎች እርስ በእርስ የሚገናኙበትን ድልድይ በመገባት የምትታወቅ አገር እንደሆነች የገለጹት ፕሬዚደንት ዩዋን ካርሎስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይዘው የሚመጡት መልዕክት ወደ መላው ዓለም የሚሰራጭበት አገር ትሆናለች ብለዋል።

ፓናማ ይህን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ለማዘጋጀት ሁለት ዓመት የፈጀባት መሆኑን የገለጹት ፕሬዚደንት ዩዋን ካርሎስ፣ የፓናማን ወጣቶች ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ የዓለም ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ሆነው፣ ለሰው ልጅ በሙሉ መልካም መኖሪያ የሚሆን ዓለምን ለመገንባት ያላቸውን ፍላጎት የሚጋሩበት አጋጣሚ ይሆናል ብለዋል። በተጨማሪም በዓላቸውን ለማክበር ወደ ፓናማ የሚመጡት ወጣቶች በሙሉ፣ ፓናማ ትንሽ ብትመስልም፣ ትልቅና እንድትወደድ የሚያደርጋት ብዙ ነገር ስላላት ለወጣቶች ለማበርከት የፓናማ ሕዝብ ዝግጁ ነው ብለዋል።  

22 January 2019, 16:09