ፈልግ

International Sheroes Forum in Monrovia International Sheroes Forum in Monrovia 

በዳካር የዓለም ካቶሊካዊ ሴቶች ሕብረት ጉባኤ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።

የጉባኤው ተካፋዮች እንደገለጹት በአንድ አገር ውስጥ ሰላም በሚጠፋበት ጊዜ በቅድሚያ የሚጠቁት ሴቶችና ሕጻናት መሆናቸውን፣ የሴነጋል ካቶሊካዊ ሴቶች ማሕበራት ቃል አቀባይ የሆኑት ወይዘሮ አን ማሪ ማንሳሊ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ. ም. ጀምሮ፣ በሴነጋል ዋና ከተማ ዳካር፣ ከ35 አገሮች የተወጣጡ የዓለም ካቶሊካዊ ሴቶች ሕብረት የተካፈሉበት ጉባኤ እየተካሄደ መሆኑን ከስፍራው የተላከልን ዜና ገልጿል። ከዕለም የተወጣጡ ሴቶች “የዓለም ካቶሊካዊ ሴቶች ሰላም ለጠማው ዓለም ሕያው ውሃን ያቀርባሉ”  በሚል ርዕሥ ጉባኤያቸውን በዳካር በማካሄድ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

በጉባኤው መካከል የዳካር ሊቀ ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ቤንጃሚን ንዲያዬ እና የሴነጋል ፕሬዚደንት ክቡር ማኪ ሳል እና ጥሪ የተደረገላቸው የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑ የሴነጋል ሴቶች በእንግድነት መገኘታቸው ታውቋል።

የጋር ስጋትን የምንጋራበት ጉባኤ ነው፣

ጉባኤው፣ ካቶሊካዊ ሴቶችን ካሳሰቧቸው ችግሮች መካከል፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እጥረት፣ ልማትና ሰላም፣ በሚሉ የጋራ ስጋቶች ላይ ለመወያየት ዕድልን ያመቻቸ ነው ተብሏል። የጉባኤው ተካፋዮች እንደገለጹት በአንድ አገር ውስጥ ሰላም በሚጠፋበት ጊዜ በቅድሚያ የሚጠቁት ሴቶችን ሕጻናት መሆናቸውን፣ የሴነጋል ካቶሊካዊ ሴቶች ማሕበራት ቃል አቃባይ የሆኑት ወይዘሮ አን ማሪ ማንሳሊ   ገልጸዋል።  

በካቶሊካዊ ሴቶች ማሕበራት መካከል ያለውን ሕብረት ማጠናከር፣

ወይዘሮ አን ማሪ ስለ ጉባኤው ዓላማ ሲገልጹ፣ በካቶሊካዊ ሴቶች ማሕበራት መካከል ያለውን አንድነትና መተጋገዝ ለማሳደግ እንደሆነ አስረድተው፣ አንድነታቸውም በውሃ በመመሰል በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ቀጣይነት እንዲኖረው፣ በሃብት የሚበልጧቸው የከተማ ሴቶች በገጠር ያሉትን ሴቶች የሚረዱበትን መንገድ ለማመቻቸት እንደዚሁም የአውሮጳ ሴቶች የአፍሪቃ አህጉር ሴቶችን የሚረዱበትን መንገድ ለማመቻቸት እንደሆነ ገልጸዋል።

የአፍሪቃ ጦርነቶች ቀዳሚ የውይይት ርዕስ፣

የወንጌል ህያው ውሃ በጉባኤው የመወያያ ርዕስ የተካተተበት ዋናው ምክንያት ለአፍሪቃ አገሮች ከጦርነት ይልቅ ሰላም እንደሚያስፈልግ፣ ጦርነቶች በሚካሄዱባቸው የአፍሪቃ አገሮች የመጀመሪያ ተጠቂዎች ሴቶች መሆናቸውን የጉባኤው ተካፋዮች ገልጸዋል። የዓለም ካቶሊካዊ ሴቶች ሕብረት፣ የአፍሪቃ መንግሥታት ድህነትን ለመቀነስና ጦረነትንና ሽብርተኝነትን ለማስቆም ብለው ለሚያደርጉት ጥረቶች ቅድሚያን እንዲሰጡ ለማሳሰብ እንደሆነ ታውቋል።

በዓለም ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሴቶች ምሕበራት አሉ፣

ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ሴቶች ሕብረት የተመሠረተው እ. አ. አ. በ1910 ዓ. ም. ሲሆን ዋና ዓላማውም በቤተክርስቲያንና በሕብረተሰብ መካከል ሴቶችን በማሳተፍ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ እንደሆነ ታውቋል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በዓለም ዙሪያ፣ በካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሥር የተመሠረቱት በመቶዎች የሚቆጥሩ የካቶሊካዊ ሴቶች ማሕበራት፣ በ66 አግሮች ዘንድ ተደራጅተው መኖራቸው ታውቋል።   

23 October 2018, 16:57