ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ፣ ቅዱስ መስቀልን ለወጣቶች በአደራ ሰጥተው እንደነበር ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል እንዲከበር ሃሳባቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ፣ ወጣቶቹ በዓላቸውን ወደሚያከብሩበት አገር ይዘው የሚሄዱትን ቅዱስ መስቀል በአደራ ሰጥተው እንደነበር ታውቋል።

ቅዱስ መስቀል ለወጣቶች ተሰጥቷል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ በቅዱስ የምሕረት ዓመት ኢዮቤልዩ መዚጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ፣ ወጣቶች ለሰው ዘር በሙሉ የፍቅር ምልክት የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ወደ ዓለም በሙሉ በመውሰድ፣ ፍቅሩን፣ ሞቱንና ትንሳኤውን፣ እንዲሁም ድነት ማስገኘቱን መስክሩ በማለት፣ በጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 22 ቀን 1984 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተገኙት በርካታ ወጣቶች መናገራቸው ይታወሳል። ሦስት ነጥብ ስምንት ሜትር ርዝመት ያለው የእንጨት መስቀል በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከመንበረ ታቦቱ በስተ ግራ በኩል በመሆን ለአንድ ዓመት እንዲቆይ ማድረጋቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በወቅቱ ባሰሙት ንግግር ለወጣቶች ያስረከቡት ቅዱስ መስቀል፣ የወንጌል ምስክርነት የሚገለጥበት፣ የዓለም ወጣቶች ለመገናኘት ጥሩ አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሚሆን አስረድተዋል። የቅዱስ ዓመት መስቀል በመባልም የሚታወቀው ይህ የወጣቶች መስቀል በዓሉ ወደሚከበርበት አገር ከመወሰዱ አስቀድሞ በሮም ውስጥ በሚገኘውና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ለወጣቶች እንዲሆን ባሉት በቅዱስ ሎሬንሶ ማዕከል ውስጥ እንዲቆይ መደረጉም የሚታወስ ሲሆን ከሮም ተነስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ የተገኘውም በጀርመን መሆኑ ይታወሳል።

300 ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ፣ በጀርመን ከተካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል በኋላ ባሰሙት ንግግር ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ተነስተው ወደ ጀርመን የመጡትን ወጣቶች እንደሚያስታውሱ ገልጸው፣ በስፍራው የበርካታ ወጣቶች መገኘት በፍቅር የተሞላ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸው እምነት የተገለጠበት እንደነበር አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ይህን በማለት ዓለም አቀፍ የወጣቶችን ቀን ካስጀመሩ በኋላ፣ እግዚአብሔር የወጣቶችን ዓለም አቀፍ በዓል በአስደናቂ ሁኔታ መባረኩን ገልጸው፣ በዓሉ በየዓመቱ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም በክብር በገባበት በሆሳዕና ዕለት እንዲከበር፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት ከምዕመናን ሐዋርያዊ አገልግሎት አስተባባሪ ጽሕፈት ጋር በመተባበ መወሰናቸው ይታወሳል።በዚህ ዓይነት መንገድ የተጀመረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ክብረ በዓል በየዓመቱ በሀገረ ስብከት ደረጃ፣ ቀጥሎም በሁለት ወይም በሦስት አመት ልዩነት ደግሞ በዓለም ዙሪያ በተለያዩ አገሮች ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር እንዲገናኙ መደረጉ ታውቋል።

በዚህም መሠረት የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል የተከበረው በአርጀንቲና፣ ቦይነስ አይረስ ከተማ ከሚያዚያ 3 እና 4፣1979 ዓ. ም.፣ በስፔን ሳንቲያጎ ደ ኮምፖስተላ ከተማ ከነሐሴ 9–14፣1981 ዓ. ም.፣ በፖላንድ ቼስቶኮቫ ከተማ ከነሐሴ 4–9፣1983 ዓ. ም.፣ በሰሜን አሜርካ ደንቨር ከተማ ከነሐሴ 4-9፣1985 ዓ. ም.፣ በፊሊፒን ማኒላ ከተማ ከጥር 2-7፣1987 ዓ.ም.፣ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ከነሐሴ 13-18፣1989 ዓ. ም.፣ በኢጣሊያ ሮም ከተማ ከነሐሴ 9-14፣1992 ዓ. ም.፣ በካናዳ ቶሮንቶ ከተማ ከሐምሌ 16-21፣1994 ዓ. ም.፣ በጀርመን ኮሎን ከተማ ከነሐሴ 10–15፣1997 ዓ. ም.፣ በአውስትራሊያ ሲድኒ ከተማ ከሐምሌ 8-13፣2000 ዓ. ም.፣ በስፔን ማድሪድ ከተማ ከነሐሴ 10-15፣2003 ዓ. ም.፣ በብራዚል ሪዮ ዲ ጀኔሮ ከተማ ከሐምሌ 15-22፣2005 ዓ. ም.፣ በፖላንድ ክራኮቪያ ከሐምሌ 19-24፣2008 ዓ. ም. ዘንድሮ ደግሞ በፓናማ ከጥር 14-19፣2011 ዓ. ም. እንደሚከበር ታውቋል።           

18 January 2019, 15:11