ፈልግ

Aleppo - Siria Aleppo - Siria 

ብጹዕ አቡነ ዣንባርት ለሶርያ ክርስቲያኖች ዕርዳታን ተማጸኑ።

ከዓመታት ጦርነት በኋላ የሰላም ጭላንጭል በታየባት በአሌፖ ለሚኖሩ የክርስቲያን ቤተሰቦች እርዳታን ለማቅረብ እቅዶች ተነድፈው በርካታ መልሶ የመገንባት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዣንባርት ከተለያዩ ቦታዎች የሚቀርቡ እርዳታዎች ለነዋሪዎች ተስፋን እንደሚሰጡ፣ አካባቢውንም መልሶ ለመገንባት ትልቅ እገዛ እንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሶርያ የአሌፖ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዣንባርት በአካባቢው ከጦርነት ጉዳት የተረፉ ክርስቲያን ቤተሰቦችን ለመርዳት የተነደፈውን የዕርዳታ መርሃ ግብር በማስታወስ ባደረጉት የዕርዳታ ተማጽኖአቸው፣ ከጦርነቱ አደጋ የተረፉት የአሌፖ ክርስቲያን ቤተሰቦች ለእርዳታ ፍለጋ ብለው እንዳይሰደዱ፣ በሚኖሩበት መንደር እርዳታን እንዲያገኙ አቅም የፈቀደውን እናድርግላቸው ብለዋል። ከተለያዩ እምነቶች ተከታዮችም ጋር አብረው  በሰላም የሚኖሩበትን መንገድ እናመቻች ብለዋል።

ከዓመታት ጦርነት በኋላ የሰላም ጭላንጭል በታየባት በአሌፖ ለሚኖሩ የክርስቲያን ቤተሰቦች እርዳታን ለማቅረብ እቅዶች ተነድፈው በርካታ መልሶ የመገንባት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን የጠቀሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዣንባርት ከተለያዩ ቦታዎች የሚቀርቡ እርዳታዎች ለነዋሪዎች ተስፋን እንደሚሰጡ፣ አካባቢውንም መልሶ ለመገንባት ትልቅ እገዛ እንደሆነ አስረድተዋል። በአሌፖ ከተማ የሚገኝ ካቴድራል በጦርነቱ የተጎዳ ቢሆንም አሁን በመጠገኑ በየቀኑ ወደ ግቢው ለሚመጡ 120 ቤተሰቦችን እንደ መመገቢያ ጣቢያ ሆኖ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በ11 የተለያዩ የሕክምና ዘርፍ አገልግሎትን እንደሚሰጥ፣ ለ186 ቤተሰቦች የሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል መቋቋሙን ተናግረዋል።

በርካታ የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች እንዲከናወኑ በሚፈለግበት ባሁኑ ወቅት የሶርያ ሕዝብ በፍቅር አብሮ የሚኖርበትን መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ብጹዕ አቡነ ዣንባርት ገልጸዋል። ብጹዕ አቡነ ዣንባርት ከቫቲካን የዜና ማዕከል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የአገሪቱ ቤተክርስቲያን ቀዳሚ ተሎኮ ለዓመታት የዘለቀውን የሶርያ ሕዝብ ስደት ማስቆም እንደሆነ አስረድተዋል። በጦርነት የወደሙትን ቤተክርስቲያኖችን በመጠገን ለምዕመናኑ ተስፋን መስጠት እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ በቅድሚያ ክፉኛ የተጎዳውን ካቴድራል በመጠገን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በካቴድራሉ ለማክበት በዝግጅት ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል። በጦርነት የተጎዱ ቤተሰቦችን ለመርዳት የምናደርገውን የእርዳታ አቅርቦት ሳንዘነጋ የሃገረ ስብከቱ የሊቀ ጳጳሳት መኖሪያዎችን በማደስ ላይ መገኘታቸውን ገልጸው በአካባቢው ለሚገኙት ነዋሪዎች የምንሰጠውን የቤተክርስቲያን ተልዕኮ የሆነውን የወንጌል ምስክርነት እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሃገረስብከታቸው 12 ቤተክርስቲያኖችና ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት እንዳሉ የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዣንባርት ከ12 ቤተክርስቲያኖች መካከል 6ቱ አገልግሎት እንደሚሰጡ እና ወደነዚህ ቁምስናዎች በርካታ ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ አዛውንትም በየቀኑ እንደሚመጡ ተናግረዋል። ለእነዚህ በሙሉ ሐዋርያዊ አገልግሎት እንዲዳረስ ለማድረግ ካህናትን፣ እገዛን ለማድረግ ፈቃደኛ ለሆኑት፣ የእርዳታ አቅርቦት ሥራ ለሚመለከታቸው በሙሉ ጥሪ ማድረጋቸውን አቡነ ዣንባርት ገልጸዋል። ጦርነት በተደረጉባቸው ባለፉት ዓመታትም ቢሆን በሀገረ ስብከታቸው የትምህርት አገልግሎት መስጠትን ያላቋረጡ አራት ትምህርት ቤቶች፣ የሞያ ማሰልጠኛ ማዕከላት መኖራቸውን ገልጸው አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉትም ቢሆን ከጥፋት እንዲተርፉ እግዚአብሔር የጠበቃቸውን የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በሙሉ ለመጠቀም የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል።

ኩላዊት ቤተክርስቲያን የወንጌል ተልዕኮ አደራ አለባት። የምስራቁ ዓለም ቤተክርስቲያን ለምዕራቡ ዓለም የእምነት ምንጭ መሆኗንም አስረድተዋል። ስለዚህ ከምስራቁ ዓለም የክርስቲያኖች መሰደድ ምክንያት የክርስትና ምንጭ እንዲደርቅ አንፈልግም ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዣንባርት ክርስቲያኖች እንዳይሰደዱ በሚኖሩበት አካባቢ የሚያስፈልጋቸውን እገዛ በማቅረብ ልንረዳቸው ያስፈልጋል ብለዋል። ጦርነት የከፋፈለው የሶርያ ሕዝብ እርስበርስ እንዲታረቅ፣ ተፋቅሮ በሰላም እንዲኖር ያስፈልጋል ብለው፣ የጦር መሳሪያንና የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ አሸባሪዎች ሶርያን ለቅቀው ከወጡ ሕዝባቸው በሰላም መኖር ይችላል ብለዋል። ቤተክርስቲያንም የሰላም ጊዜ እንዲመጣ የበኩልዋን አስተዋጽዖን በማድረግ ላይ መገኘቷን ገልጸዋል።   

07 November 2018, 15:31