ፈልግ

የኒካራጓ ወጣቶች በፓናማ ወጣቶች በዓል ላይ ለመገኘት                የኒካራጓ ወጣቶች በፓናማ ወጣቶች በዓል ላይ ለመገኘት  

እኛን የሚያገናኘን ድልድይ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሆኑ ተገለጸ።

በፓናማ የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል የቤተክርስቲያንን ዓለም አቀፋዊነት አጉልቶ ከማሳየቱ በላይ ዓለምን በሙሉ አንድ የሚያደርግ ሃይል እንድንገነዘብ፣ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከመስከረም 23 ቀን እስከ ጥቅምት 18 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደውን 15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቀላይ መደበኛ ጉባኤን የተካፈሉትና ከጥር 14 እስከ ጥር 19 2011 ዓ. ም. ድረስ በፓናማ በሚከበረው 34ኛ  ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ ለመገኘት ወደዚያች አገር የሚጓዙት፣ ኢዩኤል ማርጋሪታ እና ይስሐቅ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት የበለጠ አድጎ የተገኘው ከመላው የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከቀሰሙት ምክርና ልምድ መሆኑን ገልጸዋል። ወጣት ኢዩኤልና ማርጋሪታ ጓደኛቸው የሆነውን ይስሕቅን በአካል ሳያገኙት ቢቆዩም በፓናማ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል የእያንዳቸውን ልብ እንደሚቀሰቅስ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “በችግር ውስጥ እንዳንገባ የሚያደርገን እምነት ካለን፣ ይህ እምነት በራሱ ችግር ውስጥ የሚገኝ እምነት ነው” ያሉትን አስታውሰዋል።        

ወጣት ማርጋሪታ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፣  እንደገለጸችው፣ በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ እና በዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል መካከል የጠበቀ ግንኙነት መኖሩን ገልጻ፣ በብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ እንደተመለከትኩት ሁሉ በዓለም አቀፉ የወጣቶች በዓል ላይም የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አለም አቀፋዊነት አረጋግጣለሁ ብላለች። በፓናማ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል የቤተክርስቲያንን ዓለም አቀፋዊነት አጉልቶ ከማሳየቱ በላይ ዓለምን በሙሉ አንድ የሚያደርግ ሃይል እንድንገነዘብ፣ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብላለች። እንደ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጉባኤ ሁሉ፣ በዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይም፣ የተለያዩ ባሕል፣ ቁንቋ እና እምነት ያላቸው ወጣቶች ከዓለም ዙሪያ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መሰብሰባቸው ነው ማለቷ ታውቋል። ማርጋሪታ በማከልም የዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ሌላው ገጽታ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተሰባሰብን የዓለም ወጣቶች በሙሉ እንደ አንድ ቤተሰብ በመሆን የኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና የትንሳኤውን መልካም ዜና ለማብሰር ተጠርተናል ብላለች። የትንሳኤውን መገለጥ ለጥቂቶች ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሕዝብ በሙሉ ነው ብላለች።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል እንዲሆን ብለው ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ የወጣቶች ሃይል መላ ዓለምን ሊቀይር ይችላል ያሉት ያስታወሰችው ወጣት ማርጋሪታ ቅዱስነታቸው በወጣቶች ላይ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ገልጻ፣ በ2005 ዓ. ም. ለአርጀንቲና ወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክታቸው ወጣቶቹ እንዲረባረቡ መምከራቸውን አስታውሳ፣ ፍርሃትን የምናስወግድ ከሆነ፣ የልባችንን አውጥተን የምንናገር ከሆነ፣ ታላላቆቻችን በሚገባ ተገንዝበውን ጥበብን እና ጠቃሚ ምክሮችን ማካፈል ከቻሉበት፣ በእርግጥም ዓለምን መለወጥ እንችላለን ብላለች። እያንዳንዳችን የግላችንን አስተዋጽዖን ማበርከት የምንችለው እርስ በርስ ስንዋደድ፣ ድክመቶቻችንን ስናውቅ፣ ያለንን ተሰጥኦ መገንዘብ ስንችል ነው ብላ ከዚህም በተጨማሪ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ተቋማት፣ በከተሞች፣ በቁምስናዎችም ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር ስንተባበር ነው ብላለች።

ወጣት ማርጋሪታ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገችው ሰፊ ቃለ ምልልስ እንዳስረዳችው ወጣቶችን ማስተማርና መከታተል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድታ፣ ወጣቶችን ከተሳሳተ አካሄድ መመለስ፣ ታላላቆቹ ወጣቶችን በቅርብ ሆነው በማዳምርጥ፣ ፍላጎታቸውንና ምኞታቸውን በመረዳት ማገዝና ህልማቸውን እውን ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድታለች። ወጣቷ በማከልም ወጣቶችም በበኩላቸው የተሻለ ዓለምን የማግኘት ተስፋቸውን በመሰነቅ፣ የተሻለ ዓለምንም የሚገነባው ሌላ ሳይሆን ራሳቸው እንደሆኑ በመገንዘብ የሚያገኙትን ዕድል በሙሉ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጻለች።

ወጣት ማርጋሪታ በፓናማ በሚካሄደው 34ኛ ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ የምትሰጠውን ምስክርነት በተመለከተ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ለቀረበላት ጥያቄ ስትመልስ እንዳለችው፣ ወጣት መሆን በራሱ አንድ ጸጋ መሆኑን ገልጻ በዚህ የወጣትነት ትኩስ ሃይል በመታገዝ ዓለምን ለመለወጥ ያለን ችሎታ በራሱ መልካም ተስፋ መሆኑን ገልጻ፣ ይህን ሕልም እውን ለማድረግ የመላው ዓለም ካቶሊክ ወጣት በሙሉ በተግባር የተመለከቱትን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር በመያዝ፣ እንቅፋት ቢያጋጥማቸው፣ ሁሉ ያለቀ የተዘጋ ቢመስላቸውም ተስፋ መቁረጥ እንደማያስፈልግ አሳስባለች።

ወጣት ይስሐቅም በበኩሉ ዓለማችን የምትገኝበትን ሁኔታ መላው የፓናማ ማሕበረሰብም ይገነዘበዋል ብሎ፣ ዓለማችን ለሰው ልጆች በሙሉ ክፍት በመሆኗ ክርስቲያናዊ ማንነታችንን፣ እምነታችንንም በተለያዩ መንገዶች መመስከር ይቻላል ብሎ ከእምነታችን ብዙ መማር ይቻላል ብሏል። ወጣት ይስሐቅ፣ በዓለማችን በብዙ አካባቢዎች በእምነታቸው ምክንያት ስቃይ የሚደርስባቸው ሰዎች መኖራቸውን በማስታወስ፣ የሐይማኖት ነጻነት ያለን በሙሉ የፍቅር ልባችንን በመክፈት ከሌሎች የዓለም ክርስቲያኖች ጋር ያለንን የመንፈስ አንድነት መግለጽ ይኖርብናል ብሏል።

ወጣቶች ዘላቂ ለውጥን የምናመጣ መሆን አለብን ያለው ወጣት ይስሐቅ፣ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገልጸው፣ በ15ኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ አጠቀላይ መደበኛ ጉባኤ አማካይነት መላዋ ቤተክርስቲያን ወጣቶችን ከልብ ያዳመጠች መሆኗን ገልጾ በአሁኑ ወቅትም ወጣቶችን በሙሉ ልትረዳቸው የምትችልባቸውን ውጤታማ ሐዋርያዊ የአገልግሎት መንገዶችን እያዘጋጀች ትገኛለች ብሏል። በመሆኑም ወደ ፊት እየተጓዝን፣ በጉዟችንም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እገዛ እንዲታከልበት በጸሎታ እንለምናታለን ብሏል።                        

17 January 2019, 17:32