ፈልግ

Migranti: a Pozzallo fatti sbarcare in 184, hotspot pieno Migranti: a Pozzallo fatti sbarcare in 184, hotspot pieno  

በሮም ሀገረ ስብከት የስደርተኞች ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት የአራት ዙር የሥራ ዕቅዱን ይፋ አደረገ።

በሮም ሀገረ ስብከት የስደርተኞች ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ሞንሲኞር ፔርፓውሎ ፈሊኮሎ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስረዱት ስደትን አስመልክቶ በሚናፈሱ የተሳሳቱ ሃሳቦች ሕዝቡ እንዳይወናበድ፣ ፍርሃት ውስጥ እንዳይገባ አሳስበው ስደተኞች ለሚኖሩበት አገር ሃብት እንደሆኑ፣ ስደተኞችን መቅረብና ማነጋገር የዕውቀት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአራት ዙር የሚጠናቀቁ የሥራ ዕቅዶች በሮም ሀገረ ስብከት የስደተኞች ሐዋርያዊና ማህበራዊ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት መዘጋጀቱ ታውቋል። የሮም ሀገረ ስብከት የስደተኞች ሐዋርያዊና ማሕበራዊ ጽሕፈት ቤት የውይይት መድረኮችን ከሀገረ ስብከቱ የሐዋርያዊ ተልዕኮ ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን በጋራ ማዘጋጀቱ ታውቋል። እነዚህ ሁለቱ ጽሕፈት ቤቶች በየጊዜ ተገናኝተው በሮም ሃገረ ስብከት ውስጥ ስለሚገኙ ስደተኞች ሐዋርያዊና ማሕበራዊ ሕይወታቸውን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን እንደሚያደርጉ ታውቋል።   

ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስም ሆነ በትውልድ አገር የመኖር ነጻነት፣

ቅዳሜ ሕዳር 15 ቀን 2011 ዓ. ም. ሊካሄድ የታቀደው የመጀመሪያ ዙር የውይይት ርዕስ “ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስም ሆነ በትውልድ አገራቸው የመቆየት ነጻነት” የሚል እንደሆነ ታውቋል። በሮም ሀገረ ስብከት የስደርተኞች ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ሞንሲኞር ፔርፓውሎ ፈሊኮሎ የመጀመሪያ ዙር የውይይት ርዕስን በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያቸው እንዳስገነዘቡት ምንም እንኳን የስደት ጉዞ ወይም ሕይወት አስቸጋሪና አደገኛ ቢሆንም ስደተኞች የሕይወት ዋስትናና ከለላ ፍለጋ ወደ ሌላ አካባቢ ወይም አገር መንቀሳቀስ አስፈላጊ እነደሆነ ገልጸው ነገር ግን ሰዎች በተወለዱበት አካባቢ የማደግ፣ በሰላም የመኖርና የመበልጸግ መብታቸው የተከበረ ቢሆን ይመረጣል ብለዋል። ሞንሲኞር ፈሊኮሎ ስደተኞችን በተመለከተ ተከታታይ የውይይት ዕቅዶች መውጣታቸውን ገልጸው በየካቲት 30 2011 ዓ. ም. ስደተኞችና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች፣ መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ. ም. በውጭ አገር ለሚገኙ ሚሲዮናዊያን የሕይወት ዋስትና፣ በመጨረሻም በመጋቢት 28 ቀን 2011 ዓ. ም. የተለያዩ ሐይማኖቶችና የስደት ምክንያቶች በሚል ርዕስ ውይይት እንደሚደረግ አስረድተዋል።

ሮም እንግዳ አስተናጋጅ ከተማ፣

በሮም ሀገረ ስብከት የስደርተኞች ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑት ሞንሲኞር ፔርፓውሎ ፈሊኮሎ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስረዱት ስደትን አስመልክቶ በሚናፈሱ የተሳሳቱ ሃሳቦች ሕዝቡ እንዳይወናበድ፣ ፍርሃት ውስጥ እንዳይገባ አሳስበው ስደተኞች ለሚኖሩበት አገር ሃብት እንደሆኑ፣ ስደተኞችን መቅረብና ማነጋገር የዕውቀት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል። ሞንሲኞር ንግግራቸውን በመቀጠል የሮም ከተማ ምን ጊዜም ቢሆን ስደተኞችን በእንግድነት ተቀብላ በማስተናገድ የምትታወቅ ከተማ እንደሆነች ገልጸው፣ በጦርነት የተጎዱ የበርካታ አገሮች ስደተኞችን በመቀበል ወደሌሎች አገሮች ወይም ሀገረ ስብከቶች በማዛወር የምትታወቅ መሆኗን አስታውቀዋል። ሞንሲኞር ፈሊኮሎ በማከልም በፈቃደኝነት የሚደረግ አገልግሎት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ተልዕኮ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ማሕበራት፣ እንቅስቃሴዎችና ተቋማት ግዴታ እንደሆነ ገልጸው ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ የስነ ምግባር እድገትና የስልጣኔ ምልክት ነው ብለዋል።        

14 November 2018, 14:54