ፈልግ

ETIOPIA Assemblea Plenaria di AMECEA ETIOPIA Assemblea Plenaria di AMECEA 

የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ለትምህርተ ክርስቶስ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ምዕመናን ስለ እምነታቸው ጠለቅ ያለ እውቀት ኖሮአቸው ክርስቲያናዊ ሕይወታቸውን ማሳደግ እንዲችሉ ለማድረግ፣ የምዕመናንን የሐዋሪያዊ አገልግሎት ጥሪን ለመንከባከብ፣ በማሕበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በብቃት ሊሳተፉ የሚችሉ መንፈሳዊ መሪዎችን ለማዘጋጀት፣ ሴቶች በማሕበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ለሚጫወቱት ሚና እውቅናንና አክብሮትን መስጠት ያስፈልጋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ በጥቅምት ወር ላይ በቫቲካን ከተማ ሊካሄድ በታቀደው ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት 15ኛ መደበኛ ሲኖዶስን በተመለከተ ለመወያየት በናይሮቢ ኬንያ የተሰበሰቡት የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ለትምህርተ ክርስቶስ ትኩረት እንዲሰጥ ማሳሰባቸው ታውቋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ በምስራቅ አፍሪቃ አገሮች በሚገኙ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ለጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትኩረት እንዲሰጥ የተፈለገበትን ምክንያት ሲገልጹ፣ ምዕመናን ስለ እምነታቸው ጠለቅ ያለ እውቀት ኖሮአቸው ክርስቲያናዊ ሕይወታቸውን በማሳደግ ከሌሎች የእምነት ተቋማት የሚደርስባቸውን ጥቃት መቋቋም እንዲችሉ ለማድረግ፣ የምዕመናንን የሐዋሪያዊ አገልግሎት ጥሪን ለመንከባከብ፣ በማሕበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በብቃት ሊሳተፉ የሚችሉ መንፈሳዊ መሪዎችን ለማዘጋጀት፣ ሴቶች በማሕበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ለሚጫወቱት ሚና እውቅናንና አክብሮትን ለመስጠት እንደሆነ አስረድተዋል።

በናይሮቢ ኬንያ የተካሄደው የምስራቅ አፍሪቃ ብጹዓን ጳጳሳት ስብሰባ ሰፊ ትኩረት ከሰጡባቸውው ሐዋርያዊ የመወያያ ርዕሶች መካከል፣ በአካባቢው አገሮች የትምህርትና የስልጠና እድሎችን ማዘጋጀት፣ ሁለገብ ማሕበራዊ እድገቶች እንዲመዘገቡ ማድረግ፣ ካቶሊካዊ ተቋማትን በስልጠና ማሳደግ፣ የዲጂታል መገናኛ መሣሪያ አጠቃቀምን በተመለከተ ለወጣቶች በቂ ግንዛቤን መስጠት፣ የወጣቶችን ማሕበራዊና መንፈሳዊ ሕይወት በቅርብ በመከታተል የሚሉ እንደሚገኙበት የምሥራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ኅብረት ሐዋርያዊ ሥራ መምሪያ አስተባባሪ ክቡር አባ አማኑኤል ቺሞምቦ ለፊደስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ጳጳሳቱ የወጣቶችን የሥራ እጦት፣ የትምህርት ዕድል፣ ጦርነት፣ አመጽ፣ ስደት፣ ቤተሰብ፣ በማሕበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወት የወጣቶች ሚና የሚሉ ይገኙባቸዋል። በመጭው ጥቅምት ወር የወጣቶችን ጉዳይ በስፋት በሚመክረው 15ኛው የመላው ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ላይ ከምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ አባል አገሮች ተወካዮች እንደሚገኙ ታውቋል።

ዋና ጽሕፈት ቤቱን ናይሮቢ ኬንያ ያደረገው የምስራቅ አፍሪቃ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሕብረት አባል አገሮች ዘጠኝ ሲሆኑ እነርሱም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ማላዊ ሲሆኑ ተባባሪ አባል አገሮችም ጂቡቲ እና ሶማሊያ መሆናቸው ታውቋል።

18 September 2018, 17:31