ፈልግ

2018.09.03 Udienza Papa Francesco Vescovi del Sudan e Sud Sudan 2018.09.03 Udienza Papa Francesco Vescovi del Sudan e Sud Sudan 

የሰሜን ሱዳን ቤተክርስቲያን መሠረቷን በቅዱስ ወንጌል ላይ ያደረገች መሆኗ ተነገረ።

የካርቱም ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ዲዲ ሲመልሱ የሱዳን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፍሬ የሆኑትን በመላው ዓለም እጅግ የተወደዱ የተከበሩ ሁለቱን ቅዱሳን፣ ቅድስት ባኪታንና ቅዱስ ኮምቦኒን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዓለሙ አቀፉ ሚዲያዎች ብዙ ሲወራ የማንሰማት የሰሜን ሱዳን ሪፑብሊክ፣ 97 ከመቶ የእስልምና ተከታዮች ያሏት፣ የተቀሩት ደግሞ የክርስትናና የባሕላዊ እምነቶች ተከታዮች መሆናቸውን በሱዳን የካርቱም ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ዲዲ አድጉም ማንጎሪያ ለቫቲካን ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

በሰሜን ሱዳን የሚገኙ ክርስቲያኖች ወይም ካቶሊኮች ሁኔታ ምን እንደሚመስል ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የካርቱም ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ዲዲ ሲመልሱ የሱዳን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ፍሬ የሆኑትን በመላው ዓለም እጅግ የተወደዱ የተከበሩ ሁለቱን ቅዱሳን፣ ቅድስት ባኪታንና ቅዱስ ኮምቦኒን አስታውሰዋል።

ቅድስት ባኪታንና ቅዱስ ኮምቦኒን የቤተክርስቲያን ስጦታዎች ናቸው፣

ቅድስት ጆሴፊን የሱዳን ሕዝብና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ውስጥ ገብተው ማምለጥ ለቻሉት በሙሉ ባልደረባ እንደሆነች ታውቋል። ቅድስት ጆሴፊን ባኪታ የተወለደችው በዳርፉር ግዛት ሲሆን በዓሏ ተከብሮ የሚውለው የካቲት 1 እንደሆነ ታውቋል። ሌላው ኢጣሊያዊ ተወላጅ ዳንኤል ኮምቦኒ፣ የቅዱስ ኮምቦኒ ሚሲዮናዊያን ዓለም አቀፍ ማህበር መስራች ሲሆን ለአፍሪቃ የተለየ ፍቅር እንዳለው ይታወቃል። ስለ አፍሪቃ እምብዛም በማይወራበት ዘመን ስለ አፍሪቃ ሕዝቦች እድገት የተናገረ እና ይዞት የተነሳው ዓላማም “አፍሪቃ በአፍሪቃዊያን ትድናለች” የሚል እንደነበር ይነገራል። በዓሉ ተከብሮ የሚውለው መስከረም 30 እንደሆነም ታውቋል።

ባለፉት ዓመታት ስለ ደቡብ ሱዳን እንጂ ስለ ሰሜን ሱዳን ብዙ ሲወራ አይሰማም፣ በሰሜን ሱዳን ሪፑብሊክ አነስተኛ የሆኑ የክርስቲያን ወግኖች ሁኔታ ምን ይመስላል ተብለው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ለቀረበላቸው ጥያቄ የካርቱም ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ዲዲ አድጉም ማንጎሪያ ሲመልሱ በሰሜን ሱዳን፣ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው ያለው ተቆርቋሪነት ጠንካራ መሆኑን ገልጸው ከሌሎች ሐይማኖቶች ጋር ያለው ሰላማዊ ግንኙነት በመልካም ደረጃ ላይ እንዳለ አስረድተው፣ ችግሮች የሉም ማለት እንዳልሆነ ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ዲዲ ከ1997 ዓ. ም. በፊት በሰሜናዊው የሃገሪቱ ክፍል የክርስቲያኖች ቁጥር በርካታ እንደነበር ተናግረው፣ ሱዳን ለሁለት ከተከፈለችበት ከ2003 ዓ. ም. ወዲህ የክርስቲያኖች ቁጥር መቀነሱን አስረድተዋል። በደቡብ ሱዳን ጦርነት ሲቀሰቀስ ነዋሪዎች አካባቢዉን ለቀው ወደ ሰሜን ስለተሰደዱ ከ2005 ዓ. ም. ጀምሮ የክርስቲያኖች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል። የሱዳን ሪፑብሊክ ትልቁ ችግር ድህነት እንደሆነ የገለጹት ሊቀ ጳጳሳት ሚካኤል በዚህች አገር በገጠራማው አካባቢ የሚኖሩት ሕዝቦች የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ተናገረዋል። እነዚህም በአካባቢያቸው ጦርነት ሲቀሰቀስ ወደ ትላልቅ ከተሞች እንደሚመጡና ቀድሞ ከለመዱት የግብራና ሥራ የተለየ ሕይወት ስለሚያጋጥማቸው የድህነት ሕይወት ለመኖር እንደሚገደዱ አስረድተዋል።

ለምዕመናኑ የሚሰጥ ሐዋርያዊ አገልግሎት በካህናት እጥረት የተነሳ መዳከሙን ጠቅሰው ሚሲዮናዊያንን የመጋበዝ ፍላጎት ቢኖርም ወደ ሱዳን ለመምጣት ፍቃድ በቀላሉ አይገኝም ብለዋል። በሃገሪቱ ውስጥ በሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ ለተሰማሩትም ቢሆን የመኖሪያ ፍቃድ ማሳደስ ውጣ ውረድ የበዛበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ክርስቲያኖች በእምነታቸው ላይ የሚገጥማቸው ችግር ያለ እንደሆነደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሚካኤል ዲዲ በሰጡት መልስ፣ የሱዳን ሕዝብ ሰላም ወዳድና እንግዳ ተቀባይ እንደሆነ አስረድተዋል። የሃገሪቱ ሕገ መንግሥት ክርስቲያኖችን የሚያገልል እንደሆነና ለሱዳን የመንግሥት ባለስጣናት በተደጋጋሚ ቢነገራቸውም ሊቀበሉት አልፈለጉም ብለዋል።                       

11 September 2018, 18:17