ፈልግ

የጓዳሎፔው እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ - የጓዳሎፔው እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ -  

የጓዳሎፔው እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ - በሜክስኮ

የጓዳሎፔው እመቤታችን ማርያም ቤተመቅደስ የሚገኘው በሜክስኮ ከተማ ሰሜናዊ ክፍል ነው፡፡ ይህ ቤተመቅደስ የተሠራው ቴፔያክ ሂል በሚባለው ኮረብታ ሥር ነው፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሁዋን ድየጎ የታየችውም በዚያው ኮረብታ ሥር ነበር፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በጓዳሎፔ ለሁዋን ድየጎና ለአጎቱ ሁዋን ቤርናርዲኖ የተገለጸችው አምስት ጊዜ እንደ ነበረ የቤተመቅደሱ ታሪክ ያስረዳናል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በጓዳሎፔ የተገለጸችው ለሁዋን ድየጎ ሲሆን እ.አ.አ. በታህሣሥ 9 ቀን 1531 ዓ.ም. ጧት በማለዳ ነበር፡፡ ይህም የተከሠተው ሕንዳዊው ካቶሊክ ሁዋን ዲየጎ ጥላተሎልኮ በሚባለው ስፍራ ወደሚገኘው ቤተክርስቲያን ለቅዳሴ ጸሎትና ትምህርተ ክርስቲያን ለመማር ሲሄድ ሳለ ነበር፡፡

ሁዋን ዲያጎ በኮረብታው ከፍተኛ ስፍራ ብሩህ ብርሃን ከማየቱም በላይ ወደ ኮረብታው ላይ ከፍ ብሎ እንዲወጣ የሚጋበዝ የሴት ድምፅ ሰማ፡፡ በኮረብታው ከፍተኛ ስፍራ ሲወጣም በሚደነቅ ሰማያዊ ብርሃን መካከል የቆመችውን ሴት አየ፡፡ ዘለዓለም ድንግል የሆነችው የእውነተኛው አምላክ እናት፣ እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ሆነችም ነገረችው፡፡ እዚያም ለሰው ሁሉ እናታዊ ፍቅሯን፣ ርኀራኄዋንና ጥበቃዋን የምትገልጽበት ቤተመቅደስ በስሟ እንዲሠራ እንደምትፈልግም ነገረችው፡፡ እንዲህም አለችው፤ “እኔ መሐሪት እናትህ ነኝ፡፡ ይኸውም ላንተና እኔን ለሚወዱ፣ በእኔም ለሚተማመኑና አማላጅነቴን ለሚጠይቁ ለሰው ልጆች በሙሉ መሐሪት እናት ነኝ፡፡ ስለሆነም ወደ ሜክስኮ ከተማ አቡን ዘንድ ሄደህ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ፍላጎትዋን እንድናገር ወደ እርስዎ ልካኛለች ብለህ ንገራቸው” አለችው፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሁዋን ድየጎ ለሁለተኛ ጊዜ የተገለጸችው ለመጀመሪያ ጊዜ በተገለጸችበት በዚያው ቀን ማለትም እ.አ.አ. በታህሣሥ 9 ቀን 1531 ዓ.ም. ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሜክስኮ አቡን የሁዋን ድየጎን መልእክት በቀላሉ ለመቀበል ዝግጁ አልነበሩም፡፡ በዚህ ዐይነት ሁዋን ድየጎ ወደ ቴፔያክ ኮረብታ ሲመለስ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ስትጠብቀው አገኛት፡፡ ወደ አቡኑም ያቀረበው መልእክት ተቀባይነት እንዳላገኘ ነገራት፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በበኩሏ ወደ አቡኑ መልእክቷዋን ይዞ እንደገና በሁለተኛው ቀን እንዲሄድ ነገረችው፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሁዋን ድየጎ ለሦስተኛ ጊዜ የተገለጸችው አቡኑን ለሁለተኛ ጊዜ ባገኛቸው ዕለት ነበር፡፡ አቡኑ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ማርያም አንድ ምልክት እንድታሳያቸው እንደ ጠየቁትም ነገራት፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በበኩሏ ደግሞ አቡኑ የጠየቁትን ምልክት በሚቀጥለው ቀን ለማሳየት ቃል ገባችለት፡፡ ነገር ግን በተባለው ዕለት ሁዋን ድየጎ ወደ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ ለመሄድ አልቻለም ነበር፡፡ ምክንያቱም አጎቱ ሁዋን ቤርናርዲኖ በድንገት በጠና ታሞ ነበርና፡፡ ለአራተኛው ጊዜ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሁዋን ድየጎ የተገለጠችው እ.አ.አ. በታህሣሥ 12 ቀን 1531 ዓ.ም. ነበር፡፡ ይኸውም ሁዋን ድየጎ ለበሽተኛ አጎቱ ቄስ ለመጥራት በጥላተሎልኮ ወደሚገኘው ቤተክርስቲያን በመሄድ ላይ ሳለ ነበር፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ከቴፔያክ ኮረብታ ወርዳ ነበር ሁዋን ድየጎን በመንገድ ላይ ያገኘችው፡፡ ሁዋን ድየጎም በፊተኛው ቀን ከርስዋ ጋር የነበረውን ቀጠሮ ለማክበር ባለመቻሉም ይቅርታ ጠየቃት፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምም የሁዋን ድየጎን ንግግር በጥሞና ካዳመጠች በኋላ፣ እርሱም ንግግሩን ካበቃ በኋላ እንዲህ አለችው፤ “ከልጆቼ መካከል እጅግ አነስተኛውና እጅግ ውድ ልጄ ሆይ፣ አሁን እኔን አዳምጠኝ፡፡ አንዳች ነገር አያስጨንቅህ፣ ሕመምንም ሆነ ስቃይን አትፍራ፡፡ ያንተ እናት እኔ እዚሁ አይደለሁም ወይ? አንተም በጥላዬ፣ በጥበቃዬ ሥር፣ አይደለህም እንዴ? በክንዴ እቅፍ ውስጥ አይደለህም ወይ? ስለ አጎትህም ቢሆን አትጨነቅ፤ አይሞትምና፤ ደህና መሆኑንም አረጋግጥልሃለሁ፡፡ በጣም አጽናኝ የሆኑትን የእመቤታችንን ቃላት ከሰማ በኋላ ሁዋን ድየጎ ለአቡኑ የሚወስደውን መልእክት እንድትነግረው በትሕትና ጠየቃት፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በበኩልዋ ደግሞ በፊተኞቹ ሦስት ጊዜ ወደ ተገለጸችለት ቴፔያክ ኮረብታ ላይ እንዲወጣ ጠየቀችው፡፡ በቴፔያክ ኮረብታ ላይ ስታገኘው በኮረብታው ላይ ብዙ የፈካ አበባ እንደሚያገኝና ቆርጦም እንዲያመጣላት አዘዘችው፡፡ ነገር ግን ሁዋን ድየጎ በዚያ ደረቅ ኮረብታ ላይ የፈካ አበባ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነገር መሆኑን አሰበ፡፡ ይሁን እንጂ በኮረብታው ጎን በጣም ቆንጆ የፈካ አበባ አገኘና ቆርጦ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በጠየቀችው መሠረት በካባው ጠቅልሎ አመጣላት፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምም አበባውን በደንብ አስተካክላ ለአቡኑ እንዲወስድላቸው ነገረችው፤ ይህም አቡኑ ጥያቄዋን እንዲፈጽሙ የሚገፋፋቸው ምልክት ይሆናል አለችው፡፡ እጅግ የተደሰተው ሁዋን ድየጎም አበባውን በካባው ጠቅልሎ ይዞ በብፁዕ አቡነ ፍሬይ ሁዋን ዴ ዘማራጋ ፊት ቆሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለአራተኛው ጊዜ እንዴት እንደ ተገለጸችለት ነገራቸው፡፡ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የላከችላቸውን ምልክት ለማሳየትም ካባውን በከፈተ ጊዜ አበባዎቹ በወለሉ ላይ ሲወድቁ አቡኑንና ሁዋን ድየጎን በጣም ያስገረመ ምልክት ተከሠተ፡፡ ይኸውም በሁዋን ድየጎ ካባ ላይ ልክ በቴፔያክ ኮረብታ ላይ ትታየው የነበረችው የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ታትሞ ቀረ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጧት በማለዳ ማለትም ከላይ በተጠቀሰው ታህሣሥ 12 ቀን 1531 ዓ.ም. የጓዳሎፔ አምስተኛው መገለጽ ተከሥቶ ነበር፡፡ ይኸውም እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ለሁዋን ድየጎ አጎት ለሁዋን ቤርናርዲኖ ተገልጻ ነበር፡፡ ቀደም ብላ ለሁዋን ድየጎ ቃል በገባችለት መሠረት ከበሽታው ድኖ የተሟላ ጤንነት እንዲኖረውም ረድታው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ሁዋን ድየጎ ዕድሜው 57 ዓመት ሲሆን አጎቱ ሁዋን ቤርናርዲኖ ደግሞ የ68 ዓመት አዛውንት ነበሩ፡፡ ሁለቱም በመጀመሪያ ወደ ካቶሊክ እምነት ከገቡት ከአካባቢው ሰዎች መካከል ነበሩ፡፡ ሁዋን ቤርናርድኖም እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም በተአምራዊ መንገድ ከበሽታው እንደ ፈወሰችው ለአቡኑ እንዲነግራቸው እንዳዘዛቸውም ለሁዋን ድየጎ ነገረው፡፡ በተጨማሪም ደግሞ እመቤታችን እጅግ ቅድስት ማርያም ለሁዋን ቤርናርዲኖ ሥዕሏ “የጓዳፔው ቅድስት ማርያም ሥዕል” ተብሎ እንዲጠራ እንደምትፈልግም ነገረችው፡፡ ይኸው በዚሁ ስም እስካሁን ድረስ ለአምስት መቶ ዓመታት ያህል ስትከበር ኖራለች፡፡ የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያምን ጥያቄ መሠረት በማድረግ የመጀመሪያው የጓዳሎፔው እመቤታችን ቤተመቅደስ እ.አ.አ. በ1532 ዓ.ም. በቴፔያክ ኮረብታ ሥር እንደ ተሠራም ይነገራል፡፡ ይህም የመጀመሪያ ቤተመቅደስ ለ90 ዓመት ያህል ካገለገለ በኋላ እ.አ.አ. በ1622 ዓ.ም. ሁለተኛው ቤተመቅደሰ እንደ ተሠራም ከቤተመቅደሱ ታሪክ መዛግብት እንረዳለን፡፡

ከዚያም በኋላ እ.አ.አ. በ1695 ዓ.ም. የትልቁ ቤተመቅደስ (ባዚሊካ) መሠረት ተጣለ፡፡ ይህ ትልቁ ቤተመቅደስ እ.አ.አ. በ1709 ዓ.ም. እንደ ተመረቀም ከጓዳሎፔ ቤተመቅደስ ታሪክ ለመረዳት እንችላለን፡፡ እ.አ.አ. በ1750 ዓ.ም. አከባቢ ቤተመቅደሱ እንደ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከመቆጠሩም በላይ መነኮሳት በቋሚነት ይኖሩበት ነበር፡፡ እ.አ.አ. በ1754 ዓ.ም. ደግሞ የጓዳሎፔው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ በሮም በሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ ላትራኖ ባዚሊካ ሥር እንዲሆን ተደርጎ ነበር፡፡ በተጨማሪም ደግሞ እ.አ.አ. በጥቅምት 12 ቀን 1895 ዓ.ም. ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 13ኛው (1878-1903) በጻፉት ድንጋጌ መሠረት የጓዳሎፔው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል በታላቅ ሥነ ሥርዓት ዘውድ እንደ ደፋም ይነገራል፡፡ እ.አ.አ. በ1904 ዓ.ም. ደግሞ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ፒዮስ 10ኛው (1903-1914) በበኩላቸው ደግሞ የጓዳሎፔው እመቤታችን ቤተመቅደስ ዋና ባዚሊካ እንዲሆን ወሰኑ፡፡ እ.አ.አ. በጥቅምት 12 ቀን 1945 ዓ.ም. ደግሞ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛው (1939-1958) የጓዳሎፔው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ዘውድ የደፋበትን 50ኛው የወርቅ እዩቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ የጓዳሎፔው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የመላው አሜሪካ ባልደረባ እንድትሆን ደነገጉ፡፡ ባጭሩ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጓዳሎፔ የተከሠተው የእመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም መገለጽ በሜክስኮ ሕዝብ ዘንድ ታላቅ መንፈሳዊነት የሰጠው ክሥተት ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ባሁኑ ጊዜ ተአምረኛው የ1531 ዓ.ም. የእመቤታችን ሥዕል የሚገኝበት ዘመናዊ ባዚሊካ የተመረቀው እ.አ.አ. በ1976 ዓ.ም. ነበር፡፡ የጓዳሎፔን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ባዚሊካ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ (1978-2005) ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኙት እ.አ.አ. በ1979 ዓ.ም. ነበር፡፡ ወደ ጓዳሎፔ እንደገና በመሄድ እ.አ.አ. በ1990 ዓ.ም. ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱሰ ዮሐንስ ጳውሎሰ ዳግማዊ የጓዳሎፔ እመቤታችን መገለጽ ዋና ተዋናይ የነበረውን ሁዋን ድየጎን ብፁዕ ከማድረጋቸውም በላይ የጓዳሎፔው የእመቤታችን መገለጽ ትክክለኛ መሆኑንም በይፋ አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም ደግሞ እ.አ.አ. በሐምሌ 31 ቀን 2002 ዓ.ም. ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ብፁዕ ሁዋን ድየጎ ቅዱስ ነው በማለት በሮም በይፋ አውጀዋል፡፡ በየዓመቱ ከ18-20 ሚሊዮን መንፈሳውያን ተጓዦች የጓዳሎፔን እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ይጎበኛሉ፡፡ በዚህ ዐይነት የጓዳሎፔው እመቤታችን እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ በሁኑ ዘመን በመላው ዓለም ካሉት ብዙ ሰዎች ከሚጐበኙአቸው ታላላቅ የክርስቲያን ቤተመቅደሶች አንዱ ከመሆኑም ሌላ በዓለም ካሉት ትላልቅ መንፈሳዊ ጉዞ ከሚደረግባቸው ማዕከላትም አንዱ ነው፡፡

ምንጭ፡ ታዋቂ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የካቶሊክ ቤተመቅደሶች በዓለም ላይ

ጸሐፊ፡ ክቡር ዶክተር አባ አንጦኒዮስ አልቤርቶ ካፑቺን

 

 

12 December 2018, 15:29