ፈልግ

የታኅሣሥ 14/2011 ዓ.ም ዘብርሃን (ዘስብከት 2ኛ) እለተ ሰንበት አስተንትኖ የታኅሣሥ 14/2011 ዓ.ም ዘብርሃን (ዘስብከት 2ኛ) እለተ ሰንበት አስተንትኖ 

የታኅሣሥ 14/2011 ዓ.ም ዘብርሃን (ዘስብከት 2ኛ) እለተ ሰንበት አስተንትኖ

ወደ ወገኖቹ መጣ፣ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ይሁን እንጂ ለተቀበሉት እና በስሙ ላመኑት የእዚኣብሔር ልጅ የመሆን መብት ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።


“..ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም"

በእለቱ የተነበበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት

1. 1ዮሐ.1:1-10
2. ሐዋ.26:12-18
3. ሮሜ 13:11-14
4. ዮሐ.1:1-18

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል ዮሐንስ 1፡1-18

ቃል በመጀመሪያው ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ይህም ቃል እግዚአብሔር ነበረ። እርሱ በመጀመሪያው በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ። ሁሉ በእርሱ ተፈጠረ፣ ከተፈጠረው ሁሉ አንድም ነገር ያለ እርሱ የተፈጠረ የለም። በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ይህች ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረች። ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም ብርሃንን ከቶ አያሸንፈውም።
ከእግዚአብሔር የተላከ ስሙ ዮሐንስ የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ በእርሱ ምስክርነት ሰው ሁሉ እንዲያምን ስለብርሃም ምስክር ሆኖ መጣ እንጂ፥ እርሱ ብርሃን አልነበረም። ይህ ብርሃን ወደ ዓለም የሚመጣና ለሰው ሁሉ ብርሃን የሚሰጥ እውነተኛ ብርሃን ነበረ።
በእርሱ ዓለም ነበረ። ዓለምም የተፈጠረው በእርሱ ነው፣ ዓለም ግን አላወቀውም። ወደ ወገኖቹ መጣ፣ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም። ይሁን እንጂ ለተቀበሉት እና በስሙ ላመኑት የእዚኣብሔር ልጅ የመሆን መብት ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም።
ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን። ዮሐንስ ስለ እርሱ መሰከረ እንዲህም ብሎ ጮኸ። ከእኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ከእኔ በፊት ነበረና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል፤ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነበረ። እኛ ሁላችን ከሙላቱ ተቀብለን በጸጋ ላይ ጸጋ ተሰጥቶናልና ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና፤ ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ። መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ ይሁን እንጂ በእግዚኣብሔር ርብ ዘንድ ያለው አንድ ልጁ ብቻ ገልጦታል።

የታኅሣሥ 14/2011 ዓ.ም ዘብርሃን (ዘስብከት 2ኛ) እለተ ሰንበት አስተንትኖ

የተከበራችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ። በዛሬው የስርዓተ አምልኮ አቆጣጠር ደንብ መሰረት በሁለተኛው የስብከተ ገና ሳምንት ላይ እንገኛለን። በዚህ ለገና በዓል ዝግጅት በሚደረግበት ሁለተኛ ሳምንት ላይ የተነበበው ወንጌል እግዚአብሔር በሕዝቡ መሐል ብርሃን ሆኖ ስለመኖሩና የሰውን ከብርሃን ይልቅ ጨለማን የመምረጥ ቀጣይ ዝንባሌ ግልጽ በሆኑ ቃላት ይነግረናል።
"ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር። በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።" ይላል ወንጌላችን። ጨለማ በራሱ ያለ ነገር ሳይሆን የብርሃን ያለመኖር መሆኑን እናውቃለን። ጨለማን ስንፈልግ ማድረግ የምንችለው ነገር የብርሃን ምንጭን ማስወገድ ነው፤ በተቃራኒው ደግሞ ብርሃን እንዲሆን ከፈለግን የብርሃን ምንጭን ማግኘት ነው። ማንም ሰው በቀጥታ የክርስቶስ ተቃራኒ መሆን አይፈልግ ይሆናል፤ ነገር ግን ክርስቶስን በዕለታዊ ሕይወቱ ካልተቀበለ ሌላ ሦስተኛ ምርጫ የለምና ሊቀበል የሚችለው ጨለማን ብቻ ነው።
ክርስቶስን በብርሃን መስሎ በመናገርና ይህን ብርሃን ያልተቀበሉ ጨለማን እንደመረጡ ዮሐንስ ወንጌላዊው ያሳየናል። ብቸኛ የዓለም ብርሃን የሆነውን ክርስቶስን ያልተቀበለ ያለው ብቸኛ ምርጫ ወይም በተሻለና ግልጽ አባባል ብቸኛ ግዴታው ጨለማን መቀበል ነው። ይህን ጨለማ የሰው ልጅ በሕይወቱ ውስጥ እንዴት ይለማመደዋል ብለን የምናስብ ከሆነ እያንዳንዳችን ዕለታዊ ሕይወታችን ውስጥ ገብተን ከክርስቶስ ፈቃድ ጋር የማይሰማማ አናኗሮቻችንን መመርመሩ ጥሩ ነው። ሥጋዊ ብርሃን ውስጥ ብንመላለስም ውስጣዊ ብርሃናችንን ያጣን ልንሆን እንችላለንና ዛሬም ስለክርስቶስ ብርሃናዊነት ሲነገር ውስጣችንን በርሱ ማብራት ይጠበቅብናል።
ቁ.18 ላይ "እግዚአብሔርን ያየው ከቶ ማንም የለም፤ ይሁን እንጂ በእግዚአብሔር አብ ዘንድ ያለው አንድ ልጁ ብቻ ገልጦታል" ይላል። እግዚአብሔር እንደ ሰው በቦታና በጊዜ ተገድቦ ሊታይ ባህርይው ወይም ተፈጥሮው አይደለም። ግን ሁሉን ቻይ ነውና ራሱን በሚገባን መልክ ለመግለጥ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ በአንድ ልጁ ሥጋን ለበሰ። ይህን እውነት በዘወትር ሕይወታችን ካሰብነው ደግሞ ብዙ ትርጉም ይኖረው ይሆናል። ማለትም እግዚአብሔር ራሱን የሚገልጥበትን መንገድና እኛን የሚጠራበትን ሁኔታዎች እንድናስተውል ያግዘናል። ማንም እግዚአብሔርን በቀጥታ አይቶ በሕይወት ሊኖር የሚቻለው ሥጋ ለባሽ የለም፤ ክርስቶስ ግን አባቱን ተረከልን፣ በተለያየ መልክም እንደሚገለጥ አሳየን።
እንዲሁም "እርሱም ወደ ወገኖቹ መጣ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም" ሲል ቶሎ ብለን ልናስብ የምንችለው ነገር ካልተቀበሉት ምኑን ወገኑ ሆኑ የሚል ሊሆን ይችላል። በርግጥ እነርሱ አድርገውታል ማለትም አልተቀበሉትም፤ ጥያቄው ግን ዛሬ ለኛ ነው፤ የጥምቀት ጸጋን ተቀብለን ክርስቲያኖች በመባል የእርሱ ወገን ሆነን ለደኅንነት ማለትም ሕይወታችንን ለርሱ እንድናስገዛ ሲጠራንና ሲጋብዘን ላለመቀበል በቀጠሮ የምናሰለቸው ከሆነ አንድ ዓይነት ታሪክ እንደግማለን:- ወገኑ ነን ግን አልተቀበልነውም።
ክርስቶስ በአካል በየዕለት ሕይወታችን ውስጥ እኛ በምንፈልገው መልክ ቢገለጥ ኖሮ ለመቀበሉ እንሽቀዳደም ነበር። ግን በተለያየ መልክ ዛሬም ወደ ወገኖቹ ማለትም ወደ እኛ በስሙ ወደተጠራነው መምጣቱን አላቋረጠም እኛም እርሱን ካለመቀበል አልሰነፍንም። ይህ ነገር በቀጣይነት እንዳይጠናወተንና ከውስጣዊ ጨለማ ጋር መኖርን እንዳንመርጥ የዛሬው ወንጌል ለውሳኔ ያነቃቃናል።
"ይሁን እንጂ ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት ሰጣቸው" ሲል ይህ ለሁላችን የተደረገ ግብዣና ጥሪውን ተቀብለን ስንመልስ የብርሃን ልጆች የመሆን መብታችንን መኖር እንደምንችል ያሳያል። ብርሃን ወይ ጨለማን፤ የእርሱ ልጅነትን ወይም የጨለማው ባላባት (የሰይጣን) ልጅነትን መምረጥና መለማመድ ከኛ በኩል በሚደረገው ምርጭ ስለሚወሰን ምርጫችንን መኖር በእጃችን ነው። ይህ ምርጫ አንዴ ተደርጎ በቃ የሚባል ዓይነት ሳይሆን በቀን ውስጥ በሚቀርቡልን ተደጋጋሚ ምርጫዎች ይወሰናል።
እግዚአብሔር የኛን ዝቅተኝነት በመካፈል የእርሱን ክብር ሊያካፍለን ይህን የገና ጊዜ እንጠቀምበት ዘንድ ሰጥቶናል፤ ሰው ሆኖ በመወለዱ ብዙዎች ሊለዩትና ሊቀበሉት እንዳልፈለጉ ሁሉ ዛሬም በተለያየ መልኩ በመካከላችን ተገኝቶ እኛን ሊያከብረንና ከአእምሮ በላይ የሆነ ሰላሙን በድካም ለታጠረው ማንነታችን ሊሰጠን ይጠብቀናል።
ለሚመጣው ጌታ መንገድን ለማዘጋጀት መጥምቁ እኛን የሚጋብዘንን የለውጥ ጥያቄዎችን ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ እኛን በከፍተኛ ደረጃ ተብትበው የያዙንን የመቀዝቀዝ ስሜት እና ከቸልተኝነት የሚመነጩን የተስፋ መቁረጥ ስሜቶችን ለይተን በማውጣት ኢየሱስ ለእኛ የምያሳየንን ዓይነት ስሜት ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ያንን ስሜት በመላበስ ራሳችንን ለባልንጀሮቻችን ፍላጎቶች በመክፈት ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ክርስቶስ ለእኛ በምያሳየን ዓይነት ስሜት መንከባከብ ይኖርብናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ በችግር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ማገዝ ተገቢ ነው። በኩራት እና በትዕቢት ስሜት በሕይወታችን በተከሰቱት ስህተቶች የተነሳ የቀዘቀዘውን ሕይወታችንን ከወንድሞቻችን ጋር ተጨባጭ በሆነ መልኩ እርቅ በመፍጠር እና ለሰራናቸው ኃጢኣቶቻችን ይቅርታን በመጠየቅ ልንኖር ይገባል። በእርግጥ የእኛን ስህተቶች፣ እምነትን ማጉደላችንን እና አለመታዘዛችንን በትህትና በመቀበላችን የተነሳ የተሟላ መንፈሳዊ ለውጥ ማምጣት እንችላለን።
አማኝ የሚባል ሰው ተጨባጭ በሆነ መልኩ ወንድሞቹን የሚቀርብ ሰው፣ መጥምቁ ዮሐንስ በበራሃ ውስጥ መንገድ እንደ ከፈተ ሁሉ መጥፎ በሚባሉ የሕይወት ገጠመኞች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ሁሉ ተስፋ እንዲያደርጉ መንገድ በማመላከት ሰዎች ከውድቀት እና ከአሰቃቂ ሽንፈት ነጻ ሆነው እንዲኖር ተጨባጭ በሆነ መልኩ የሚሰራ ሰው እርሱ አማኝ የሆነ ሰው ነው ለማለት እንችላለን። አሉታዊ እና አፍራሽ ወደ ሆኑ ነገሮች ተመልሰን መግባት የለብንም፡ የእኛ የህይወት ማዕከል ኢየሱስ እና የእሱ በብርሃን የተሞሉ ቃላት፣ፍቅር እና የእርሱ መጽናኛ በመሆኑ የተነሳ እኛ የአለም አስተሳሰብ መቀበል የለብንም። መጥምቁ ዮሐንስ በወቅቱ የነበሩትን ሰዎች ሁሉ በብርታት፣ በመጸጸት እና በትህትና መንፈሳዊ የሆን አለውጥ እንዲያመጡ ሲጋብዝ እናያለን። ሆኖም ግን እርሱ እንዴት መስማት እንዳለበት ያውቅ ነበር፣ ኃጢአታቸውን ለመናዘዝ እና በኃጢአተቸው ተጸጽተው ከኃጢኣታቸው ለመንጻት በማሰብ ለመጠመቅ ወደ እሱ የሚመጡትን ብዙ ወንዶችና ሴቶችን በርኅራኄ እንዴት ማስተናገድ እንደ ሚገባውም በሚገባ ያወቅ ነበር።
ስለ ህይወቱ የሰጠው ምስክርነት፣ ኑፁዕ የሆነ አዋጅ በማወጁ፣ እውነቱን ለማወጅ ያለው ድፍረት እና ብርታት ለረጅም ጊዜ ሲዘገይ የቆየውን የመሲህ ተስፋዎችን በድጋሚ እንዲለመልም በማድረግ እና ተስፋዎችን እንደገና በማነሳሳት ያደርገው ከፍተኛ ጥረት ተሳክቶለታል። ዛሬም ቢሆን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሙሉ በታላቅ ብርታት የእርሱን ተስፋዎች እንደ ገና ለማለምለም ከሁሉም በላይ ደግሞ የእግዚአብሔር መንግሥት በየቀኑ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየተገነባ እንደ ሚሄድ በመረዳት የእርሱ ትሁት እና ደፋር ምስክሮች እንዲሆኑ ተጠርተዋል።
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከራሳችን በመጀመር በእየለቱ ለእግዚኣብሔርን መንገድ ማዘጋጀት እንችል ዘንድ እንድትረዳን እና የትዕግስት፣ የሰላም፣ የፍትህ እና የወንድማማችነት ዘርን በእየአከባቢያችን መዝራት እና ማሰራጨት እንችል ዘንድ እድትረዳን አማላጅነቷን መማጸን ይገባል።
የቫቲካን ሬዲዮ አማርኛ ክፍል


 

22 December 2018, 17:37