ፈልግ

Vigil for victims of synagogue shooting Vigil for victims of synagogue shooting 

የሰሜን አሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ዘረኝነትን በጽኑ እንደሚቃወሙት ገለጹ።

“ዘረኝነት ባሕላችንን እየጎዳው ይገኛል፣ በክርስቲያን ልብ ውስጥም ቦታ የለውም፣ ሕዝባችን ቃል የተገባለትን የነጻነትን፣ የእኩልነትንና የፍትህን ቃል ኪዳን በሚገባ እንዲያውቅ የሚያስችለው እውነተኛ የልብ መለወጥ እንዲኖር ያስፈልጋል”።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት ዘረኝነትን በጽኑ እንደሚቃወሙትና ሕዝባቸውም ዘረኝነትን ለማስወገድ፣ ዘረኝነትም ካስከተለው ጥላቻ ማገገም እንዲቻል ልቡን በስፋት እንዲከፍት አሳስበዋል። የሰሜን አሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት “ልባችንን በስፋት መክፈት ለዘላቂ ፍቅር አስፈላጊ ጥሪ ነው” በሚል ርዕስ ለሕዝቡ ሐዋርያዊ መልዕክት ይፋ ማድረጋቸው ታውቋል። እሑድ ጥቅምት 4 ቀን 2011 ዓ. ም. ጠቅላላ ጉባኤ ያቸውን ያካሄዱት የሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን በሙሉ ድምጽ ማጽደቃቸው ታውቋል።

ብጹዓን ጳጳሳት በሐዋርያዊ መልዕክታቸው መግቢያ ላይ እንደገለጹት ዘረኝነት ሰዎችን በቆዳ ቀለማቸው ወይም በጎሳ ልዩነታቸው የተነሳ አንዱን ከሌላው አሳንሶ መመልከት እንደሆነ አስረድተው በዚህ የተነሳ በሰዎች መካከል አንዱ በሌላው ላይ የበላይነት ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል ብለው ይህም ፍትህን እንደሚያጓድል አስረድተዋል። በክርስትና መንገድም ያየነው እንደሆነ ለጎረቤታቻችን ያለን ፍቅር እንዲጠፋ ያደርጋል ብለዋል። ሁሉም ሰው በእኩልነት፣ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጥሯል የሚለውን መሠረታዊ እውነትን ይቃረናል ብለዋል። በሰሜን አሜሪካ የሚንጸባረቁ የተለያዩ የዘረኝነት ዓይነቶችንም በጥንቃቄ የተመለከቱት ብጹዓን ጳጳሳቱ በሰሜን አሜሪካ የሚታይ ዘረኝነት ከመጀመሪያ ጀምሮ የነበሩ አገር በቀል አሜሪካውያን፣ አፍሮ አሜሪካውያን እና የስፓኒሽ ዝርያ ያለው ላቲን አሜርካዊ ተብለው በሦስት እንደሚከፈሉ ገልጸዋል።

“ዘረኝነት ባሕላችንን እየጎዳው ይገኛል፣ በክርስትያን ልብ ውስጥም ቦታ የለውም፣ ሕዝባችን ቃል የተገባለትን የነጻነትን፣ የእኩልነትንና የፍትህን ቃል ኪዳን በሚገባ እንዲያውቅ የሚያስችለው እውነተኛ የልብ መለወጥ እንዲኖር ያስፈልጋል” ብለዋል።

ብጹዓን ጳጳሳት በአገር በቀል አሜሪካውያን፣ አፍሮ አሜሪካውያን እና የስፓኒሽ ዝርያ ያለው የላቲን አሜርካዊያን መካከል የሚታይ የዘረኝነት ስሜት እንዴትና ከወዴት ሊመጣ እንደቻለ ሲያስረዱ፣ አንዱ ዘር የበላይነትን በመጎናጸፍ በጉልበት ሌላውን ከመሬቱ እንዲፈናቀል ማድረግና መሬቱንም መቀማት፣ የአፍሪቃዊ ዝርያ ያለውን በባርነት መግዛት ብቻ ሳይሆን ከማሕበራዊ እድገት የሚያግድ ሕጎችን በማጽደቅ የበታችነት ማዕረግን መስጠት፣ የስፓኒሽ ወይም የላቲን ዝርያ ያላቸውን የመኖሪያ ቤት ባለቤትነት፣ የሥራ ዕድል፣ የጤና አገልግሎትና የትምህርት ዕድሎችን መከልከል እነደሆኑ አስረድተዋል።

ዘረኝነት የሚቀርበት መንገድ፣

የሰሜን አሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ከሕዝቦቻቸው መካከል የተስፋፋው ዘረኝነት የሚወገዱበትን መንገዶች “ሰው ሆይ እግዚአብሔር ካንተ የሚፈልገው፣ ፍትህን ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትሕትና ትራመድ ዘንድ አይደለምን?” በማለት (በትንቢተ ሚክያስ በምዕ. 6. 8) ላይ የተገለጸውን ጠቅሰው አስረድተዋል። ፍትህ በእውነተኛ ታማኝነት ላይ የተመሠረተ መዋደድን ይጠይቃል ብለው ለዚህም ለጎረቤቶቻችን የምናሳየው ፍቅር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል። በልባችን ውስጥ ለሌሎች ቦታ እንዲኖር ያስፈልጋል፣ የኢየሱስ ቤተሰብ ከሆኑት መካከል አንዱ ሲሰቃይ ሌሎችም አብረውት እንደሚሰቃዩ እናውቃለን። በዘረኝነት ምክንያት የታጣውን መልካም ግንኙነት መልሰን መገንባት የምንችለው ከእግዚአብሔር ጋር በትሕትና በመጓዝ ነው። ብጹዓን ጳጳሳቱ በሐዋርያዊ መልዕክታቸው በጥንት ጊዜም ይሁን በአሁኑ ዘመን በውስጧ የሚታየውን የዘረኝነት መንፈስ የሰሜን አሜሪካ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል። ብጹዕን ጳጳሳቱ እንደ ምሳሌ፣ ደቡብ አፍሪቃን፣ ጀርመንንና ሩዋንዳን ጠቅሰው የሌሎች አገሮች ተቋማትም ቢሆኑ ያለፈውን ስሕተታቸውን ተገንዝበው ወደ እውነት ለመመለስ ችለዋል ብለዋል።

የክርስቲያኖች ውሕደት፣

በክርስቲያኖች መካከል አንድነትን ሊኖር ይገባል የሚለውን የማርቲን ሉተር ኪንግን ሃሳብ የሚጋሩት የሰሜን አሜርካ ብጹዓን ጳጳሳት ዘረኝነትን ለመዋጋት የክርስቲያኖች አንድነት ያስፈልጋል ብለው ዘረኝነትን ለማስወገድ መለወጥ ያስፈልጋል ብለዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ በማከልም የፍትህ መጓደልና ዘረኝነት ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት የሰው ልጅ ሕይወትን ማጥፋት ነው ብለው ዘረኝነት የሰው ልጅ ሕይወትንም ይመለከታል ብለዋል። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን ተስፋችንም በሰማዩ ቤታችን፣ የዓለም ሕዝቦች በሙሉ አንድ ይሆናሉ ብለው በሰሜን አሜርካ ሕዝብ መካከል የሚታየውን ዘረኝነት ለማስወገድ በሚያደርጉት ጥረት እንዲተባበሩ ሕዝባቸውን አደራ ብለዋል። በመልዕክታቸው መጨረሻም ለሰሜን አሜርካ ሕዝብ ያስተላለፉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን የሚያገኙት ወንድሞችና እህቶች በሙሉ አንድነታቸውን በማደስ፣ ዘረኝነት በመቃወም ከእግዚአብሔርም ጋር በትሕትና መጓዝ እንዲችሉ ጸሎታችንን እናቀርባለን ብለዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
20 November 2018, 16:04