ፈልግ

የ15ኛው አጠቃላይ መደበኛ ሲኖዶስ አባቶች ለወጣቱ ያስተላለፉት መልእክት

ከባለፈው መስከረም 23/2011 ዓ.ም እስከ እሁድ ጥቅምት 18/2011 ዓ.ም “ወጣቶች፣ እምነት እና በጥሪ ላይ በማስተዋል ጥበብ የተሞላ ውሳኔ ማድረግ” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የነበረው 15ኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን አጠቃላይ መደበኛ የብጹዕን ጳጳሳት ሲንዶስ በትላንትናው እለት ማለትም በጥቅምት 18/2011 ዓ.ም መጠናቀቁ ይታወሳል።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

የዚህ 15ኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን ብጹዕን ጳጳሳት አጠቃላይ መደበኛ ሲንዶስ ላይ ተሳታፊ የነበሩት የቤተ ክርስትያን አባቶች በዚህ ሲኖዶስ ማብቂያ ላይ ለወጣቱ ትውልድ አንድ ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወሳል። በዚህ 15ኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን አጠቃላይ መደበኛ የብጹዕን ጳጳሳት ሲንዶስ ተካፋይ የነበሩ የቤተ ክርስትያን አባቶች ለወጣቶች የጻፉትን ደብዳቤ ሙሉ ይዘት እንደ ሚከተለው ተርጉመነዋል አብራችሁን በመሆን እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

እኛ የ15ኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስትያን አጠቃላይ መደበኛ የብጹዕን ጳጳሳት ሲንዶስ ተካፋይ አባቶች በዓለም ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች ሁሉ በተስፋ፣ በመተማመን እና በመጽናናት መንፈስ ይህንን መልእክት እንጽፍላችኋለን። በእነዚህ ቀናት “ለዘለዓለም ወጣት የሆነውን” የኢየሱስን ድምፅ ለመስማት እና በእርሱ ውስጥ የእናንተን ብዙ ድምጾች፣ የእናንተን የደስታ ድምጾች፣ የእናንተን ለቅሶዎች እና የእናንተን የጸጥታ ጊዜያት ለመስማት አንድ ላይ ተሰብስበን ነበር።

የእናንተን ውስጣዊ ፍለጎቶች፣ ደስታችሁን እና ተስፋዎቻችሁን፣ ህመማችሁን እና እንድትቃትቱ የሚያደርጋችሁን ምኞቶቻችሁን ሁሉ እናውቃቸዋለን። አሁን ደግሞ እኛን ቃላት እንድትሰሙ እንፈልጋለን፡ የእናንተ ፍላጎት እውን ይሆን ዘንድ የእናንተ ደስታ ተካፋዮች ለመሆን እንፈልጋለን። ለሕይወት ያላችሁን ቅንዓት፣ ሕልማችሁ እውን እንዲሆን እና በታሪክ ውስጥ ቅርፅን እንዲይዝ በሚደርገው ጥረት ተሳታፊ ለመሆን ዝግጁ ነን።

የእኛ ድክመቶች እናንተን ሊያግዳችሁ በፍጹም አይገባም፣ ስህተቶቻችን እና ኃጢያቶቻችን እናንተ በእኛ ላይ ላላችሁ መተማመን እንቅፋት መሆን የለባቸውም። ቤተ ክርስቲያን እናታችሁ ናት፡ እናንተን በፍጹም ልትረሳ አትችልም፣ እናንተ በአዳዲስ መንገዶች ላይ፣ የመንፈስ ቅዱስ ንፋስ እየጠነከረ በሚንፍስባቸው ወይም በሚሄድባቸው ከፍተኛ መንገዶች ላይ በምትጓዙበት ወቅት ከእናንተ ጋር አብራ ለመጓዝ ዝግጁ ናት - ይህም የቸልተኝነት፣ የታይታን እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይደመስሳል።

እግዚኣብሔር አምላክ አንደኛ ልጁን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አሳልፎ እስከ መስጠት ድረስ የወደዳት ዓለማችን ለቁሳዊ ነገሮች፣ ለአጭር ጊዜ ስኬቶች፣ ለጊዜያዊ ደስታ እና ዓለም ደካማ የሆኑትን ሁሉ ሲደስቅ እናንተ ይህ ነገር እንዲታረም እና እንደገና እንዲነሳሳ በማድረግ ወደ ፍቅር፣ ውበት፣ እውነት፣ እና ፍትህ እንደገና መመልከት ይኖርባችኋል።

ለአንድ ወር ያህል ከእናንተ ከአንዳንዶቹ ጋር እና እንዲሁም ከተለያዩ ብዙ በጸሎት እና በፍቅር ከእኛ ጋር ከነበሩ ሰዎች ጋር አብረን ተጉዘናል። ጌታ ኢየሱስ ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርት አድርጎ ወደ ምልከን እያንዳንዱ የምድር ክፍል ጉዞውን መቀጠል እንፈልጋለን።

ቤተክርስቲያን እና አለም የእናንተን ፍላጎቶች ይሻሉ። ለጉዳት ተጋላጭ ለሆኑ፣ ለድኾች እና በሕይወት ጉዞዎቻቸው ከተጎዱ ሰዎች ጋር አብራችሁ ለመጓዝ ሞክሩ።

ዘመኑ የእናንት ነው፣ ብርህ ተስፋ ይኑራችሁ!

ጥቅምት 28/2011 ዓ.ም

29 October 2018, 08:23