ፈልግ

2018.09.03 Madre Teresa Shen Nene Tereza 2018.09.03 Madre Teresa Shen Nene Tereza 

ማዘር ተሬዛ ቅድስት የተባለችው ለድሆች ባበረከተችው የፍቅር ሥራ ነው።

የማዘር ተሬዛ ቀዳሚ የአገልግሎት ዓላማ በድህነት ምክንያት የሚቸገሩትን፣ መጨረሻቸው ከሞት በስተቀር ሌላ ምንም ዕድል የሌላቸውን፣ መጠለያ አጥተው መንገድ ላይ የወደቁትን ለመሰብሰብ፣ እግዚአብሔር የሰጣቸው ሰብዓዊ ክብር እንዳይነካባቸው ወይም እንዳይነፈግባቸው መጠበቅ ነበር።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች የደረሰባቸውን ከእነዚህም መካከል የተራቡትን፣ የተጠሙትን፣ የታረዙትን፣ የታመሙትንና ሌሎች ማሕበራዊ ችግሮች የደረሰባቸውን ለመርዳት፣ ለማጽናናትና ተስፋን ለመስጠት በማለት ሕይወቷን ለሌሎች አገልግሎት የሰጠች ማዘር ተሬዛ፣ በመልካም ሥራዋ በዓለም ዙሪያ በብዙዎች ዘንድ ትታወቃለች። ይህ ብቻም ሳይሆን የእርሷን የሕይወት ፈለግ ለመከተል፣ ዕድሜ አቸውን በሙሉ ሌሎችን ለማገልገል ፍላጎት ያደረባቸውና ጥሪው የደረሳቸው ሌሎችም እህቶችም የሚኖሩበትን ዓለም አቀፍ ማሕበር መስርታለች።    

መላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ማዜር ተሬዛ በዓለም ዙሪያ ለድሆችና ለተናቁትና ለተገለሉት ሰዎች ያበረከተችውን የፍቅር አገልግሎት በማጤን ከሁለት ዕመት በፊት ማለትም ነሐሴ 29 ቀን 2006 ለቅድስና መብቃቷን በይፋ አውጃለች። በዛሬው ዕለት ዝግጅታችን ማዘር ተሬዛ ለቅድስና የበቃችበት ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከአገልግሎቶቿ መካከል አንዳንዶችን ለማስታወስ እንፈልጋለን።    

“ከሁሉ የማዘር ተሬዛ ቀዳሚ የሕይወት ጉዞ ዓላማ በድህነት ምክንያት የሚቸገሩትን፣ መጨረሻቸ ከሞት በስተቀር ሌላ ምንም ዕድል የሌላቸውን፣ መጠለያ አጥተው መንገድ ላይ የወደቁትን ለመሰብሰብ፣ እግዚአብሔር የሰጣቸው ሰብዓዊ ክብር እንዳይነካባቸው ወይም እንዳይነፈግባቸው ለመጠበቅ ነው። ይህን ተልዕኮ ለማሳካት ማሕበራዊ ችግር እጅግ ግልቶ በሚታይባቸው አካባቢዎች በመሄድ፣ እግዚአብሔር ለተጨነቁት፣ ለተቸገሩትና ለተናቁት ሰዎች ያለውን ፍቅር በተግባር በመግለጽ ታገለግላቸው ነበር። ምናልባትም ቅዱስ ብለን ልንጠራት ላይመቸን ይችላል። ምክንያቱም እርሷን ቅድስት ያሰኛት አገልግሎቷ በእኛ መካከል በጉልህ ስለሚታይና ለእኛ በጣም የቀረበ በመሆኑ እንዳለፉት በርካታ ዓመታት ማዘር ተሬዛ እያልን ብንጠራት ይቀለናል።” በማለት የዛሬ ሁለት ዓመት፣ ነሐሴ 29 ቀን 2006 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመላዋ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ውስጥ የማዘር ተሬዛን ቅድስና ይፋ ባደረጉበት ንግግራቸው አስታውሰዋል። 

ቅድስት ማዘር ተሬዛ ማን ናት፣

የካልኩታዋ ቅድስት ማዘር ተሬዛ እውነተኛ የእምነት ምልክት ነበረች። በ18 ዓመት ዕድሜዋ ሌሎችን የማገልገል ተልዕኮን በመቀበል፣ ወደ ሎረቶ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተቋም በመግባት ማርያ ተሬዛ የሚል ስም ተሰጣት። በ1938 ዓ. ም. በባቡር ተሳፍራ ስትጓዝ ሳለ ድሆችን ለማገልግል ያነሳሳትን የአገልግሎት ጥሪን ተቀበለች። ከአራት ዓመት ቆይታ በኋላ የፍቅር ሥራ ልኡካን ማሕበር መሠረተች። ይህ ማሕበርም ማዘር ተሬዛ በሚኖሩበት፣ በሕንድ አገር በካልኩታ ሀገረ ስብከት እውቅናን አገኘ።

በድሆች ዓለም፣

በ1940 ዓ. ም. ታላቅ ደስታ በተመላበት መንፈስ የማሕበሯ መለያ የሆነውን፣ ሙሉ ነጭ ከሰማያዊ ቀጭን ጥለት ጋር የተሰራውን የምንኩስና ልብሷን ለበሰች። ይህን ልብስ ለብሳ በካልኩታ ከተማ ዳር እጅግ ደሃ ወደ ሆነው መንደር ሄደች። ደሆቹን፣ የተናቁትንና የተረሱትን ፈልጋ ለማገልገል በምትሄድበት ጊዜ በሙሉ በእጇ መቁጸሪያን በመያዝ ጸሎት ታደርስ ነበር። ከወራት በኋላም የእርሷ የቀድሞ ተማሪ የነበሩት ወደ እርሷ ዘንድ መጡ።

ዓለም በትኩረት ይመለከታት ነበር፣

ቅድስት ማዘር ተሬዛ ለመሠረተችው የፍቅር ሥራ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብጹዕ ጳውሎስ ስድስተኛ ዓለም አቀፋዊነት እውቅናን ከሰጡ በኋላ ቀድሞ ተወስኖ ከቆየበት ከሕንድ አገር በተጨማሪ ወደ ሌሎችም የዓለማችን ክፍሎች እንዲስፋፋ ተደረገ። በዚህም የቅድስት ማዘር ተሬዛ የፍቅር ሥራ ልጆች ማሕበር በዓለም ሕዝብ መካከል ተፈላጊነቱ እየጨመረ ሊመጣ ቻለ። በቁመናዋ ትንሽ ብትሆንም በምታበረክተው የፍቅር አገልግሎትዋ እምነት የሌላቸውንም ጨምሮ የመላውን ዓለም ሕዝብ ልብ ልትማርክ ቻለች። ለማሕበራዊ መገናኛ መንገዶች ምስጋና ይግባውና ቅድስት ማዘር ተሬዛ ለድሆች የምታከናውናቸው የፍቅር ሥራዎችዋ በዓለም ሕዝቦች መካከል ጎልቶ መታየት ቻለ። በተጨማሪም ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ጋር የነበራት መልካም ግንኙነት የነበራትን እውቅና አሳደገው።

ለኖቤል የሰላም ሽልማት መብቃት፣

በሁሉም የዓለም ክፍሎች፣ በድሆች መካከል ሆና ለድሆ ያደረገችው የፍቅር ሥራ በብዙዎች ዘንድ እውቅናን በማትረፉ በ1971 ዓ. ም.  ለሰላም የኖቤል ሽልማት እንድትታጭ አደረጋት። ለዓለም ሕዝብም ምስጋናን ካቀረበች በኋላ ያገኘችውን መልካም መድረክ በመጠቀም ጽንስ ስለማውረድ አስከፊነት የሚገልጽ ጠንከር ያለ የተቃውሞ መልዕክቷን ለዓለም ሕዝብ አስተላለፈች። በዚህ መልዕክቷም “አንድ እናት ልጇን እንድትገድል መብት ከተሰጣት ሌሎች ሰዎች እርስ በርስ እንዳይገዳደሉ የሚያግድ ምንድር ነው”? በማለት መናገሯ ይታወሳል።  ጽንስ የማውረድ ሕገወጥ ሥራን የሚቃወም ጠንካራ አቋሟን በማራመድ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኗ ይነገርላታል። ይህን አስመልክተው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ የማዘር ተሬዛን ብጽዕናዋ ባወጁበት እለት ባሰሙት ንግግር “እናት በሆዷ የያዘችዉን ጽንስ ለማስወረድ እንደምትፈልግ ከሰማችሁ እባካችሁ ወደ እኔ አምጡት፣ በእርሱ በኩል የእግዚአብሔርን ፍቅር መመልከት እችላለሁና”። በማለት ማዘር ተሬዛ የተናገረችውን መጥቀሳቸው ይታወሳል።

የማዘር ተሬዛ ብጽዕና፣

ማዘር ተሬዛ ካረፈች ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሕይወቷ እንዲጠና ብለው ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ በጠየቁት መሠረት አስፈላጊው ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ጥቅምት 6 ቀን 1996 ዓ. ም. የማዘር ተሬዛ ብጽዕና ይፋ ሆነ። በዕለቱም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ባሰሙት ንግግር “ማዘር ተሬዛ የመጨረሻ ደሃ በሆኑት ሰዎች መካከል በመገኘት እነርሱን በማፍቀር፣ እገዛዋንም ለማቅረብ ታጥቃ መነሳቷ በግል ዘወትር ይሰማኝ ነበር፣ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አመጾችና ጦርነቶች ለድሆች የምታቀርበውን አገልግሎት ሊያደናቅፋት አልቻሉም፣ የመረጠችው የሕይወት አቅጣጫዋ ከሁሉ አንሳ መገኘትን ብቻ ሳይሆን የድሆች አገልጋይ ሆና መገኘትንም ጭምር ነበር፣ ለእርሷ ትልቅ መሆን ማለት ሌሎችን ለመርዳት ስትነሳ የምትችለውን ሁሉ በምንም ሳትለካውና ሳትቆጥረ አሳልፋ መስጠት ነበር፣ ሕይወቷም ቆራጥነት የታከለበት የወንጌል ምስክርነት ነበር።” ማለታቸውው ይታወሳል።

የትንሿ ማዘር ተሬዛ ውርስ የነበረው ክርስቲያናዊ ፍቅርና መግለጽ ነበር፣

የማዘር ተሬዛ ሕይወትና አገልግሎቷ ባጠቃላይ ከፍቅር የሚገኘውን ደስታ መመስከር፣ ትንሽም ቢሆን ለሌሎች ጥቅም እንዲሆን  በማለት በፍቅር የሚታደርገው ሥራ ነው። እስከ ዛሬም ቢሆን የእርሷ የፍቅር ሥራ፣ በዓለም ዙሪያ ተሰማርተው በሚገኙት የፍቅር ሥራ እህቶች ወይም ልጆች አማካይነት ሳያቋርጥ በመከናወን ላይ ይገኛል።

04 September 2018, 17:38