ፈልግ

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የአትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት (ፋይል) ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን የአትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት (ፋይል) 

የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት 45ኛ መደበኛ ጉባኤያቸውን ተከትሎ ያስተላለፉት መልዕክት

ህግና ሥርዓት ተከብሮ ዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በሠላም መኖር ይችሉ ዘንድ ማንም በሀገሩ ባዳነት ሳይሰማው ተከብሮ ይኖር ዘንድ ሕዝባችን እርስ በርሱ እንዲቻቻል እንዲሁም ህግ አስከባሪው አካል ህግን እንዲያስከብር ማንኛውም ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን እንዲገታ በእረኝነት እና በአባትነት መንፈስ እናሳስባለን፡፡


"በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን!!" (ሉቃ 2፡14)

ለመላው ካቶሊካውያን ካህናት፣ ደናግል፣ ምዕመናን፣ ወጣቶችና ህፃናት እንዲሁም በጎ ፈቃድ ላላችሁ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፤
የእግዚአብሔር ሠላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን!!
እኛ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ከታህሣሥ 1 - 5 ቀን 2011 ዓ.ም. 45ኛ መደበኛ ጉባኤያችን በአዲስ አበባ ከተማ በጳጳሳት ጉባዔ ማዕከል አካሂደናል፡፡ በዚህ ጉባኤያችን የቤተክርስቲያናችን ስብከተ ወንጌል ሥራ ጉዳይ በስፋት ተወያይተናል፡፡ አቅጣጫም አስቀምጠናል፡፡ ስለሀገራችን ሠላም ስለህዝቦች አንድነት ጸሎት አድርገናል፡፡ ያለንበት ጊዜ ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በጸሎት ዝግጅት የምናደርግበትና ልደቱንም በናፍቆት የምንጠባበቅበት ጊዜ ነው፡፡ ለበዓሉ ዝግጅት ስናደርግ በህይወታችን ተገቢውን መንፈሳዊ ዝግጅት እያደረግን በዚህም መንፈስ ለአምላካችን የተገባን ሆነን እንድንገኝ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በዓሉም ስናከብር የሰላም አለቃ፣ የዘላለም አባት፣ መካር፣ ድንቅ ኃያል የሆነው ጌታችን መድኃኒታችን ሰላምን ለሀገራችን ለህዝባችንና ለቤተሰባችን እንዲሁም ለእያንዳንዳችን እንዲሰጥ በልዩ ሁኔታ የምንጸልይበት ጊዜ ነው፡፡
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ልዩ የፀጋ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ሁሉም የሰው ልጆች ልባችንን ክፍት አድርገን ፀጋ የሆነው ህፃኑ ኢየሱስን እንድንቀበል ተጠርተናል፡፡
የልደት በዓል የምህረት ጊዜ ነው፡፡ እግዚአብሔር ዓለምን በምህረቱ በቸርነቱ ፣ በደግነቱ የጎበኘበት ፤ የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ምህረት የቀመሰበት ፤ ከኃጢአት ቀንበር ነፃ የወጣበት ጊዜ ነው፡፡
የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ስናከብር የዓለም ብርሃን የሆነው የኢየሱስ የማዳን ምሥጢር የተገለጸበት ወቅት ነው፡፡ "ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፡፡” (ዮሐ 1፡9) በዚህም ኢየሱስ ለሕዝቦች የተገለጸ ብርሃን መሆኑን የምናስተነትንበት ጊዜ ነው፡፡ እግዚአብሔር እኛን እጅግ ስለወደደና ስላከበረን አንድ ልጁን ወደ ዓለም ላከ፡፡ ክርስቶስ ከእርሱ ጋር ብርሃናቸው መሆኑን በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለገባልን በቤተልሔም ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ብርሃን ሆኖ መጥቶ በእያንዳንዳችን ህይወት ገብቶ በመሀከላችን ማደርያውን ሠርቶ እኛንም የብርሃን ልጆች እንዲሁም የዓለም ብርሃንም አደረገን፡፡ (ማቴ 5፡14)
የልደቱን ዝግጅት ላይ ባለንበት ወቅት ጊዜ ዓለም ሁሉ በተለይ ደግሞ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁን ጊዜ ምን ያህል አጣብቂኝ ውስጥ እንደሆነችና በልዩ መልኮች፣ ፍርሃትና ጭንቀት እየተስተዋሉ እንዳሉ ተመልክተናል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙዎች መብታቸው የተገፉበት ፣ በድህነት የሚማቅቁበት፣ ብዙዎች የሰው ልጅ ስቃይ እንግልትና መዋረድ ያስተናገደችበት ፣ በዘርና በጎሳ የተከፋፈልንበት፣ ብዙዎች በሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት የአካል እና የስነልቦና ጉዳት የደረሰባቸው፣ ብዙዎች ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ የእኛ ብሔር አይደላችሁም ዉጡልን ተብለው ከቤት ንብረታቸው እና ከክብራቸው የተፈናቀሉበት፣ ቤት ንብረታቸው ወድሞ የተንገላቱበት፣ በዚህም ምክንያት ብዙዎች በህይወታቸው አደጋ ላይ የወደቁበት፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉበት፣ ሠላም ጠፍቶ በምትኩ የኃዘን የቁጭትና የበቀል ስሜት ውስጥ የገቡበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ፣ የዘረኝነት፣ የአድልኦአዊነት ጨለማ ሀገራችንን ውጦ የቆየ ቢሆንም በቅርቡ እየተደረጉ ባሉት የለውጥ እንቅስቃሴዎች የተስፋ ጭላንጭል እያየን እንገኛለን፡፡
በዚህ ከባድ ወቅት ውስጥ ሆነን ለዓለማችን እንዲሁም ለሀገራችን ተስፋ ይሆን ዘንድ ጌታችን መድኃኒታችን ይመጣልና ፤ የሰላም አለቃ፣ የዓለም ብርሃን በቤተልሔም ይወለዳልና ፤ እርሱ ራሱ በጨለማ ለሚኖሩ ሰዎች ብርሃን እንዲያዩ ያበቃ በልደቱ አማካይነት ሀገራችን ከጨለማ ከክፋት ወደ ብርሃን፤ ወደ ተስፋ፤ ወደ ደግነት፤ ወደ መተማመን፤ ወደ ይቅርታና ፍቅር ያሸጋግራታል እናምናለን፤ ተስፋም እናደርጋለን፡፡ እግዚአብሔር ይህችን ሀገር አይተዋትምና!!
‹‹የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፤ የሚከተለኝ የህይወት ብርሃን ያገኛል እንጂ በጨለማ ውስጥ አይመላለስም›› ዮሐ 8፡12 እንግዲህ የልደት ብርሃን በሁላችን ልብ ውስጥ ያብራ፡፡ ምንም እንኳን ምድራችን ጨለማና ክፋት የሞላት ቢመስለንም ጨለማ ብርሃንን፤ ክፋት ደግነትን ሊያሸንፍ አይችልም፡፡
የልደት በዓል የሠላም የፍቅር የእርቅ በዓል ነው፡፡ ሠማይና ምድር የተስማሙበት መላእክት በሠማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው (በጎ ፈቃድ ላላቸው ሁሉ) ሠላም ይሁን ብለው የዘመሩበት ወቅት ነው፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ወደ እኛ እንደቀረበ ከእኛ ጋር ቀጥተኛ ውይይት እንደጀመረ እርስበርሳችን እውነተኛ ውይይት የምንጀምርበት፣ የምንከባበርበት እና የምንደጋገፍበት ወቅት ነው፡፡ እኛን እንዳከበረን እርስ በርሳችን እንድንከባበርና እንድንዋደድ፤ እንድንተሳሰብ መንፈሱን አድሎናል፡፡ በጌታቸን ክብሩን ትቶ ወደ ምድር መምጣት እግዚእብሔር ሰማይና ምድር እንደታረቁ ሁሉ የሰው ልጆች እርስ በእርሳቸው ዘር፣ ኃይማኖት፣ ብሔር፣ ጾታ ሳይገድባቸው እንዲታረቁ አድርጓል፡፡ ስለዚህም በሕዝቦች መካከል ፍጹም ህብረት፣ አንድነትና መከባበር ይጎለብት ዘንድ እኛ ክርስቲያኖች ትልቅ ኃላፊነት ተጥሎብናል፡፡ ሁላችንም ልብ ለልብ ተቀራርበን ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምንነጋገርበት እና የምንግባባት፤ የምንረዳዳበት ብሎም ሰላምና ደስታ የምንጎናጸፍበት ዘመን እንዲመጣ ተግተን እንድንሰራ እና እንድንጸልይ ያስፈልጋል፡፡
በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ፍቅሩ በልባችን ውስጥ ስላስገባ በዓለም ውስጥ እንዲሁም በሀገራችን ሠላም እንድናሰፍን ያስችለናል፡፡ የእርሱ ሠላም የትኛውም ሰብአዊ ኃይል ሊያቆመው አይችልም፡፡ የእርሱ ሰላም ለልባችን ደስታን ይሰጣል፡፡ ነፍሳችንን ያበረታል፤ ለህይወታችን ትርጉም ይሰጣል፣ መንገዳችንን ያቀናል፡፡ የክርስቶስ ሰላም ጥላቻን እንድናስወግድ ፤ ቂምና በቀልን እንድንተው፤ መልካምነትን እና መተሣሠብን፣ እውነትን እንድንይዝና ጨለማንና ክፋትን እንድናሸንፍ ያደርገናል፡፡ ክርስቶስ ተስፋችን ነውና፡፡ በሀገራችን ዛሬ የምናየው ዘረኝነት ፣ ሙሰኝነት፣ ህግ አልበኝነት ፣ ብልሹ አስተዳደር ፣ የሞራል ዝቅጠት ጊዜያዊ እንደሆነ አምነን ክርስቲያናዊ ህይወታችን አጠንክረን ለህግ ተገዢ እና የሠላም መሣሪያ ከሆንን አሸናፊው የክርስቶስ ፍትህ ሠላምና እውነት ነው፡፡ ስለዚህ በተስፋ እንኑር፡፡
ህግና ሥርዓት ተከብሮ ዜጎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በሠላም መኖር ይችሉ ዘንድ ማንም በሀገሩ ባዳነት ሳይሰማው ተከብሮ ይኖር ዘንድ ሕዝባችን እርስ በርሱ እንዲቻቻል እንዲሁም ህግ አስከባሪው አካል ህግን እንዲያስከብር ማንኛውም ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን እንዲገታ በእረኝነት እና በአባትነት መንፈስ እናሳስባለን፡፡ የንፁኃን ደም በእግዚአብሔር ፊት እንደ አቤል ደም ይጮሃልና፡፡ የንፁኃን ደም ማፍሰስ ይብቃ፤ መንግሥት ለሕዝብ ሠላም ዋስትና የመስጠት ኃላፊነት ስላለበት ይህንን ህገመንግሥቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ ሊወጣ ይገባዋል፡፡ እያልን ባላችሁበት ሁሉ በሞት ሕይወታቸውን ላጡ ደግሞ ፀሎት፣ ከቤት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ሁሉ ዕርዳታችሁን እንድትሰጡ አደራ እንላለን፡፡ ውስጣችሁ በሀዘን የተጎዳ ባልጠበቃችሁት ጊዜና ሰዓት ውድ ወገናችሁን በሞት የተነጠቃችሁ ወገኖች ሁላችሁ የበቀልን ብድራት የሚመለስ እግዚአብሔር ስለሆነ በቀልን ለእግዚአብሄር ትታችሁ ልባችሁን በምህረትና በይቅርታ በእርቅ እንዲሞላ ወደ አምላካችሁ ጸልዩ፡፡ በበቀል በሀዘን እና በቁጭት የተሞላው መንፈሳችሁ በእግዚአብሔር ጸጋ ወደ ሠላም፣ ወደ ምህረት፣ ወደ ይቅርባይነት ይመልስላችኋል፡፡ እውነትን ታውቃላችሁ ፤ እውነትም ነፃ ታወጣችኋለች፡፡ ዮሐ8፡32 እኛም በጸሎታችን ከጎናችሁ ነን፡፡
በየትኛውም ቦታ ሕዝብን እና ወገንን መበደል ፣ ማሠቃየት፣ ማፈናቀል፣ ማጋጨት፣ ኃጢአት ስለሆነ በክፋት ሃሳብና ተግባር የተጠመዳችሁ ግለሰቦችና ቡድኖች ወገኖቻችንም ልቦናችሁ ወደ እግዚአብሔር እንድትመልሱና ንሰሐ እንድትገቡ አጥብቀን እንጠይቃችኋለን፡፡ ከዚህ ድርጊት በመቆጠብ ፣ በመቻቻልና በመረዳዳት አብረን መኖር እንዳለብን እናሳስባችኋለን ‹‹እውነትን በፍቅር እየተናገርን እንገስፃችኋለን›› ኤፌ 3፡15 የወገኖቻችሁ ድሆች ሥቃይ እና ለቅሶ ወደ እግዚአብሔር ደርሷልና፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ቃየልን ወንድምህ የት አለ? ብሎ እንደጠየቀ እናንተንም ይጠይቃችኋል፡፡›› ዘፍ 4፡9-11
ቀደም ባሉት ዘመናት ስለተፈጸመው በደል ፍትህን በሚያሰፍን መልኩ በእርቅና በይቅርታ ይፈጸም ዘንድ ካቶሊካውያን በያሉበት ‹‹የሚያስታርቁ ብጹዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና›› (ማቴ 5፡9) የሚለውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ በመከተል ህዝቡን የማስታረቅ የመምከር መልካም አብነት የመስጠት ክርስቲያናዊ ኃላፊነታችሁን እንደትወጡ እናሳስባለን፡፡
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቁምስናዎች ፣ ት/ቤቶች ፣ የጤና ተቋማት እንዲሁም በማህበራዊና ሐዋሪያዊ ዘርፎች ያላችሁ ሁሉ እና ሌሎችም የሠላም፤ የእርቅ፣ የይቅርታ ሥራዎች እንዲሰሩ ቀዳሚ ኃላፊነት እንዲወስዱ እናሳስባለን፡፡ ገዳማውያን ካህናት ምዕመናን በየአካባቢያቸው የሚፈጠሩ ችግሮች በሠላም፣ በይቅርታ፣ በምህረት ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ከማህበረሰቡ ጋር በቀጥታ በመሳተፍ በመደገፍ እንድትሠሩ እናሳስባለን፡፡ በቤተክርስቲያን የሚደረጉ ስብከቶችና አስተምህሮዎች ሁሉ ሠው ሁሉ እኩል ክቡር እንደሆነ የዘር ልዩነቶች የእግዚአብሔር ድንቅ ስጦታ እንጂ የመለያያ ምክንያቶች እንዳልሆኑ የሚያሳዩ እርቅን፣ ሠላምን፣ ፍቅርን፣ መተሣሠብን ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ እናሳስባለን፡፡ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ሁላችሁ የምታስተምሩት እውነት ህይወትም ኑሩት፡፡
የኃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች በያለንበት በጋራም ይሁን በተናጠል በእውነት በአስታራቂነት መንፈስ ሕዝባችንን ማገልገል ቅድሚያ ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊነት እንጂ ብሔርተኝነት መስበክ ለሕዝባችን አይጠቅመንምና የተሻለውን ሁሉ እንምረጥ፡፡
የመገናኛ ብዙኃንም ችግሮችን በሚያባብሱ በሚያወሳስብ መንገድ ሣይሆን ፍቅርንና ሰላምን፣ አንድነትን፣ እርቅን፣ ይቅርታን በሚያሠርፁ ፕሮግራሞች እንዲያተኩሩ እናሳስባለን፡፡
ካቶሊካውያን ምዕመናን እንዲሁም ቤተሰቦች በእምነታችሁ በርትታችሁ ዘረኝነትን ተጠይፋችሁ ‹‹ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ስለሆናችሁ በአይሁዳዊና በግሪካዊ በአገልጋይና በጌታ በወንድና በሴት መካከል ምንም ልዩነት የለም›› ገላ 3፡28 የሚለው የጳውሎስ መልእክት አንግባችሁ ያለልዩነት ሁሉንም የሰው ልጅ በፍቅር እንድታቅፉና ለሌሎች መልካም ምሣሌ ትሆኑ ዘንድ ክብሩን ትቶ ወደ ዓለም የመጣው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ እንድትከተሉ እናሳስባችኋለሁ፡፡ በየቤታችሁ ጌታሆይ የሠላም መሣሪያ እንድሆን አድርገኝ የሚለው የቅዱስ ፈራንሲስኮስ ጸሎት ቀንና ማታ እንዲፀለይ እንጠይቃለን፡፡ ካቶሊካውያን ቤተሰቦች በቤታችሁ ለልጆቻችሁ ዘረኝነትን ሣይሆን ፍቅርን አንድነትን እና መከባበርን አስተምሩ፡፡
ካቶሊካውያን ‹‹ያለኝ ይበቃኛል›› በሚል ክርስቲያናዊ መንፈስ እየተመራችሁ በወዛችሁ ለፍታችሁ በታማኝነት ሠርታችሁ እንድትኖሩ በእግዚአብሔር መንፈስ እንድትመሩና ከሙስና እና ከኃጢአት ራሳችሁን እንድትለዩ እናሳስባለን፡፡
ወጣቶቻችን ለሀገራችን ዕድገት ለሠው ልጅ መብት መከበር ትልቅ ሚና ይጫወታሉና በጥንቃቄና በማስተዋል በመንፈሳዊ ህይወት በሥነምግባር አንፀን ኃላፊነታቸውን በተገቢው መልኩ እንዲወጡ ልናግዛቸው ፤ ልናሰለጥናቸው እና ልናበቃቸው ይገባል፡፡ የካቶሊክ ት/ቤቶቻችን የሰው ልጅ በሞራል በመንፈሳዊ ህይወት በአእምሮና በስነልቦና የሚበለፅግባቸው ቦታዎች እንዲሆኑና በዚህም ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ እናሳስባለን፡፡ የተወደዳችሁ ወጣቶች የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት እና የቤተክርስቲያን አስተምህሮ በልባችሁ ውስጥ አሳድራችሁ በያላችሁበት በትምህርትም ይሁን በሥራ ቦታችሁ በሥነምግባር እና በሞራል እየተመላለሳችሁ ሌሎችን በፍቅር የምትቀበሉና በማስተዋልና በእርጋታ ነገሮችን በመመልከት ህይወታችሁን እንድትመሩ ከጥፋት እራሳችሁና ወገኖቻችሁ እንድትጠብቁ እናሳስባችኋለን፡፡
ኢየሱስ በፍትህ የሚያስተዳድር የሠላም አለቃ ህዝቦችን አንድ የሚያደርግ ታላቅ መሪ ነው፡፡ በኃይማኖት ተቋማት በማህበራዊ በፖለቲካ እና ፤ በመንግሥት ተቋማት በመሪነት የምንገኝ ሰዎች ህዝቦችን በፍትህና በእውነት የምናስተዳድር ሕዝቦችን የምናስተሳስር እና ወደ አንድነት የምናመጣ የራሳችን ክብርና ጥቅም ሳይሆን የህዝቦችን ክብርና ጥቅም የምናስቀድም እንድንሆን ኢየሱስ ሁላችንም ይመክረናል፡፡
በመጨረሻም በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች መካከል የተጀመረው የአብሮነት ጉዞ በዘላቂነት እንዲቀጥል ሕዝቦች በይቅርታ መንፈስ እንዲመላለሱና በተለይ ደግሞ በሁለቱ ሀገሮች የሚገኙ ካቶሊካውያን በልዩ መተሳሰብ ቤተክርስቲያናቸውን በጋራ እንዲያሳድጉ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እናሳስባለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!!

ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ
ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን
የአትዮጵያ ካቶሊካውያን ጳጳሳት ጉባዔ ፕሬዚዳንት
አዲስ አበባ
 

22 December 2018, 18:17