ፈልግ

የሊባኖስ ቀውስ፣ የሊባኖስ ቀውስ፣ 

የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ወጣቶችን የወደ ፊት ተስፋዋ ማድረጓ ተገለጸ።

በካቶሊካዊት ቤተክስቲያን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ወጣቶች በእምነታቸው ጠንክረው እንዲገኙ፣ ለሀገራቸው እድገት፣ ሰላም፣ ፍቅርና ፍትህ መጎልበት መሥራት እንዳለባቸው፣ ስቃይና መከራ ቢበዛም ስቃይንና መስዋዕትነትን ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር በመጋራት የሰው ልጆችን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በመልዕክታቸው፣ በአካባቢው አገሮች የሚገኙ ክርስቲያኖች መከራ፣ ስቃይና ስደት ቢፈራረቅባቸውም የወንጌል ምስክርነትን መስጠታቸውን አላቋረጡም ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ፓትሪያርኮች በጋራ ሆነው ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው ወጣቶቻቸው ከመሰደድ ይልቅ በአውልድ አገራቸው ሆነው ጦርነት፣ አመጽና ስደት የደረሰባቸውን አገራቸውን መልሰው እንዲገነቡ አደራ ብለዋል።

ብጹዓ ጳጳሳቱ ለመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ወጣቶች ባስተላለፉት ጥብቅ መልዕክታቸው እንዳስገነዘቡት፣ ሰውና ጊዜው በጭካኔ የተሞላ ቢሆንም የአገሮቻችሁ ዋና አለኝታ በመሆን ታሪክን የምትሠሩ ሁኑ ብለዋል። በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ብጹዓን ፓትሪያርኮች በኢራቅ ዋና ከተማ በባግዳድ ካካሄዱት 26ኛ የሕብረት አገሮች ጳጳሳት ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ባወጡት የጋራ መልዕክታቸው እንደገለጹት የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ወጣቶች በየአገሮቻቸው የሚከሰቱትን አመጾችና ጦርነቶች ሸሽተው በሚሰደዱበት ጊዜ ቤተክርስቲያን ተስፋ ያደረገቻቸውን በርካታ ወጣቶች እንደምታጣ ገልጸው፣ ብጹዓን ጳጳሳቱ የወጣቶችን ስቃይ እንደሚጋሩ ገልጸው፣ ከመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የወጣቶች መሰደድ ወደ ፊት በአካባቢው የክርስቲያኖችን መገኘት አደጋ ላይ እንደሚጥል አስረድተዋል።

“በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ወጣቶች የወደ ፊት ተስፋ ናቸው” በሚል ርዕስ ህዳር 21 ቀን 2011 ዓ. ም. በኢራቅ ዋና ከተማ በባግዳድ 26ኛ ጉባኤ ያቸውን ያደረጉት የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዓን ፓትሪያርኮች ለወጣቶች ባስተላለፉት ልዩ መልዕክታቸው፣ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ውስጥ የክርስቲያኖች ቁጥር ጥቂት እንደሆነ ገልጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስም እናንተ የዓለም ጨውና ብርሃን ናችሁ ያለውን አስታውሰው፣ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ብዙ ሰማዕታትን ያፈራች ቤተክርስቲያን የምትገኙባቸው አገሮች እንደሆኑም አስረድተዋል። በመሆኑም በካቶሊካዊት ቤተክስቲያን የምስራቅ አብያተ ክርስቲያናት ወጣቶች በእምነታቸው ጠንክረው እንዲገኙ፣ ለሀገራቸው እድገት፣ ሰላም፣ ፍቅርና ፍትህ መጎልበት መሥራት እንዳለባቸው፣ ስቃይና መከራ ቢበዛም ስቃይንና መስዋዕትነትን ከሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር በመጋራት የሰው ልጆችን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብጹዕን ጳጳሳት በመልዕክታቸው፣ በአካባቢው አገሮች የሚገኙ ክርስቲያኖች መከራ፣ ስቃይና ስደት ቢፈራረቅባቸውም የወንጌል ምስክርነትን መስጠታቸውን አላቋረጡም ብለዋል።

ከፍልስጤም ጋር አንድነት እንዲኖር፣

ብጹዓን ፓትሪያርኮቹ ጭቆናና ግድያ የሚፈጸምባቸውን የፍልስጤም ሕዝብ አስታውሰው በአካባቢው እርቅን ለማምጣት የተጀመረው የሰላም ውይይት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት በመልዕክታቸው ገልጸዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከከል እየተደረገ የሚገኘው የሰላምና የእርቅ ውይይትም መልካም ውጤት እንዲያስገኝ፣ ሁለት ራስ ገዝ መንግሥታት በሚለው ሃሳብ የምፍትሄ ሃሳብ ላይ ሁለቱ መንግሥታት ስምምነት ላይ እንዲደርሱና ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም ድጋፍን ያገኘ የእርቅ መንገድ በመሆኑ ይህ የሰላምና የእርቅና ሃሳብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው ኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲና እንድትሆን የሚለውን፣ አሜርካ ኤምባሲዋን ከቴላቭቭ ወደ ኢየሩሳሌም ለማዛወር ያደረገችውን ውሳኔና እስራኤል የአይሁድ ሕዝብ ብሔራዊው ክልል የሚያደርጋትን የቅርብ ጊዜ ሕግ በጽኑ መቃወማቸውን ገልጸዋል።

ሶርያን በተመለከተ፣

በበርካታ የሶርያ ግዛቶች ውስጥ ቀስ በቀስ እየታየ የመጣው መረጋጋት፣ የሰላም ተስፋን እንደሰጠ የጉባኤው ጳጳሳት ገልጸው ይህን ተከትሎ በጦርነቱ ምክንያት በየአጎራባች አገሮች ተበታትነው የሚገኙ የሶርያ ስደተኞችና ተፈናቃዮች ወደ አገራቸው እንዲመለሱና ለብሔራዊ አንድነት በሕብረት እንዲቆሙ ጥሪያቸውን አቅርበውላቸዋል። የጉባኤው ብጹዓን ጳዓሳት ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሶርያ የሚሰደዱትን ቤተሰቦች ተቀብላ ላስተናገደች፣ የእርዳታ እጆችዋን ለዘረጋች ሊባኖስ ያላቸውን አድናቆት በጭብጨባ ገልጸው ምስጋናም አቅርበውላታል።

ብጹዓን ፓትሪያርኮቹ በመልዕክታቸው ፍጻሜ ላይ እንደገለጹት ቀጣዩ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ካቶሊካዊ ብጹዓን ፓትሪያርኮች ጉባኤ የሚካሄደው በግብጽ፣ አሌክሳንድሪያ ከተማ ከህዳር 15 እስከ ህዳር 19 ቀን 2011 ዓ. ም. እንደሚሆን ይፋ አድረገዋል።

07 December 2018, 16:10