ፈልግ

2018.11.21 Venezia in rosso 2018.11.21 Venezia in rosso 

ለእምነት ነጻነት ድምጽ ማሰማት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

በመላው ዓለም በሚገኙት ትላልቅ ቤተክርስቲያኖችና ካቴድራሎች ውስጥ ሻማ የማብራት ስነ ስርዓት እንዲከናወን ጥሪን ያስተላለፈው፣ በስቃይና መከራ ውስጥ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍን በመስጠት የሚታወቅ ካቶሊካዊ የእርዳታ ድርጅት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ስቃይና መከራ የሚደርስባቸውን ክርስቲያኖች ለመደገፍ፣ በቁጥር አናሳ በመሆናቸው ምክንያት ጭቆና የሚደርስባቸውን የክርስቲያን ወገኖችን ለማጽናናት ተብሎ ትናንት ረቡዕ ህዳር 19 ቀን 2011 ዓ. ም. “ቀይ መብራት እናብራ፣ ቀይ ልብስ እንልበስ፣ በቀይ ቀለማት የተጻፉ መልዕክቶችን እንለዋወጥ” በሚል ርዕሥ ዙሪያ በመሰባሰብ፣ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች በሚገኙት ትላልቅ ቤተክርስቲያኖችና ካቴድራሎች ውስጥ የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት ተክሂዶ ማለፉ ታውቋል።

በመላው ዓለም በሚገኙት ትላልቅ ቤተክርስቲያኖችና ካቴድራሎች ውስጥ የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት እንዲከናወን ጥሪን ያስተላለፈው፣ በስቃይና መከራ ውስጥ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍን በመስጠት የሚታወቅ ካቶሊካዊ የእርዳታ ድርጅት መሆኑ ታውቋል። በእንግሊዝ ውስጥ የድርጅቱ የመረጃ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ጆን ስነ ስርዓቱ እንዲከናወን የተፈለገበትን ምክንያት ሲገጹ በዓለም ዙሪያ በርካታ የክርስቲያን ወገኞችና የማህበረሰብ ክፍሎች ለከባድ ስቃይና በደል መጋለጣቸውን ገልጸው፣ ለሚደርስባቸው ስቃዮች ዓለም በቂ ትኩረት ባለመስጠቱ ነው ብለዋል። በመሆኑም ለማድረግ ያሰብነው የስማዕትነት ምልክት የሆነውን ቀይ ቀለም በመምረጥ፣ በሻማ መብራት በመታገዝ ዓለም የስቃይን ትርጉም እንዲረዳው ፈልገናል ብለው፣ በርካታ ሰዎች ሊሸከሙት የማይችሉትን የስቃይ መስቀል ተሸክመው በመጓዝ ላይ መሆናቸውንና ሕይወታቸውን እስከማጣት እንደሚደርሱ ለማስገንዘብ ነው ብለዋል። አቶ ጆን በማከልም የዘንድሮ እቅዳቸው እንደ ፓክስታን፣ ኢራቅ፣ ሶርያ፣ ቻይናና በአፍሪቃ ውስጥም በብዙ አገሮች፣ ሕዝቦች ለእምነታቸው ሲሉ የሚቀበሉት ስቃይ እያደገ በመምጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የሃይማኖት ነጻነት፣

በዓለማች ከሚገኙ ክርስቲያኖች ውስጥ ከሰባቱ መካከል አንዱ ስቃይ መከራና ስደት በሚያደርሱ አገሮች እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን ይህም በዓለም ውስጥ ስቃይ የሚደርስበት የክርስቲያን ጠቅላላ ቁጥር ከ300 ሚሊዮን በላይ እንደሚያደርገው ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አስታውቋል።

በስደትና መከራ ውስጥ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍ የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ከሰኔ ወር 2008 እስከ ሰኔ ወር 2010 ዓ. ም. ድረስ ባደረገው ጥናት መሠረት ከሌሎች ሁሉ የከፋ ጭቆናና በደል የሚደርስባቸው የሐይማኖት ወገኖች የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደሆነ ገልጿል። ይሁን እንጂ በሌሎች በርካታ የእምነት ክፍሎች ላይም የሃይማኖት ነጻነት ጥሰት እንዲሁ እየጨመረ መሆኑን ሪፖርቱ ገልጾ፣ በክርስቲያኖች ላይ ይፈጸማሉ የተባሉ በደሎችና ጭቆናዎችም፣ እምነታቸውን ወደ ክርስትና ለውጠዋል በመባል፣ ጋብቻን አስገድዶ መፈጸም፣ የአጥፍታ ጥውፊዎች ጥቃት፣ ዘረፋ፣ የአምልኮ ስፍራዎችንና መንፈሳዊ ምስሎችን፣ ቅርሶችንና ምልክቶችን ማውደም፣ አፈና፣ የሐሰት ክሶችን ማቅረብ፣ በሐይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባት፣ በእምነት ተቋማት ላይ ቁጥጥር ማድረግና በሐይማኖት ነጻነት ላይ ገደብ መጣል እንደሚገኙበት ሪፖርቱ አብራርቷል።

በስቃይና መከራ ውስጥ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍን በመስጠት የሚታወቅ ካቶሊካዊ የእርዳታ ድርጅት የእንግሊዝ ጽሕፈት ቤት የመረጃ ክፍል አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ጆን ፖንቲፈጽ እንደገለጹት በዋና ድርጅታቸው ጥሪ መሠረት በእንግሊዝና በሌሎች አገሮች የሚገኙ ትላልቅ ቤተክርስቲያናት ካቴድራሎች የሻማ ማብራት ስነ ስርዓትን ትናንት ረቡዕ ህዳር 19 ቀን 2011 ዓ. ም. መፈጸማቸውን ገልጸው ይህ ብቻ ሳይሆን የዕለቱ ልብሳቸውን ቀለም ቀይ እንዲሆን ማድረጋቸውንና ከጓደኞቻቸው ጋር የሚለዋወጡት የማሕበርዊ ሚዲያ ገጽ መልዕክታቸውን በቀይ ቀለም ጽፈው መለዋወጣቸውን አስረድተዋል። በእንግሊዝ ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ካቴድራሎች መካከል በለንደን በሚገኘው ወስት ሚኒስትር ካቴድራል የተከናወነው ስነ ስርዓት ደማቅ እንደነበር፣ ተመሳሳይ ስነ ስርዓት በአንግሊካን ካቴድራልም መከናወኑን አስረድተዋል።  

29 November 2018, 16:07