ፈልግ

የታኅሳስ 07/2011 ዓ.ም ዘስብከት 1ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የታኅሳስ 07/2011 ዓ.ም ዘስብከት 1ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የታኅሳስ 07/2011 ዓ.ም ዘስብከት 1ኛ እለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ሰው እግዚአብሔርን ሲንቅ እግዚአብሔር ሰውን ሲያከብር!

የታኅሳስ 07/2011 ዓ.ም እለተ ሰንበት የተነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት

1.     1ዮሐ.:1-14

2.     ዕብ.1:1-14

3.     2ጴጥ.3:1-9

4.     ሐዋ.3:17-26

5.     ዮሐንስ 1፡ 44-51

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል፦

በማግሥቱ ኢየሱስ ወደ ገሊላ ለመሄድ ፈለገ፣ ፊልጶስንም አገኘውና ተከተለኝ አለው።  ፊልጶስ እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ የቤተ ሳይዳ ከተማ ሰው ነበረ።  ፊልጶስ ናትናኤልን አግኝቶ “ሙሴ በሕግ መጽሐፍ ነቢያትም በትንቢት መጽሐፍት ስለ እርሱ የጻፉትን የዮሴፍን ልጅ የናዝሬቱን ኢየሱስን አግኘነው አለው። ናትናኤልም ከናዝሬት መልካም ነገርከቶ ሊገኝ ይችላልን? አለው። ፊልጶስም መጥተህ እይ” አለው።  ኢየሱስ ናትናኤልን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ “እነሆ ተንኰል የሌለበት በእውነተኛ የእስራኤል ሰው !” በማለት ስለ እርሱ የናገረ።  ናትናኤልም እንዴት አወከኝ”?  አለው። ኢየሱስም  “ፊልጶስ ሳይጠራህ በፊት   ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነህ አይቼሃለሁ” ሲል መለሰለት።  በዚህን ጊዜ ናትናኤል “መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” አለው። ኢየሱስም መልሶ ከበለስ ዛፍ ሥር ሆነ አይቼሃለሁ ስላልኩ ነውን? ከዚህ የሚበልጡ ነገሮችን ገና ታያለህ” አለው። (ዮሐንስ 1፡44-51)

 

የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የተከበራችሁ የእግዚኣብሔር ቤተሰቦች እና በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

የዛሬው እለት ሰንበት ዘስብከት 1ኛ በመባል ይጠራል። ስብከተ ገና ኢየሱስ በዓለም ታሪክ ውስጥ በመግባት የዓለምን የቀን አቆጣጠር ወደ ዓመተ ምሕረት እንደቀየረው ሁሉ የእኛንም ሕይወት በምሕረቱ ሊሞላት በእርሱ በኩል ሁሌም ዝግጁ መሆኑን የሚሰበክበት ወቅት ነውና የዛሬው ሰንበት "ዘስብከት" በመባል ይጠራል።

በዚህ የስብከተ ገና ወቅት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን ከመበሩ ከሦስት ሳምንታት በፊት ለዚህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን የሚሆን መንፈሳዊ ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት ሲሆን በእነዚህ ሳምንታት ምዕመኑ በጸሎት፣ በአስተንትኖ፣ በኖቪና እና በመሳሰሉ መንገዶች መንፈሳዊ ዝግጅቶችን በማድረግ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት ቀን ለማክበር የሚዘጋጁበት ወቅት ነው። በእነዚህ የስብከተ ገና ሳምንታት ውስጥ “ኢየሱስን ለመቀበል ያስችለን ዘንድ ልባችንን መክፈት ይኖርብናል”።

ዛሬ የሚጀመረው የስብከተ ገና ሳምንት ስርዓተ አምልኮ ለገና በዓል የምያዘጋጃን ወቅት ሲሆን ኢየሱስን ለመቀበል ልባችንን መክፈት እንችል ዘንድ ይጋብዘናል። በስብከተ ገና ወቅት እየተጠባበቅን የምንገኘው ጌታ የተወለደበትን ቀን ብቻ አይደለም፡ ነገር ግን በተጨማሪም ክርስቶስ ዳግመኛ በክብር የሚመጣበትን ቀን በጉጉት ነቅተን እንድንጠባበቅ ጭምር ይጋብዘናል- እርሱ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ተመልሶ በሚመጣበት ወቅት ከእሱ ጋር ለመገናኘት ያስችለን ዘንድ የሚረዱንን ተገቢ የሆኑ ምርጫዎችን በማድረግ በብርታት በእርሱ ፊት እንቆም ዘንድ የሚረዱንን ተግባሮች በመፈጸም ተዘጋጅተን የምንጠባበቅበት ወቅት ነው። የገናን በዓል ስናስታውስ፣ ክርስቶስ በክብር የሚመጣበትን ቀን በምንጠባበቅበት ወቅት፣ እኛም ከእርሱ ጋር በግለሰብ ደረጃ ለመገናኘት በመዘጋጀት፣ ክርስቶስ በሚጠራን ወቅት ለእርሱ ጥሪ መልስ ለመስጠት የምንዘጋጅበት ወቅት ነው። በእነዚህ ሦስት ሳምንታት ውስጥ ከተገለለና ከተለመደ የሕይወት ጎዳና እንድንወጣ እና በአዲስ ጎዳና ላይ ተስፋ በማድረግ እንድንራመድ ጥሪ የሚያደርጉልን ሳምንታት ሲሆኑ በተጨማሪም የወደፊቱን ተስፋ በማለምለም የወደፊቱ ኑሮዋችንን በአዲስ መልክ ለመኖር የምናልምበት እና በዚህ መልክ እንድንኖር ጥሪ የሚያቀርብልን ወቅት ነው።

ከዛሬ ቀን ጀምሮ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን የገና በዓል እስከ ምናከብርበት ቀን ድረስ ያሉትን የስብከተ ገና ሳምንታት መኖር የሚገባን ተግቶ በመጠበቅ እና በጸሎት ሊሆን ያስፈልጋል። ተግቶ መጠበቅ እና መጸለይ!! ውስጣዊ የሆነ እንቅልፍ የሚከሰተው ኑሮዋችንን ራሳችንን ብቻ ባማከለ መልኩ በምንኖርበት ወቅት እና በሕይወት ውስጥ በምያጋጥሙን ችግሮች፣ ደስታዎች፣ ሕመሞች ውስጥ ራሳችንን በራሳችን ቆልፈን ስንቀምጥ ነው። እናም ይሄ ያደክመናል፣ ይህ ስልቹዎች እንድንሆን ያደርገናል፣ ይህ ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርገናል።

የዛሬ ቅዱስ ወንጌሉ የሚናገረው ይህንኑ ነው፣ ደንዝዘን እና ሰንፈን እንዳንቀመጥ ይጠይቀናል። ይህ የስብከተ ገና ወቅት ከራሳችን ውጭ በመሄድ ሌሎችን እንድንመለከት፣ እራሳችንን እና ልባችንን በማስፋት፣ ለሕዝቦች እና ለወንድሞቻችን  ፍላጎት ልባችንን በመክፈት  በአዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ያላቸውን ምኞት እውን ለማድረግ እንድንሠራ ይጋብዘናል። ይህም በረሃብ፣ በፍትሕ መዛባትና በጦርነት የተሠቃዩ የብዙ ሕዝቦች ፍላጎት እና ምኞት ነው፡ የድሆች፣ የደካማዎች  እና የተተው ወይም የተረሱ ሰዎች ምኞት ነው። ይህ የስብከተ ገና ወቅት ህይወታችንን እንዴት እና ለማን መክፈት እንዳለብን በማሰብ ግልጽ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንድንችል ልባችንን ለመክፈት እድሉን ይፈጥርልናል።

በዚህ በስብከተ ገና ወቅት ጌታን በመልካም ሁኔታ ላይ በመሆን ለመጠባበቅ ከሚያስችሉን ባሕሪያት መላከል በሁለተኛ ደረጅ የሚጠቀሰው ደግሞ ጸሎት ነው። “ይህ ሁሉ መሆን በሚጀምርበት ጊዜ ደኅንነታችሁ ቀርቦአልና ቀና ብላችሁ ወደ ላይ ተመልከቱ” (ሉቃ 21፡28) በማለት የሉቃስ ወንጌል ያሳስበናል። ይህም የምያመልክተው አስተሳሰባችንን እና ልባችንን በኢየሱስ ላይ በማድረግ ነቀተን እንድንጸልይ ነው። አንድ ነገር ወይም አንድን ሰው የምንጠብቀው ተነስተን በመቆም ነው። እኛም በዚሁ መልክ ኢየሱስን በምንጠባበቅበት ወቅት በጸሎት መንፈስ በመሆን እርሱን መጠበቅ ይኖርብናል፣ ይህም ተግባር በቀጥታ ተግቶ ከመጠበቅ ጋር ይያያዛል። ኢየሱስን ለመጠበቅ፣ ራሳችንን በራሳችን ሳንዘጋ ሌሎችን ነቅተን ለመጠበቅ እንችል ዘንድ እና በትጋት ለመቆም ያስችለን ዘንድ መጸለይ ያስፈልጋል። ነገር ግን እኛ የገናን በዓለ ለማክበር እንዲሁ የፍጆታ ቁሳቁሶችን ብቻ በመግዛት የተጠመድን ከሆነ፣ ይህንን ነገር ወይም ያንን ነገር ለማድረግ፣ ይህንን ብገዛ ወይም ያንን ብገዛ እያልን ዓለማዊ የሆነ በዓል ለማክበር በምንሞክርበት ወቅት በዚህ አኳኋን እያለን ኢየሱስ በሚመጣበት ወቅት እኛን አልፎ ይሄዳል፣ እኛም እርሱን ልናገኘው አንችልም። እኛ ግን ኢየሱስን ለመጠበቅ እንፈልጋለን፣ በጸሎት መንፈስ በትዕግስት ልንጠብቀው እንፈልጋለን፣ ይህም በቀጥታ ተግቶ ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ነው።

በዛሬው ቅዱስ ወንጌል ውስጥ በፊልጶስ፣ በናትናኤልና በኢየሰኡስ መካከል የተደረገውን ንግግር እናገኛለን። ፊልጶስ በኢየሱስ ከተጠራ በኋላ ናትናኤልን ሲያገኘው፦ "ሙሴ በሕግ መጽሐፍ ነቢያትም በትንቢት መጻሕፍት ስለ እርሱ የጻፉለትን አገኘነው፤ እርሱም የዮሴፍ ልጅ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው" አለው። ናትናኤል ግን "ከናዝሬት መልካም ነገር ከቶ ሊገኝ ይችላልን?" አለው። ፊልጶስም "መጥተህ እይ" አለው። ኢየሱስ ናትናኤል ወደ እርሱ ሲመጥ አይቶ "እነሆ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው!" ሲል ስለ እርሱ ተናገረ(ቁ.44-47)። ጊዜ ሰጥቶ በማስተዋል ላሰበው ሰው በእዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ በተለያየ መልኩ ይሁን እንጂ ዘወትር የሚደጋገም እውነት አለ። እግዚአብሔር ደካማ ሆኖ፣ በሥጋ ሰው ሆኖ፣ በማይመስለን መልኩ ሲገለጽ ሰው ደግሞ ሲንቀውና ሲጠራጠረው ይታያል። "ከናዝሬት መልካም ነገር ከቶ ሊገን ይችላልን?" - እግዚአብሔር ናዝሬትን መረጣት፤ በማይመስልና በሚናቅ ነገር መሥራት ልማዱ የሆነ አምላክ ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬም ይህን እውነት ያደርጋል።

ክርስቶስ የሰው ልጅን ለማዳን ሰው መሆን ነበረበትና ይህንን ለመተግበርም ከኃጢአት በስተቀር እንደሰው ተቆጠረ፣ ተወለደ፣ ተናቀ፣ ተንገላታ፣ ተራበ፣ ተጠማ፣ ተሰደደ፣ ታማ፣ ለሌባና ለነፍሰ ገዳይ የሚደረግ ፍትሕና እንክብካቤ ተነፍጎት ተሰቀለ - ሞተ። እሱ ፍጹም ሰው ነበርና እያንዳንዷ ስቃይ እኛን ከምታሰቃየን በላይ ብዙ እጥፍ እንደምታሰቃየው መገመቱ ከባድ አይደለም።

ይህ በክርስቶስ ላይ የተፈጸመው እውነታ "በአንድ ወቅት" የነበረ ክሥተት አይደለም። እግዚአብሔር ዛሬም ደካማ ነገሮችን የመምረጥ አሠራሩን አልቀየረም፤ የሰው ልጅም የእግዚአብሔር ድካም በሆኑ ነገሮች ውስጥ የሚገኘውን ጸጋ መናቁን አላቋረጠም። የሚገርመው ነገር ደግሞ ደካማው ኃያሉን ሲንቅና ኃያሉ ግን ደካማውን ሲያከብረው ማስተዋሉ ነው። ናትናኤል ስለ ኢየሱስ "ከቶ ምን መልካም ነገር ይገኛል" ሲል ኢየሱስ ግን ስለ ናትናኤል "እነሆ ተንኮል የሌለበት እውነተኛ የእስራኤል ሰው" አለው።

የዛሬው ቅዱስ ወንጌል እኛ ስንንቀውና ስናርቀው እርሱ ሲጋብዘን፣ ሲያከብረን እና ሲቀረብን ያሳያል። የእሱ አካል የሆነችውና እሱ ፈቅዶ በተለመደ አመራረጡ በደካማ ሰዎች ላይ የቆረቆራትን ቤተ ክርስቲያንን በተለያየ መልኩ ለማናቅና ለማወረድ ጥረት ባደረግን ቁጥር ለንስሐና ለቅድስና ዘወትር በራሷ በኩል ይጋብዘናል።

ይህን ሀሳብ የእሱን መወለድ ለማክበር በምናደርገው ዝግጅት ሂደት ውስጥ በጸሎት እያሰላሰልን ዛሬም እግዚአብሔር ደካማ በሚመስሉ ነገሮች የሚያደግልንን ጥሪ ተቀብለን በክርስትና ሕይወት ውስጥ ዳግም የምንወለድበትን ጸጋ አናሳልፍ።

ወደ ኢየሱስ እንድንቀርብ የምታደርገን፣ በጸሎት እና በትዕግስት የመጠባበቅ ተምሳሌት የሆነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠንን ተስፋ መጠባበቅ የምንችልበትን ኃይል እንድትሰጠን፣ በታሪክ ሂደት ውስጥ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ታማኝ በመሆን እና ምንም እንኳን የሰው ልጆች በስህተቶች ተሞልተው የሚኖሩ ቢሆንም ቅሉ፣ ነገር ግን የእርሱን መለኮታዊ ምሕረት በትዕግስት መጠባበቅ እንችል ዘንድ አማላጅነቷን መማጸን ያስፈልጋል። የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርልን።

በቫቲካን ሬዲዮ የአማርኛ ክፍል የተዘጋጀ

 

 

15 December 2018, 15:43