ፈልግ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ 

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ

በዚህ በእኛ ዘመን የሚኖሩ ሰዎች ደስታ እና ተስፋ፣ ሐዘን እና ጭንቀት በተለይም ደግሞ በድህነት የተጎዱ ሰዎች ሁኔታ የእነርሱ ደስታ እና ተስፋ፣ ሐዘን እና ለቅሶ ሁሉ የክርስቶስ ተከታይ የሆኑ ሰዎች የሚጋሩት ነው”

ክፍል አንድ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በተሰኘው ዝግጅታችን ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅብራዊ አስተምህሮ መስረት የጣሉ የቤተ ክርስቲያን ቀኖናዎችን፣ አንቀጸ እምነቶችን፣ ማኅበራውዊ አስተምህሮዎችን እንዲሁም ይህንን የካቶሊክ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት የቤተ ክርስቲያን አባቶች የጻፉቸውን፣ ሐዋሪያዊ መልእክቶች እና ቃለ ምዕዳኖችን በመዳሰስ ነባራዊ የሆነውን የዓለማችን፣ የቤተ ክርስቲያናችንን እና የሀገራችንን ሁኔታ በዳሰሰ እና ከግምት ባስገባ መልኩ ወደ እናንተ እንደ ሚከተለው እናቀርባለን።

መግቢያ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ በአንድ ማኅበርሰብ ውስጥ የሚገኙ የሰው ልጆች ሁሉ በእኩልነት በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚገኙትን ቁሳዊ ሐብቶች እና መንፈሳዊ የሆኑ እሴቶች በጋራ እንዲቋደሱ የምያስተምር፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የመደጋገፍ መንፈስ እንዲኖር የሚመክር እና በአጠቃላይ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ሊኖር ሰለሚገባው የጋራ ተጠቃሚነት እና ማኅበራዊ ዋስትናን ማረጋገጥ በተመለከተ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አቋም በሰፊው የሚያመለክት አስተምህሮ ሲሆን ቤተ ክርስቲያኗ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ሊኖራት ሰለሚገባው ማኅበራዊ ፍትህ ያላትን አቋም በግልጽ የምታንጸባርቅበት የቤተ ክርስቲያኗ አስተምህሮ አንዱ ክፍል ነው። እነዚህ አስተምህሮዎች ጭቆናን፣ የመንግሥት ኃላፊነትን፣ ድጎማ ወይም ድጋፍ ማድረግን፣ ማህበራዊ አደረጃጀቶችን፣ የማኅበራዊ ፍትህ ስጋቶች እና ፍትሀዊ የሐብት ክፍፍል . . . ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚመለክት አስተምህሮ ነው።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በይፋ የተጀመረው እንደ አውሮፓዊያኑ የቀን አቆጣጠር 1891 ዓ.ም በወቅቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በነበሩት ሊዮ 13ኛ እንደ ነበረ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ በአውሮፓ በማበብ ላይ በነበረው የኢንዱስትሪ አብዮት ምክንያት ለተከሰተው ማኅበራዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት እና የቤተ ክርስቲያኗን አቋም ለመግለጽ በላቲን ቋንቋ “Rerum Novarum በአማርኛ በግርድፉ ሲተረጎም “አዳዲስ ነገሮች/ክስተቶች” በሚል አርእስት ለንባብ ባበቁት ሐዋርያዊ መልእክት እንደ ነበረ ይታወሳል። የዚህ ሐዋርያዊ መልእክት አጠቃላይ ይዘት ፍትዓዊ የሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍል በማኅበርሰቡ ውስጥ እንዲኖር እና ሠራተኞች በቂ በሆነ ሁኔታ ማኅበራዊ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ፣ በሥራ ቦታ ከአቅማቸው ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የሥራ ዘርፍ ላይ እንዲሰማሩ የሚጠይቅ እና በሥራ ቦታ ለሠራተኞች ጤንነት እንክብካቤ እንዲደረግ፣ በአጠቃላይ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የሰው ልጅ ሕልውና እና ሰብዓዊ ክብር ሊሆን እንደ ሚገባ፣ ገንዘብ የሰውን ልጅ ለማገልገል እንጂ በተቃራኒው የሰው ልጅ ገንዘብን ማገልገል እንደ ማይገባው በመግለጽ በስፋት የምያሳስብ ሐዋርያዊ መልእክት ነው።

ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ ከተመሰረተችበት እለት አንስቶ እስከ ዛሬ ቀን ድረስ በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም ድምጽ ለሌላቸው ሰዎች ድምጽ በመሆን፣ በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖሌቲካዊ ምክንያቶች የተነሳ በሕዝቦች ላይ የሚደረሰውን ማኅበራዊ ጫናና በደል በመቃወም ለዓለም ድምጽዋን ስታሰማ መቆየቷ ይታወቃል።

የዓለማችን ችግሮች እና ተግዳሮቶች እንዲሁም እድገት እና ብልጽግና በታሪክ ውስጥ በሚፈጠሩ የተለያዩ አጋጣሚዎች የተነሳ እነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎችም እንደ ወቅቱ ሁኔታ የሚለያዩ  ቢሆኑም ለእነዚህ ማኅበራዊ እድገቶች፣ ቀውሶች እና ተግዳሮቶች በተለይም ለድሃው የማኅበረሰብ ክፍል እና ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ማስተጋባት ላልቻሉ የተጨቆኑ ሕዝቦች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያት ጭቆና ጠፍቶ በአንጻሩ ፍትህ እና የጋራ ተጠቃሚነት በዓለም ዙሪያ እንዲሰፍን የተለያዩ ሰላማዊ የሆኑ መንገዶችን በመጠቀም የራሷን ከፍተኛ አስተዋጾ ማበርከቷ እና አሁንም ቢሆን ይህንን መልካም ተግባሩዋን አጠናክራ መቀጠሏ ይታወቃል።

1. የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ አጠቃላይ ይዘት እና ፅንሰ-ሐሳብ

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊ አስተምህሮ የማኅበርሰቡን መብት እና ግዴታ ከግምት ባስገባ መልኩ የሚከተሉትን ሁለት መሰረታዊ መርሆችን በማንገብ ይህንን ማኅበራዊ አስተምህሮ ሕጋዊ መልክ ታላብሰዋለች፣ ሕጋዊነቱንም ታረጋግጣለች። ምን አልባት አንድ ሰው የቤተ ክርስቲያን ተግባር እና ትኩረት በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ እና አግልግሎት መስክ ብቻ ሊሆን ይገባል ሊል ይችል ይሆናል። ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ወንጌልን መስበከ፣ ክርስቶስን ለዓለም ማስተዋወቅ እነዚህን እና እነዚህን በመሳሰሉ መንፈሳዊ እና ስነ-ምግባራዊ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ነው የሚገባት እንጂ ከእነዚህ ተልዕኮ ውጪ በመሄድ ማኅበረሳባዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መሥራት ለምን አስፈለጋት፣ ምንስ አገባት ብሎ ልጠይቅ ይችል ይሆናል። ይህም ተገቢና ሊነሳ የሚገባው ጠቃሚ የሆነ ጥያቄ መሆኑን እንረዳለን።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይህንን ጥያቄ በተመለከተ ያለት ምላሽ “ቤተ ክርስቲያን በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ገብታ በንቃት መሳተፏ ተገቢነት ያለው ጉዳይ ነው” በማለት ለእዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሆን ዘንድ የሚከተለውን ማብራሪያ እና መልስ ትሰጣለች።

1.     በእዚህም መሰረት በቅድምያ ማንኛውም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ የሚጀምረው ግብረ-ገባዊ ሥነ-ስርዓቶችን በቀጥታ ከፍጡራን ሁሉ በላይ ካለው መለኮታዊ የሆነ ኃይል፣ እርሱ ካለው መለኮታዊ ስነ-ምግባር ጋር በማቆራኘት ይጀምራል። ይህም ማለት ማንኛውም በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለው አዎንታዊ የሆነ ስነ-ምግባር በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ከፈጣሪ ጋር ይገናኛል ማለት ነው።

በዚህም የተነሳ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የሆኑ እሴቶች በቀጥታ ከስነ-ምግባር ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው የተነሳ እነዚህም የስነ-ምግባርና ሐይማኖታዊ የሆኑ እሴቶችን አቅፈው የሚይዙ ጉዳዮች በመሆናቸው የተነሳ ጭምር ሲሆን ቤተ ክርስቲያን የማኅበረሰቡ የሞራል፣ የስነ-ምግባር እና የሐይማኖት እምብርት በመሆኗ ጭምር የተነሳ ቤተ ክርስቲያን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የመግባት መብት ይሰጣታል ማለት ነው። ይህንንም ጣልቃ ግብነት የምታደርገው ሙያዊ የሆነ ትንታኔዎችን፣ በመስጠት የፖሊሲ ለውጦች እንዲመጡ በማስገደድ ሳይሆን ማኅበራዊ፣ ሞራላዊ እና ስነ-ምግባራዊ እሴቶች ተጠብቀው እንዲሄዱ እነዚህ ስነ-ምግባራዊ እሴቶች በታሪክ ሂደት ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮት ለመፍታት በማሰብ የምታደርገው ጣልቃ ግብነት ነው።

ይህንን ቀደም ሲል የተገጸውን ጭብጥ ሐሳብ በሚገባ ማብራራት አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ ይመስለኛል። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ለምን ትገባለች? ቢባል መልሱ አንድ እና አንድ ብቻ ነው። ማኅበረሰብ ስንል የሰዎች ስብስብ ማለት እንደ ሆነ ይታወቃል። የሰው ልጆች ተሰብስበው በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ሁሉ መልካም እና ገንቢ የሆኑ ነገሮች እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው ደግሞ ማኅበራዊ ግጭቶች፣ ኢፍታዊ ተግባሮች፣ የመብት ጥሰት . . .ወዘተ እነዚህን እና እነዚህን የመሳሰሉ ክስተቶች በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ልፈጠሩ ይችሉ ይሆናል፣ እየተፈጠሩም ይገኛሉ።

በማንኛውም ዓይነት ምክንያት የተነሳ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ ተገቢ ያልሆኑ ግጭቶች የሕብረተሰቡን ሰላም በማወክ፣ በተለይም ደግሞ ሕጻናትን፣ ሴቶችን እና አዛውንቶችን በአጠቃላይ መላውን የማኅበረሰብ ክፍል እና ማኅበራዊ መዋቅሩን ሳይቀር አደጋ ላይ በመጣል ማኅበራዊ ኑሮ አደጋ ላይ እንዲወድቅ በማድረግ የሕዝቡን ሰላም በማወክ የእግዚኣብሔር ስጦታ የሆነው የሰው ልጆች ነፍስ እንደ ዋዛ እንዲጠፋ ያደርጋል።  በእዚህም ምክንያት የተነሳ ቤተ ክርስቲያን የእግዚኣብሔር ስጦታ የሆነው የሰው ልጆች ክቡር የሆነ ነፍስ እንደ ዋዛ እንዳይጠፋ በማሰብ፣ የግጭቶች ሁሉ መንስሄ የሆኑ ማኅበራዊ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ሰላማዊ በሆነ መልኩ ውይይት እንዲደርግ፣ ለችግሮች ሁሉ ሰላማዊ በሆነ መልኩ ፊት ለፊት ተገናኝቶ የመወያየት ባሕልን ባማከለ መልኩ ችግሮች እና አለመግባባቶች በሰላም ይፈቱ ዘንድ የበኩሉዋን ማኅበራዊ አስተዋጾ ማድርግ ሰለሚኖርባት በእዚህ አግባብ እና በዚህ ምክንያት የተነሳ በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ በትኩረት ትሳተፋለች።

በተመሳሳይ መልኩ ቤተ ክርስቲያን በኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ውስጥ በቀጥታ በመሳተፍ ሙያዊ የሆነ ትንታኔ የመስጠት ሕጋዊ የሆነ መብት ባይኖራትም፣ ነገር ግን በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጫናዎች ምክንያት የሚጎዳው የሰው ልጅ መሆኑን በሚገባ ስለምትረዳ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በእነዚህ ጉዳዮች ውስጥ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተሳትፎ ታደርጋለች። ምክንያቱም ፍታዊ የሐብት ክፍፍል በአንድ ሀገር ውስጥ የሌለ ከሆነ፣ ለሰው ልጆች ሕልውና አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ነገሮች የማይሟሉ ከሆነ ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው ያወ የማኅበረሰብ ክፍል ነው፣ በተለይም ደግሞ ድሃ እና አቅመ ደካማ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል በቀጥታ የእዚህ ጥቃት ሰለባ ይሆናል። በተመሳሳይ መልኩም በአንድ ሀገር የፖለቲካ እና ማኅበራዊ መዋቅር ውስጥ በሚከሰተው እና በሰፊው በሚንጸባረቀው ሌብነት/ ሙስና፣ ሕዝብን ያላማከለ ውሳኔ፣ ስነ-ምግባርን እና የተፈጥሮ ሂደትን ባላማከለ መልኩ የሰው ልጆችን ማኅበራዊ ዋስተና እና ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ውሳኔዎች በሚተላለፉበት ወቅት ሰላማዊ የሆነ ተቃውሞዋን ቤተ ክርስቲያን የማስተጋባት ሞራላው እና ሰነ-ምግባራዊ ግዴታ አለባት።

ምክንያቱም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጫናዎች እና ኢፍታዊ ድርጊቶች ምክንያት የሚጎዳው ያው የሰው ልጅ ነው፣ በተለይም ደግሞ አቅመ ደካማ እና ድኸ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል በመሆኑ የተነሳ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ ስንመለከት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ማኅበራዊ ፍትህ እንዲኖር፣ በተለይም ዝቅተኛ የተባሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መብት ለማስከበር እና ብሎም ከፍ ሊያደርጋቸው በማሰብ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑ እና ኢፍታው ተግባራትን ማውገዙ ያታወቃል። ቤተ ክርስቲያንም የክርስቶስ ተከታይ በመሆኗ የተነሳ የክርስቶስን መንፈሳዊ፣ ስነ-ምግባራዊ እና ማኅበራዊ ተልዕኮ አጠናክራ የመቀጠል ተልዕኮ ስለተሰጣት በእዚሁ አግባብ ተግባሩዋን ማከናወን ይገባታል ማለት ነው።

2.    ቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ የሆኑ አስተምህሮዎችን እንድትሰጠ መብት የሚሰጣት ሁለተኛው ምክንያት  “የክርስቲያን ራዕይ ታሪካዊ ገጽታ አለው” የሚለው ጭብጥ ነው። ቤተ ክርስቲያን ከማኅበርሰቡ እና  ከታሪክ ጋር ከፍተኛ እና እውነተኛ ኅብረት አላት። እናም የሰው ልጅን ለማዳን እና ማኅበረሰቡን ለማደስ ከሚሳተፉ አካላት ጋር በመሆን “በዚህ በእኛ ዘመን የሚኖሩ ሰዎች ደስታ እና ተስፋ፣ ሐዘን እና ጭንቀት በተለይም ደግሞ በድህነት የተጎዱ ሰዎች ሁኔታ የእነርሱ ደስታ እና ተስፋ፣ ሐዘን እና ለቅሶ ሁሉ የክርስቶስ ተከታይ የሆኑ ሰዎች የሚጋሩት ነው” (ሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ Gaudium et Spes ቁ. 1) በማለት ቤተ ክርስቲያን የሕዝቡን መከራ እና ሐዘን ደስታቸውን እና ተስፋቸውን እንደ ምትካፈል ያረጋግጣል። በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራዊ አስተምህሮ መዐከሉን ያደርገው በሰው ልጆች ላይ ነው። ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የተመሰረተችው የመላእክት ጠባቂ ለመሆን አይደለም፣ በተቃራኒው የሰው ልጆችን አቅፋና ደግፋ፣ በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲኖሩ በማድረግ፣  እግዚኣብሔር የሰጣቸውን በረከት በሰላም እና በደስታ እየተቋደሱ እንዲኖሩ በማድረግ የሰው ልጆችን ለእግዚኣብሔር መንግሥት የማብቃት ተልዕኮ እንደ ተሰጣት ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያን የሰው ልጆችን ሰላም እና ደስታ የሚነጥቁ ነገሮችን እና ተግባራትን ለማስወገድ በማሰብ እነዚህን ነገሮች መሰረት በማድረግ እና ከግምት ባስገባ መልኩ ማንኛውም ዓይነት ማኅበራዊ ገጽታ ያላቸው ችግሮች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ይፈቱ ዘንድ የምታስተምረው በዚሁ ምክንያት ነው፣ በተለይም ደግሞ ድሃ የተባሉ እና አቅመ ደካማ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍል ድምጽ ለማስተጋባት በማኅበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የምትገባው እና ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ግንዛቤ ማስጨበጫ የሆኑ አስተምህሮዎችን የምትሰጠው በዚሁ ምክንያት የተነሳ ነው።

የዚህ አስተምህሮ አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

ይህንን ዘገባ በድምጽ ለመከታተል ከዚህ በታች ያለውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
20 November 2018, 14:24