ፈልግ

የሕዳር 23/2021 ዓ.ም ሰንበት ዘምኩራብ (ዘአስተምሮ 3ኛ) የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የሕዳር 23/2021 ዓ.ም ሰንበት ዘምኩራብ (ዘአስተምሮ 3ኛ) የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ 

የሕዳር 23/2021 ዓ.ም ሰንበት ዘምኩራብ (ዘአስተምሮ 3ኛ) የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዛሬው ወንጌል ውስጥ የተካተቱት ሁለት ክንዋኔዎች ማለትም፤ ኢየሱስ የማዕበልን ሞገድ ጸጥ ማስባሉና በአጋንንት የተያዙ ሰዎችን ማዳኑ፤ ነገሮች ሁሉ ከምናመልከው አምላክ ኃይል በታች መሆናቸውን በማሳየት የክርስቶስ ተከታይነታችን በነገሮች ገደብ ሳይሆን በርሱ ህላዌ ስለመሆኑ ያለንን እምነት እንድንመረምር ያግዙናል።

የእለቱ ምንባባት

1.     ዕብ.12:25-29

2.   ያዕ.3:4-12

3.   ሐዋ.21:27-40

4.     ማቴ.8:23-34

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል ማቴ 8፡23-34

ወደ ታንኳም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱ ተከተሉት።  እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉ አስነሡት።  እርሱም። እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ።  ሰዎቹም። ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ ተደነቁ።

ወደ ማዶም ወደ ጌርጋሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፥ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ወጥተው ተገናኙት፤ እነርሱም ሰው በዚያ መንገድ ማለፍ እስኪሳነው ድረስ እጅግ ክፉዎች ነበሩ።  እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ።  ከእነርሱም ርቆ የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማራ ነበር። አጋንንቱም። ታወጣንስ እንደሆንህ፥ ወደ እሪያው መንጋ ስደደን ብለው ለመኑት። ሂዱ አላቸው። እነርሱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ሄዱና ገቡ፤ እነሆም፥ የእሪያዎቹ መንጋ ሁሉ ከአፋፉ ወደ ባሕር እየተጣደፉ ሮጡ በውኃም ውስጥ ሞቱ። እረኞችም ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ሄደው ነገሩን ሁሉ አጋንንትም በአደሩባቸው የሆነውን አወሩ። እነሆም፥ ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ሊገናኝ ወጣ፥ ባዩትም ጊዜ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት።

 

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በእግዚአብሔር ፊት የመገኘት ፍቅር

የዛሬው ወንጌል ውስጥ የተካተቱት ሁለት ክንዋኔዎች ማለትም፤ ኢየሱስ የማዕበልን ሞገድ ጸጥ ማስባሉና በአጋንንት የተያዙ ሰዎችን ማዳኑ፤ ነገሮች ሁሉ ከምናመልከው አምላክ ኃይል በታች መሆናቸውን በማሳየት የክርስቶስ ተከታይነታችን በነገሮች ገደብ ሳይሆን በርሱ ህላዌ ስለመሆኑ ያለንን እምነት እንድንመረምር ያግዙናል።

ለሰው ልጅ ህልውና ወሳኙ ነገር የእግዚአብሔር ህልውና በሕይወታችን ያለው ቦታ ነው። ደቀ መዛሙርቱና ኢየሱስ በባሕር ላይ ሳሉ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ ታላቅ መናወጥ በሆነበት ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደርሱ ቀርበው። "ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን" እያሉ ሲያስነሡት "እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ?" በማለት ከማዕበሉ በፊት እነርሱን የገሰፃቸው ምናልባት ከርሱ ህልውና ወይም በመካከላቸው መገኘት በላይ የርሱን ሥራ ስለፈለጉ ይመስላል።

ይህ ዓይነት ግንዛቤ በመንፈሳዊ ጉዟችን ላይ መዘዝ የሚያስከትል ነገር ነው። ክርስትናችን በእግዚአብሔር ሥራ ወይም እሱ በሚያደርግልን ብለን በምናስባቸው ነገሮች መጠን ከሆነ፤ በተወሰነ ደረጃ ላይ ነገሮች በራሳቸው መሳካት የጀመሩልን ሲመስለን እግዚአብሔርን ከሕይወታችን የማስወጣት ድምዳሜ ላይ ልንደርስ እንችላለን። ወይም በተቃራኒው አላደረገልንም ብለን ስናስብ ሌላ "አምላክ" ፍለጋ እንሄዳለን። በጠባብ እቅዳችን ውስጥ እግዚአብሔር የገባ ሲመስለን እውነተኛውን አምላክ አገኘን ብለን እናውጃለን። እውነቱ ግን ያገኘነው አምላክን ሳይሆን  የፈለግነውን ነገር ነው ። በርሱ ሰፊ እቅድ ውስጥ ራሳችንን ማስገባት ሲከብደን እሱን በኛ ደካማ እቅድ ውስጥ ለማስገባት እንጥራለን።

ስለዚህ ክርስቶስ የተኛ በመሰላቸው ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ተረበሹ። የእርሱ በመሃላቸው መገኘት ማመንን ሳይሆን እሱን "ቀስቅሰው" ተአምር ማድረግ መጠየቅን ወሰኑ። ማዕበሉን ጸጥ ማሰኘቱ የኢየሱስ ህልውና ማረጋገጫ እስኪመስል "ቀሰቀሱት"። እሱ ስለነርሱ የሚያስብ ሳይሆን እሱን ስለነርሱ አሳስበውት የሚያስብ አስመሰሉት። ክርስትናን በእግዚአብሔር ፊት የመገኘትን ፍቅርና እውቀት ማስፋፋትና መኖርን ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት መጮህ አስመሰሉት።

የእግዚአብሔር ህልውና በሕይወቱ መተከሉን የማያምን ሰው እግዚአብሔር "ጸጥ" ያለ ሲመስለው የመኖሩ መሠረት የተናወጠ ይመስለዋል። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር መኖሩን ለማረጋገጥ የማስረጃ ውጫዊ ምልክትን ይሻል። ይህንንም በማድረጉ ሳይታወቀው ለእምነት እንደ ሳይንስ አካላዊና ግዙፍ ማስረጃ መሰብሰብን ይጀምራል። ቶማስ ሜርተን "እግዚአብሔርን በደንብ የማናውቀው ከሆነ እሱ የሌለ በሚመስለን ሰዓት ይበልጥ በሕይወታችን እንደሚገኝ አንገነዘብም" ይላል። የእምነት ሰው እግዚአብሔር አለ ብሎ በሚያስብበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን የሌለ በሚመስልበትም ሰዓት ሁሉ የአምላኩን ህልውና የሚይምን ነው።

ደቀ መዛምርቱ ጥያቄያቸው በራሱ ምንም ክፋት ያለው አይመስልም "ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን" ነው ያሉት። እንደዚህ ብሎ ወደ እግዚአብሔር መጸለይ የእምነት ሰው መሆን ምልክት እንጂ እንዴት የእምነተ ቢስነት ወይም ጎዶሎነት ሊሆን ይችላል? "ጌታ ሆይ! ይህን አድርግልኝ፤ ያን ስጠኝ..." ብለን የጸለይናቸውና የምንጸልያቸው ሁሉ ትርጉም የለሽ ሊሆኑ ይችል ይሆን የሚል ስጋት ይፈጥራል። ክርስቶስ ግን "እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ?" ብሎ ሲመልስላቸው የሚያስተላልፈው መልእክት የኔ ይህን ወይም ያን ማድረግ ሳይሆን የእኔ ከናንተ ጋር መኖር ትልቅ ነገር መሆኑን አታውቁምን የሚል ነው።

ስለዚህ የርሱ ከኛ ጋር መኖር የምንፈልጋቸው ነገሮች ከመሆናቸው ወይም ካለመሆናቸው በላይ በሕይወታችን ትልቅ እፎይታን መስጠት አለበት። ስላደረገልኝ የማምነው ከሆነ "እምነት" የምንለውን ትርጉማችንን እናጢነው። ኢየሱስ ሆይ እኔ ያልኩትን ማግኘት ሳይሆን በሕይወቴ ውስጥ የአንተ ህልውና፤ ያንተ መገኘት ለኔ በቂ ነው እንበለው።

ምንጭ፡በኢትዮጲያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የሲታዊያን መነኮሳት ድሕረ ገጽ ከሆነው www.ethiocist.org ላይ እ.አ.አ. በታኅሣሥ 01/2018 ዓ.ም ከቀኑ 04፡19 ላይ የተወሰደ።

 

 

01 December 2018, 10:42