ፈልግ

በዓለማችን በ300 ሚሊዮን ክርስቲያኖች ላይ ስቃይና መከራ እንደሚደርስባቸው ተገለጸ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዓለማችን በሚገኙ 38 አገሮች ውስጥ ክርስቲያኖች ስቃይና በደል እንዲሁም መገለል እንደሚደርስባቸው በስደትና መከራ ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍ የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አስታወቀ። ጳጳሳዊ ፋውንዲሽኑ ይህን ያስታወቀው ትናንት ህዳር 13 ቀን 2011 ዓ. ም. በሮም ከተማ ባቀረበው 14ኛ ሪፖርቱ መሆኑ ታውቋል።

በዓለማች ከሚገኙ ክርስቲያኖች ውስጥ ከሰባቱ መካከል አንዱ ስቃይ መከራና ስደት በሚያደርሱ አገሮች እንደሚኖር የተገለጸ ሲሆን ይህም በዓለም ውስጥ ስቃይ የሚደርስበት የክርስቲያን ጠቅላላ ቁጥር ከ300 ሚሊዮን በላይ እንደሚያደርገው ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አስታውቋል። ፋውንዴሽኑ በሪፖርቱ እነዚህ በእምነት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሆኑ ምዕመናን ደምና ስጋ ናቸው በማለት ትናንት በሮም ከተማ የሚገኘው በኢጣሊያ የቅድስት መንበር ኤምባሲ አስታውቋል።

የከፋ ስቃይ የሚደርስባቸው ክርስቲያኖች ናቸው፣

በስደትና መከራ ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍ የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ከሰኔ ወር 2008 እስከ ሰኔ ወር 2010 ዓ. ም. ድረስ ባደረገው ጥናት መሠረት ከሌሎች ሁሉ የከፋ ጭቆናና በደል የሚደርስባቸው የሐይማኖት ወገኖች የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደሆነ ገልጿል። ይሁን እንጂ በሌሎች በርካታ የእምነት ክፍሎች ላይም የሃይማኖት ነጻነት ጥሰት እንዲሁ እየጨመረ መሆኑን ሪፖርቱ ገልጾ፣ ሪፖርቱ የቀረበው  በዓለማችን በ150 አገሮች ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ ከሚፈጸሙ ጭቆናዎች መካከል ጎልተው በሚታዩት ላይ ጥናት አካሂደው ሪፖርት እንዲያቀርቡ በተመደቡ ፕሮጀክቶች አማካይነት እንደሆነ ታውቋል። በክርስቲያኖች ላይ ይፈጸማሉ የተባሉ በደሎችና ጭቆናዎችም፣ እምነታቸውን ወደ ክርስትና ለውጠዋል በመባል፣ ጋብቻን አስገድዶ መፈጸም፣ የአጠፍታ ጥውፊ ጥቃት፣ ዘረፋ፣ የአምልኮ ስፍራዎችንና መንፈሳዊ ምስሎችን፣ ቅርሶችንና ምልክቶችን ማውደም፣ አፈና፣ የሐሰት ክሶችን ማቅረብ፣ በሐይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባት፣ በእምነት ተቋማት ላይ ቁጥጥር ማድረግና በሐይማኖት ነጻነት ላይ ገደብ መጣል ይገኙባቸዋል ብሏል ሪፖርቱ።

በ38 አገሮች ውስጥ የከፉ ጥሰቶች ደርሰዋል፣

የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን አሰሳ አድሮጎ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በ38 አገሮች ውስጥ ከባድ የሐይማኖት ነጻነት ጥሰቶች መካሄዳቸውን ያስታወቀ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሃያ አንዱ በክርስቲያኖች ላይ ስቃይ፣ መከራና ስደት የሚያደርሱ ናቸው ተብሏል። ሪፖርቱ የእነዚህን አገሮች ስም ዝርዝር እንደሚከተለው አስቀምጦታል። አፍጋኒስታን፣ ሳውድ አረቢያ፣ ባንግላደሽ፣ ቢርማኒያ፣ ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያ፣ ኤርትራ፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ኒጀር፣ ናይጀሪያ፣ ፓክስታን፣ ፍልስጤም፣ ሶሪያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ቱርክመኒስታን፣ ኡዝቤክስታንና የመን መሆናቸው ታውቋል። መድሎ የሚያደርጉ አገሮችም አልጀሪያ፣ አዘርባዣን፣ ቡታን፣ ብሩኔይ፣ ግብጽ፣ የሩሲያ ፌደሬሽን፣ ኢራን፣ ካዛክስታን፣ ኪርጊዚስታን፣ ላኦስ፣ ማልዲቭስ፣ ማውሪታኒያ፣ ኳታር፣ ታጂክስታን፣ ቱርክ፣ ዩክሬንና ቬትናም መሆናቸውን ሪፖርቱ ይዘረዝራል።

ሁኔታው እጅግ ከሚያሳስብባቸው መንግሥታት መካከል፣

ጥናቱ በተካሄደባቸው 38 መንግሥታት ውስጥ በ17 ሁኔታው እጅግ ከሚያሳስብበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ሪፖርቱ ገልጾ በሰሜን ኮሪያ፣ በሳውድ አረቢያ፣ በናይጀሪያ፣ በአፍጋኒስታንና በኤርትራ፣ ሁኔታው ምንም ለውጥ እንዳላሳየ አስረድቶ ከዚህ የከፋ እንዳይሆን ያደረበትን ስጋት ገልጿል። የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ሪፖርት የእስላማዊ ታጣቂ አሸባሪ ቡድን አል ሻባብ በታንዛኒያና በኬንያ ላይ እየተዳከሙ መምጣታቸው ለክርስቲያኖች ተስፋን የሚሰጥ እንደሆነ ገልጾ እነዚህ ሁለት አገሮች ከ2008 እስከ 2010 ዓ. ም. ድረስ በክርስቲያኖች ላይ መከራና ስደት ከሚደርስባቸው አገሮች መካከል ከተቀመጡበት ተርታ ያወጣቸዋል ብሏል። በሌላ ወገን የአፍሪቃ፣ የመካከለኛው ምስራቅ አገሮችና የእስያ ጦር ሃይሎች በእስላማዊ መንግሥት ታጣቂዎችና በሌሎች የተለያዩ አሸባሪ ቡድኖች ላይ የዘረጉት የጥቃት ዘመቻ ውጤት እያስገኘ መምጣቱን ሪፖርቱ ገልጿል።

በአክራሪነትና በብሔረተኝነት መካከል፣

በተለያዩ አገሮች ውስጥ በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸም በደል በእስላማዊ አክራሪነትና በብሔረተኝነት እየታገዘ  መሆኑ  ቢስተዋልም እንደ ሪፖርቱ ገለጻ መሠረት አሳሳቢው አናሳ ቁጥር በሆኑ የክርስቲያን ወገኖች ላይ የሚፈጸም ጥቃትና ጥፋት እንደሆነ፣ አንዳንድ ጊዜም በክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የሃይማኖት ወገኖች ላይም በደል እንደሚደርስባቸው ሪፖርቱ አመልክቷል።

በሕንድ ያለው ሁኔታ ሲዳሰስ፣

በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸም ግፍ እንደ የአገሩ ይለያያል ያለው የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ሪፖርት፣ በሕንድ አገር በተለየ መልኩ በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸሙ ግፎች ከፍተኛ ሃይማኖታዊ ጥላቻን ያካተቱ መሆናቸውን ሪፖርቱ ገልጿል። አናሳ ቁጥር ያላቸው የክርስቲያን ወገኖች ለአገሪቱ አንድነት ጠንቅ ናቸው በማለት የሕንድ ፓርላማ አባል በቅርቡ የተናገሩትን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። ይህም የሕንድ ፌደራል መንግሥት ከሕንዱ እምነት ጋር የተዛመደ የብሔረተኝነት አስተሳሰብ ይዞ መምጣቱ እንደሚያረጋግጥ ሪፖርቱ ግልጽ አድርጓል። በስደትና መከራ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍን የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን እንዳስረዳው ብሔረተኝነት የግድ ከሐይማኖት ጋር መያያዝ የለበትም ነገር ግን መንግሥት በሐይማኖቶች ላይ ጥቃትና በደል ለመፈጸም ወይም የሐይማኖትን ነጻነት በጥብቅ ለመገደብ ሲያስብ የሚከተለው መንገድ እንደሆነ አስረድቷል።

በምእራቡ ዓለም ጸረ አይሁድነት እየጨመረ ነው፣

የጳጳሳት ፋውንዴሽን ሪፖርት፣ በምእራቡ ዓለም ጸረ አይሁድነት በአውሮጳ ውስጥ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁሞ ይህንንም ከእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች መበራከት ጋር አያይዞ ለምስክርነትም የአይሁዶች ቁጥር ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚደረሰባትን ፈረንሳይ በመጥቀስ በዚህች አገር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አይሁዶችንና የአይሁዳዊያን ተቋሞችን ያነጣተሩ ጥቃቶች ከእስላማዊ ታጣቂ ቡድኖች በኩል መሰንዘራቸውን አስታውሷል። በስደትና መከራ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍ የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን በማከልም በርካታ የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት በጦርነት የተፈናቀሉትንና የተሰደዱትን አናሳ ቁጥር ያላቸው የክርስቲያን ወገኖችን ወደ አገራቸው መልሶ ለማቋቋም ምንም ፍላጎት አለማሳየቱን ገልጿል።

የፋውንዴሽኑን ጋዜጣዊ መግለጫ የተከታተሉት፣

የጳጳሳት ፋውንዴሽን ጋዜጣዊ መግለጫን ከተከታተሉት መካከል በቅድስት መንበር የኢጣሊያ አምባሳደር ክቡር አቶ ፔትሮ ሰባስቲያኒ፣ በስደትና መከራ ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍ የሚያደርግ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት ክቡር አቶ ቶማስ ሔይንጀልደርንና የፋውንዴሽኑ የኢጣሊያ ዳይረክተር ክቡር አቶ አሌሳንድሮ ሞንተዱሮ ይገኙበታል። በተጨማሪም በግብጽ የኮፕት ስርዓተ አምልኮን በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የሚኒያ ሀገረ ስብከት ጳጳሳ ብጹዕ አቡነ ቡትሮስ ፋሂም አዋድ ሐና፣ በፓክስታን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ጠበቃና የመብት ተከላካይ አቶ ታባሱም ዩሳፍና፣ የጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ቃል አቀባይ ወይዘሮ ማርታ ፔትሮሲሎ መሆናቸው ታውቋል።

በስደትና መከራ ላይ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ድጋፍ የሚያደርግ ጳጳሳዊ የኢጣሊያ ዳይረክተር ክቡር አቶ አሌሳንድሮ ሞንተዱሮ፣ ቸልተኝነት ሽብርተኝነት ከሚያደርሰው ጥቃት ይበልጣል ብለው በክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰውን ስቃይና ስደት ማውገዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

23 November 2018, 15:16