ፈልግ

2018.11.15 giornata mondiale dei poveri 2018.11.15 giornata mondiale dei poveri 

በር.ሊ.ጳ. ፍራንችስኮስ ጥሪ መሠረት የማልታ በጎ አድራጊ ማሕበር ድሆችን የበለጠ ለመርዳት ተዘጋጀ።

በዛሬ ዓለም ተስፋፍቶ የሚገኝ የድህነት ዓይነት የሃብት ማጣት ብቻ ሳይሆን፣ የሃብት ወይም የገንዘብ ማጣትን ተከትሎ የሚመጡ ለምሳሌ ከማሕበረሰብ መካከል መገለል፣ ብቸኝነት፣ ተቀባይነትን አለማግኘት፣ ትኩረትን መነፈግ፣ በሃብት ባለቤትነት አለመመጣጠን እንደሆነ ገልጸው እነዚህም በማሕበረሰቡ መካከል ውጥረትን መፍጠራቸውን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስጀመሩትንና፣ ትናንት እሑድ ህዳር 9 ቀን 2011 ዓ. ም. ሁለተኛ አመቱን ያከበረውን ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን በድምቀት ያከበሩት የማልታ በጎ አድራጊ ማሕበራት አባላት፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የአደራ ጥሪን ተቀብለው ከዚህ በፊት ለድሆች የሚሰጡትን የእርዳታ አገልግሎት አጠናክረው ለመቀጠል መነሳታቸውን አስታወቁ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ የሚከበረውን የድሆች ቀን ምክንያት በማድረግ ላስተላለፉት መልዕክታቸው መሪ ርዕስ “ይህ ደሃ ሰው ጮኸ፣ እግዚአብሔርም ሰማው” የሚል እንደሆነ ታውቋል። በማልታ በጎ አድራጊ ማህበር አባላት መካከል፣ ለደሆች የሚሰጡ በርካታ የፍቅር ሥራ የአገልግሎት ዘርፎች እንዳሉ የታወቀ ሲሆን ማሕበርተኞችም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የአደራ ጥሪን ተቀብለው የዕርዳታ አቅርቦት ሥራቸውን በብቃት እንደሚወጡት ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድሮ በተከበረው ሁለተኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን መልዕክታቸው እንዳስገነዘቡት፣ ደሆች በድህነት ብቻ ተፈርጀው እንዳይቀሩ፣ ነገር ግን የሕይወት ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚሹ፣ ቋሚ የመኖሪያ ቤት የሚያስፈልጋቸው፣ ከዕለታዊ የሕይወት አካሄድ ወይም መስመር ወጣ ያሉ እንዳይሆኑ ማድረግና ከማሕበረሰብም እንዳይገለሉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የማልታ በጎ አድራጊ ማሕበር ለድሆች ከሚያቀርበው የእርዳታ አቅርቦት መካከል በሆስፒታል ውስጥ የሕክምና  አገልግሎትም እንደሚገኝ የሚታወቅ ሲሆን የዚህ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ዶሚንክ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ከባድ ድህነት ተወግዷል ቢባልም፣ በዛሬ ዓለም ተስፋፍቶ የሚገኝ የድህነት ዓይነት የሃብት ማጣት ብቻ ሳይሆን፣ የሃብት ወይም የገንዘብ ማጣትን ተከትሎ የሚመጡ ለምሳሌ ከማሕበረሰብ መካከል መገለል፣ ብቸኝነት፣ ተቀባይነትን አለማግኘት፣ ትኩረትን መነፈግ፣ በሃብት ባለቤትነት አለመመጣጠን እንደሆነ ገልጸው እነዚህም በማሕበረሰቡ መካከል ውጥረትን መፍጠራቸውን አስረድተዋል። በማከልም ራስ ወዳድነትና ብቻዬን ልደግ የሚል አስተሳሰብ እየተስፋፋ መምጣቱን የገለጹት የሕክምና እርዳታ አስተባባሪው ክቡር አቶ ዶሚኒክ፣ የቤተሰብ ወገኖችም ይህን እየተገነዘቡ መምጣታቸውንና እርስ በርስ መረዳዳት የሚለው አባባል በተግባር እየተገለጸ አለመሆኑን ተናግረው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ይህን አዝማሚያ ለመለወጥ የተነሱ ይመስላል ብለዋል።

ክቡር አቶ ዶሚኒክ በቃለ ምልልሳቸው የመተጋገዝ ወይም የመረዳዳት ስሜት እየጠፋ የመጣው ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ ሲገልጹ፣ በማሕበረሰብ መካከል የመተጋገዝ መንፈስ እየቀነሰ የመጣው በግለ ሰቦች እና በቤተሰብ መካከል የነበረ መረዳዳት፣ እንደዚሁም መንግሥት ለዜጎች ሊያቀርብ ቃል የገባው የሕክምና እርዳታን ጨምሮ ሌሎችም በርካታ ማሕበራዊ ድጋፎች ተግባራዊ ሳይሆኑ ሲቀር እንደሆነ አስረድተዋል። አቶ ዶሚኒክ በማከልም በዓለማችን የእያንዳንዱ ግለ ሰብ የፍጆታ መጠን ከሚያስፈልገው በላይ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው ይህም በሰዎች ውስጥ የግለኝነትን ስሜት ፈጥሯል ብለዋል።

አሁን በዓለማችን የሚታይ ድህነት ሥራ አጥ ወጣቶችን በመጉዳት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ዶሚኒክ ከዓለማችን ወጣቶች መካከል 25 ከመቶ የሚሆኑ ወጣቶች ሥራ አጥ እንደሆኑ ጠቅሰው በርካታ አገሮች ለእነዚህ ወጣቶች የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እየሠሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል። አቶ ዶሚኒክ በተጨማሪም የጡረታ መብታቸው የተከበረላቸው አዛውንትም ቢሆኑ ከፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ መናር የተነሳ መንግሥት የሚከፍላቸው የጡረታ ገንዘብ ሕይወታቸውን በበቂ ሁኔታ ሊመሩ የሚያስችላቸው ሆኖ አልተገኘም ብለዋል። በመሆኑም እነዚህን ማሕበራዊ ችግሮች ግልጽ በሆነ መንገድ መመልከት እንደሚያስፈልግ በድህነት የተጠቁና ከማሕበረሰቡ መካከል የተገለሉትን ብቸኛ ግለሰቦችንና ቤተሰቦች በመልሶ ማቋቋም ሥራ በመታገዝ ወደ ማሕበራዊ ኑሮ መመልስ፣ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።  ለድሆች የሚሰጥ የሆስፒታል አገልግሎቶች አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ዶሚንክ፣ መተጋገዝ ካለ፣ የተቸገሩትን ተቀብሎ የመርዳትና የማስተናገድ ቅን ፍላጎት ካለ፣ በቃለ ምልልሱ ከጠቀሷቸው ማሕበራዊ ችግሮች የመላቀቅ ተስፋ እንዳለ ገልጸዋል። ማሕበራቸው ከኢጣሊያ የባሕር ሃይል ጋር በመተባበር የሜዲቴራኒያንን ባሕር ለሚያቋርጡ ስደተኞች የሚያቀርቡት፣ ስደተኞችን ከሞት አደጋ የማዳንና ሕይወታቸውንም የመታደግ አገልግሎት አገልግሎቱን ከሚሰጡት ብቻ ሳይሆን አገልግሎትን ከሚያገኙት ሰዎች ልብ የሚፈልቀውን ደስታ መመልከት እንደሚያስደስታቸው ገልጸዋል። የሆስፒታል አገልግሎቶች አስተባባሪ ክቡር አቶ ዶሚንክ በመጨረሻም ካለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ ማሕበራችው በሩሲያ ውስጥ በቀን ከ300 እስከ 350 ተረጂዎችን ተቀብሎ ዕለታዊ ምግብን እንደሚያድል አስታውሰው በአካባቢው የእርዳታ አቅርቦታቸው ጥቂት ነው ቢባልም የእርዳታ አቅራቢዎች ቁጥር እየተበራከተ በመጣ ቁጥር የችግሮችም መጠን ሊቀንስ እንደሚችን አስረድተዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
19 November 2018, 15:58