ፈልግ

Cristo Re dell'universo, Gesu Cristo, Cristo Pantocratore Cristo Re dell'universo, Gesu Cristo, Cristo Pantocratore 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “እግዚአብሔር መከራና ስቃይ ያለበትን የመስቀል ዙፋን መረጠ”።

የኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥነት የሃብት፣ የስልጣንና የምቾት ፍለጋ ሳይሆን ለሌሎች የሚሰጥ የፍቅርና ራስን ለመስውዕትነት አሳልፎ የሰጠበት ስጦታ እንደሆነ ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የዓለም ሃያላን የስልጣን ዙፋናቸውን አመቻችተው ሲገነቡ እግዚአብሔር ግን ለሞት ተላልፎ የሰጠበትን፣ ስቃይና መከራ ያለበትን የመስቀል ዙፋን እንደመረጠ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጹ። የላቲን ስርዓተ አምልኮን በምትከተል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዘንድ ትናንት እሑድ ህዳር 16 ቀን 2011 ዓ. ም. የተከበረውን የክርስቶስ ንጉሥ ክብረ በዓል ምክንያት በማድረግ በላኩት የቲውተር መልዕክታቸው እንደገለጹት የኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ በዓል የሚያስታውሰን ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሳችን፣ ታሪክንም በሙሉ የሚገዛ አምላክ እንደሆነ አስረድተዋል።

በቅድስት መንበር ሥር የቤተክህነት ጳጳሳዊ ምክር ቤት ዋና ተጠሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ቤኒያሚኖ ስቴላ፣ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ በዓል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የእያንዳንዳችን ሕይወትና የቤተክርስቲያንም የማይሻር ዘለዓለማዊ ንጉሥ መሆኑን ያስታውሰናል ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ በ1917 ዓ. ም. በተከበረው ቅዱስ ዓመት መዝጊያ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ መሆኑ በታላቅ ክብረ በዓል በየዓመቱ እንዲታወስ ብለው ያስጀመሩት በዓል እንደሆነ ገልጸዋል። ካርዲናል ቤኒያሚኖ በማከልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 11ኛ፣ የዓለማዊነት አስተሳሰብና ያስከተላቸው ስህተቶች በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው የገለጹትን በማስታወስ፣ ዛሬም ቢሆን የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት ለማቋረጥ፣ ከእርሱም ለመራቅ የሚያደርገውን ጥረት በግልጽ ማየት ይቻላል ብለዋል።

ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ክብረ በዓልን ለማክበር ወይም ለማስታወስ ይቻላት ዘንድ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል በምዕ. 18 33-37 የጻፈውንና፣ የእግዚአብሔር ልጅ በሰንሰለት ታስሮ ወደ ጲላጦስ ፊት መቅረቡን መመልከት ማስታወስ በቂ እንደሚሆን ብጹዕ ካርዲናል ቤናሚኖ ገልጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእንጨት መስቀል ላይ ሆኖ ዓለምን እንደገዛ አስታውሰው፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ንጉሥነት የምናውቀው ከዚያው ከመስቀል ላይ እንደሆነ አስረድተዋል። ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥነት የሃብት፣ የስልጣንና የምቾት ጉዳይ ሳይሆን ለሌሎች የሚሰጥ የፍቅርና ራስን ለመስውዕትነት አሳልፎ የሚሰጥበት ስጦታ እንደሆነ አስረድተዋል። ብጹዕ ካርዲናል ቤናሚኖ በማከልም በመስቀል ላይ የተሰቀለው ኢየሱስ ክስቶስ ፊት በመመልከት ለእኛ ያለን ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ መረዳት እንችላለን ብለዋል።

የሰው ልጅ ታሪክ አልፋና ኦሜጋ፣

ብጹዕ ካርዲናል ቤናሚኖ ስቴላ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ንጉሥ ክብረ በዓል፣ ዓመታዊው የአምልኮ ስርዓት እንደሚደመደምና ቀጣዩ የአምልኮ ስርዓት የሚጀምረው በፋሲካ ወራት በሚጀመረው ቅዱስ ሳምንት እንደሆነ ገልጸዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ በዓል የሚያሳስበን የክርስትና ሕይወታችን የሚመራው ለሰዎች እንዳይገለጡ ተብሎ በተደበቁ የስልጣን ዓይነቶች ሳይሆን በዕለታዊ ሕይወታችን መካከል በምናከናውናቸው ተግባራት የሚገለጽ መሆኑን አስረድተዋል። በቅርቡ የወጣቶችን መንፈሳዊና ማሕበራዊ ሕይወት በዝርዝር በመመልከት የተጠናቀቀውን 15ኛ አጠቃላይ መደበኛ የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ያሳታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ቤናሚኖ ስቴላ፣ የክርስትና ሕይወታችን የሚጀምርበት የምስጢረ ጥምቀት ጸጋ፣ ንጉሳችን የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን መልክ እየተመለከትን የምንጓዝበት፣ ከሁሉም በላይ በክርስትና ሕይወታችን መሪ የሆነውንና ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቃየበትን መስቀል እየተመለከትን እንድንጓዝ የሚያደርገን ጸጋ እንደሆነ አስረድተዋል።

ቸርነት በሕብረት እንድንኖርና እንድናድግ ያግዛል፣

በኢጣሊያን ውስጥ ዓመታዊው የአምልኮ ስነ ስርዓት የሚደመደምበት የመጨረሻው እሑድ ካህናትን በአገልግሎታቸው ለማገዝ ድጋፍ እንዲደረግ የግንዛቤ ማስያዣ ቀን እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ቤናሚኖ ይህም የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌን በመከተል ለምዕመናን ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ ለሚገኙት ካሕናት የሚደረግ የቸርነት መግለጫ ጊዜ እንደሆነ አስረድተው ከምዕመናን በኩል የሚገለጽ የቸርነት ምሳሌ፣ ካህናት በሐዋርያዊ አገልግሎት ወቅት በምዕመናን መካከል የሚታየውን የድህነትና የመከራ ሕይወት ለማቃለል እንደሚያግዛቸው አስረድተዋል።

                

26 November 2018, 15:55