ፈልግ

2018.09.14 Messa di apertura Ccee nella Chiesa dei gesuiti di Poznan 2018.09.14 Messa di apertura Ccee nella Chiesa dei gesuiti di Poznan 

የአውሮጳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ቀዳሚ ዓላማቸው መተባበር እንደሆነ ገለጹ።

የአውሮጳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከርና እርሳቸውን በጸሎት ማገዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

 የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የፖላንድ ከተማ በሆነችው በፖዝናኝ፣ ከመስከረም 3 እስከ መስከረም 6 ቀን 2011 ዓ. ም. የተሰበሰበው የአውሮፓ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት፣ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፈው መልዕክቱ ከሁሉ በፊት የአውሮጳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከርና እርሳቸውን በጸሎት ማገዝ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። የአውሮጳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት በመልዕክቱ እንደገለጸው በአውሮጳ አገሮች ለሚገኙ ወጣቶች ልዩ ትኩረትን በመስጠት ድጋፍ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በአውሮጳ ውስጥ የሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶችና ቁምስናዎች አንድነታቸውንና ግኑኙነታቸውን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጽኑ ማሳሰባቸውን ገልጸዋል። የአውሮጳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት በማከልም የዘንድሮን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤን ያዘጋጀውን የፖዝናኝ ሀገረ ስብከትንና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳሳት የሆኑትን ብጹዕ አቡነ ስታንስላው ጋዴስኪን አመስግኗል። ምክርቤቱ ዘንድሮ በፖላንድ ያካሄደው ስብሰባ፣ በአውሮጳ ውስጥ የወንጌል ተልዕኮ አገልግሎት ለማበርከት የገቡትን ቃል ኪዳን ለማደስ ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረም ገልጿል። ከሁለት አስከፊ የዓለም ጦርነቶች በኋላ የአውርጳ አገሮች በመካከላቸው መግባባትን በመፍጠር፣ ክርስትያናዊ የእርስ በርስ ግንኙነትና ትብብር ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው እንዳሳሰቡት እንደ ቤተክርስቲያን አባቶች ተልዕኮአችን በቅርብም ሆነ በሩቅ ሆነው የሚሰቃዩትን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጩሄት ከልብ እንድናዳምጥ ይጠይቀናል ብለው፣ በስፋት ለመወያየት ዕድል ከተሰጡባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል አንዱ የበጎ አድራጎት ስራ አስፈላጊነት ላይ ትኩረት መስጠት እንደሆነ ገልጸዋል። በአውሮጳ ውስጥ የበጎ አድራጎት ስራ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናንን በፍቅር በማሳተፍ በድህነትና በሌሎች ማሕበራዊ ችግሮች ምክንያት ከሕብረተሰቡ መካከል የተገለሉ በርካታ ችግረኞችን ለማገዝ እንደሚያስች ገልጸው ይህም በቤተክርስቲያን የሕይወት ምዕራፍ አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል። ምዕመናን በበጎ አድራጎት ስራ ላይ በመሰማራት በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሰውን የመልካም ሳምራዊ ምሳሌን ለመሆን ያስችላቸዋል ብለዋል። የአውሮጳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በማከልም በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ክርስቲያኖች በያሉበት አገር በማሕበርም ሆነ በግል ተነሳሽነት ራሳቸውን ያዘጋጁ ከሆነ በምስጋና በመቀበል የሚያስፈልጋቸውን  ሁሉ ለማድረግ ዝግጁዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአውሮጳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በመልዕክታቸው እንዳስገነዘቡት ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውንን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታማኝነትና በብቃት ለማቅረብ ራሳቸውን በቅዱስ ቃሉ እና በቅዱሳት ምስጢራት በማሳደግ፣ በመንፈሳዊ መነቃቃት ምስክርነትንም መስጠት እንደሚያስፈልጋቸው አስረድተዋል። ፍጥረታትን ወደ መልካም ጎዳና ለመመለስ የእምነት ተሞክሮ እና የፍቅር አገልግሎት የተሳሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ብጹዓን ጳጳሳት ይህም በርካታ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመድረስ እንደሚያግዝ ገልጸው ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያዊ አገልግሎትን ለማነቃቃትና ለዘመናዊ ድህነት የወንጌል ምስክርነትን ለመስጠት ያግዛል ብለዋል። ከወንጌል የሚገኝ ደስታ የተሰኘውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን የጠቀሱት ብጹዓን ጳጳሳት በማከልም ለፍጥረት ሊሰጥ የሚገባው ክብር እየጎደለ መምጣቱ፣ የቤተሰብ መለያየት እየጨመረ መምጣቱ፣ የጾታ ባህል በሕብረተሰብ ላይ ጫና ማድረግ፣ የሐይማኖት ነጻነት መገደብ፣ የስደትና የጥገኝነት ጠያቂ ቁጥር እየተበራከተ መምጣት እነዚህንና ሌሎችንም ችግሮች ለመቋቋም የእምነት ተሞክሮ እና የፍቅር አገልግሎት አንድ ላይ መሆን እንዳለባቸው አስረድተዋል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የአብያተ ክርስቲያናት አንድነት መጎልበት እንዳለበት፣ በሃይማኖቶች መካከል የሚደረጉ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና ከሲቪል ማሕበረሰብ ጋር የሚደረግ ውይይትም መጠናከር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። የአውሮጳ አህጉር እየደረሰበት ያለው ችግሮችና ውጥረት ለማርገብ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያላቸውን እምነት ገልጸው፣ በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የሚሳተፉ ምዕመናን አንድነትን በማደስ፣ ፍትሕንና ሰላምን ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት ጉልህ አስተዋጽዖ ሊያበረክት እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የሕዝቦች አንድነትና መተጋገዝ የቅድስት ስላሴን የፍቅር ባሕርን ያንጸባርቃል ያሉት ጳጳሳት እያንዳንዱ ሰው የቅድስት ስላሴን መልክ የተላበሰ በመሆኑ በምንም ሊተካና ሊወዳደር የማይችል ክብር እንዳለው ገልጸው እንደ ቤተክርስቲያን መጠራታችን የማያቋርጥ የፍቅር መታደስን በማሳየት፣ በመንፈስ ቅዱስ የጸጋ ስጦታዎች በመታገዝ፣ በአህጉሩ ክርስቲያናዊና ካቶሊካዊ ባሕልን በመከተል የእርዳታ አገልግሎታችንን ማበርከት ያስፈልጋል ብለዋል። ይህን በተመለከተም የዘንድሮ የአውሮጳ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ስብሰባ ያስገኟቸውን ፍሬዎች በመጠቀም ቤተክርስቲያናችን ተግባራዊ ልታደርጋቸው የምትችልባቸውን ሌሎች የአንድነት ጎዳናዎችን መከተል ያስፈልጋል ብለዋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ የስደተኞችን ጉዳይ አስመልክተው ባደረጉት ውይይታቸው የአውሮጳ አገሮች መንግሥታት የሚወስዱትን የተለያዩ ውሳኔዎችን ከቅዱስ ወንጌል እይታ ጋር ያገናዘቡ መሆናቸውን ገልጸው የጂኦፖለቲካ ጠበብት ባይሆኑም ነገር ግን ሐዋርያዊ አባቶች በመሆናችን የእያንዳንዱን ሰብዓዊ ሕይወት ሁኔታ የመከታተል አደራ ተጥሎብናል ብለዋል። በማከልም የሰደተኞችና የጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳይ ውስብስብ መሆኑን ብንገነዘብም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በመወያየት ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮችን ለማቃለል በጋራ ከመሥራት በቀር ሌላ አማራጭ አይገኝለትም ብለው የተገኙትን አጋጣሚዎች በሙሉ በመጠቀም ለስኬታማነት ጥረት እናደርጋለን ብለዋል። የአውሮጳን አህጉር የተጠናወተው የግለኝነት ባሕል፣ ከስብዓዊ ባሕርይ ይልቅ ወደ ኤኮኖሚው አስተሳሰብ ስለሚያዘነብል ይህም የአንድነትንና የመተጋገዝን ዓላማ በማዳከም ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች  ለአውሮጳ አገሮች እንደሸክም ሆነው እንዲቆጠሩ አድርጓል ብለዋል።


ብጹዓን ጳጳሳቱ በመጨረሻም የሐዘንተኞች እናት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጸጋዋ የአውሮጳ አህጉርን እንድትጠብቅና ይህን አህጉር ለመርዳት በምናደርገው ጥረት ሁሉ እንድታግዘን በጸሎት እንጠይቃታለን ብለዋል።                  

17 September 2018, 08:38