ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ ከወጣቶቻቸው ጋር፣ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ ከወጣቶቻቸው ጋር፣  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በፓናማ ሁሉን ለማገልገል የቆመች ቤተክርስቲያንን እንደሚያገኙ ተገለጸ።

ሊቀ ጳጳስ ሆሴ ዶሚንጎ የመላው ዓለም ወጣቶች በበዓሉ ቆይታ ወቅት፣ በእግዚአብሔር የፍቅር ምሕረት በመታገዝ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚያቀርቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን ከልብ በመቀበል፣ ራሳቸውንም ለእምነት በማስገዛት ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ደፍረት እንደሚኖራቸው ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ቤተክርስቲያንም ሆነ መላው ማሕበረሰብ ወጣቶችን እንደሚፈልግ ገልጸው፣ መላው ምዕመናንም ወጣቶችን በጸሎታቸው እንደሚያግዟቸው ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

34ኛውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ ለመገኘት ወደ መካከለኛዋ የላቲን አሜርካ አገር ፓናማ የሚጓዙት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዚያች አገር በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ሁሉን ለማገልገል የቆመች ቤተክርስቲያንን እንደሚያገኙ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ ገልጸዋል።

የፓናማው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ ኡሎአ ሜንዴታ፣ በፓናማ ከጥር 14 እስከ ጥር 19 2011 ዓ. ም. ድረስ ለ34ኛ ጊዜ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል፣ የፓናማን ወጣቶች ማሕበራዊ ሕይወት፣ የስደት ሕይወት፣ ከጥንታዊ ቤተሰብ የተወለዱ ወጣቶችንና አፍሪቃዊ የዘር ሐረጋ ያላቸውን ወጣቶች ሕይወት በግልጽ የሚያሳይ አጋጣሚን እንደሚፈጥር ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሳ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ፣ በአገራቸው ላይ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል አስቀድመው ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት በፓናማ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ልዩ ቢመስሉም ነገር ግን ቅርብ ከሆኑ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር፣ ከሐይማኖት ወገኖች ጋር እየተወያየች፣ በሰዎች መካከል ልዩነትን ሳትፈጥር ለሁሉም አገልግሎቷን የምታበረክት ቤተክርስቲያን መሆኗን ገልጸዋል።

ታላቁን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ለማዘጋጀት ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር እንደረዳቸው፣ የእርሱንም እርዳታ ለማግኘት ካለፉት ሁለት ዓመት ወዲህ በየወሩ በጸሎት ሲጠይቁ መቆየታቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ ገልጸዋል። ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል በጥር 14 እንዲከበር የተደረገበትም ዋናው ምክንያት የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የሚታሰቡበት ቀን መሆኑን አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ይህን ታላቅ በዓል በተሳካ መልኩ ለማዘጋጀት ቤተክርስቲያን ካዋቀረችው የበዓል አዘጋጅ ኮሚቴ ጋር የሚተባበር ታዋቂ የሃገር ውስጥ ድርጅት ተሳትፎና እገዛ መኖሩን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ ገልጸዋል።

የፓናማው ሊቀ ጳጳስ፣ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ በገለጻቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ፓናማ በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት በእምነት የቆመች፣ እውነተኛና ደስተኛ፣ የባሕልና የጎሳ ብዛህነት ያላትና በወንጌል ምስክርነት ላይ የምትገኝ ቤተክርስቲያንን እንደሚያገኙ ተናግረው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ዘንድሮ ከጥር 14 እስከ ጥር 19 2011 ዓ. ም. ድረስ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል እንድናዘጋጅ ሲጠይቁን በእርግጠኝነትና በሙሉ ፍላጎት ተነሳስተው እንደሆነ አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ሆሴ ዶሚንጎ ስለ ፓናማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሲናገሩ፣ የፓናማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አስተዳደር  የምትመራ፣ የተሰጣትን የወንጌል ምስክርነት ተልዕኮዋን በሕዝቦች መካከል፣ በተለይም በተረሱት፣ በተናቁትና በተገለሉት ሰዎች መካከል በደስታ የምታከናውን ቤተክርስቲያን መሆኗን ገልጸው፣ ልዩ ቢመስሉም ነገር ግን ቅርብ ከሆኑ የማሕበረሰብ ክፍሎች ጋር፣ ከሐይማኖት ወገኖች ጋር እየተወያየች፣ በሰዎች መካከል ልዩነትን ሳትፈጥር ለሁሉም አገልግሎቷን የምታበረክት ቤተክርስቲያን መሆኗን አስረድተዋል።

ዘንድሮ ከጥር 14 እስከ ጥር 19 2011 ዓ. ም. ድረስ በአገራቸው በፓናማ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል፣ በፓናማ የሚገኙ የተለያየ ባሕል፣ የዘር ሐረግ እና ልማድ ያላቸውን የፓናማ ወጣቶች ማሕበራዊ እውነታን በሚገባ ለማየት የሚያስችል እንደሚሆን ያላቸውን እምነት የገለጹት የፓናማው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ፣ ከዓለም አቀፉ የወጣቶች በዓል የፓናማን ወጣቶች የሚጠቅም ብዙ ነገር መማር እንደሚቻል ገልጸው፣ የመካከለኛው ላቲን አሜርካ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም የበኩሏን ድጋፍ እንደምታደርግ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በአገራቸው ላይ ከሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል፣ ከሌሎችም የላቲን አሜርካ አገሮችና የመካከለኛው የላቲን አሜርካ የሚመጡ በርካታ ወጣቶች ከክብረ በዓል የሚገኘውን ጠቃሚ ሃሳብ፣ ምክር፣ ልምድና ትምሕርት ቀስመው እንደሚመለሱ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ ሆሴ ዶሚንጎ፣ በዓሉ ወደሚከበርበት ስፍራ ወይም አገር  መምጣት የማይችሉ ወጣቶች የበዓሉን ዝግጅቶች በጋራ እንዲከታተሉ የሚያስችላቸው የብዙሃን መገናኛ መንገዶች መመቻቸታቸውን አስረድተዋል። የወጣቶች ዋና ዓላማና ምኞትም በሕይወታቸው ውስጥ ለሚመላለሱ ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ማግኘት መሆኑን ሊቀ ጳጳስ ሆሴ ዶሚንጎ አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ሆሴ ዶሚንጎ በመጨረሻም የመላው ዓለም ወጣቶች በበዓሉ ቆይታ ወቅት፣ በእግዚአብሔር የፍቅር ምሕረት በመታገዝ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚያቀርቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን ከልብ በመቀበል፣ ራሳቸውንም ለእምነት በማስገዛት ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ደፍረት እንደሚኖራቸው ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ ቤተክርስቲያንም ሆነ መላው ማሕበረሰብ ወጣቶችን እንደሚፈልግ ገልጸው፣ መላው ምዕመናንም ወጣቶችን በጸሎታቸው እንደሚያግዟቸው ተናግረዋል።                     

15 January 2019, 16:00