ፈልግ

2018.09.03 suor carla venditti 2018.09.03 suor carla venditti 

ስደተኛ ወጣት ልጃ ገረዶችን ከሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ማውጣት ይቻላል።

ጸሎት የአንድን ሰው ሕይወት ሙሉ በሙሉ ሊለውጥ መቻሉን ነው ብለዋል። ብዙ ችግር ሊያጋጥም ይችላል፤ ቢሆንም ፍቅር ከሁሉ በላይ ስለሆነ እነዚህን ችግሮች ለማሸነፍ የሚያስችል ሃይል ከጸሎት እናገኛለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከሚኖሩበት አገር ተሰድደው በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ላይ የገቡትን ወጣት ሴቶች ለመታደግ የሚያግዝ ጥናታዊ ጽሑፍ ተዘጋጅቶ መቅረቡ ተገለጸ። ይህን ጽሕፍ ያቀረቡት፣ እህት ካርላ ቨንዲቲ በኢጣሊያ ውስጥ በአኩዊላ አውራጃ የቅዱስ ልበ ኢየሱስ ደናግል ማሕበር አባል መሆናቸው ታውቋል።

የአቨዛኖ ቅዱስ ልበ ኢየሱስ ደናግል ማሕበር አባል የሆኑት እህት ካርላ ቨንዲቲ ያሳተሙት መጽሐፍ በዋናነት የተመለከትው ርዕስ ከአገራቸው ተሰድደው በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ውስጥ በመግባት ወደ ኢጣሊያ መድረስ የቻሉ ወጣት ልጃገረዶች በደረሱበት አገር የሚያጋጥሟቸውን የተለያዩ ችግሮች ለመቋቋም የሚረዳ ዘዴ ጠቋሚ መጽሐፍ እንደሆነ ታውቋል። በዚህም መሠረት ወጣት ልጃገረዶች ሥራ በማጣት ምክንያት የሚያጋጥሟቸውን የኑሮ ችግሮችን ለመቋቋም በሚያደርጉት ጥረት መካከል ወዳልተፈለገ አደገኛና ሕገወጥ ተግባር እንዳይሰማሩ የመፍትሄ መንገዶችን የሚጠቁምና የሚመክር እንደሆነ ታውቋል። እህት ካርላ መጽሐፋቸውን ለንባብ ባበቁበት ወቅት ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት በርካታ ወጣት ልጃገረዶች ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ስጦታ ካለመረዳት የተነሳ ተሳስተው ችግር ላይ ይወድቃሉ ብለዋል።

መጽሐፉ የጾታ ጥቃት ለደረሰባቸው ወጣት ሴቶች ጠቃሚ ነው፤

እህት ካርላ እንደገለጹት እኛ ገዳማዊያን ሕይወታችንን አሳልፈን የሰጠነው ከእግዚአብሔር በተቀበልነው ስጦታ አማካይነት እንደየ አቅማችን ሌሎችን ለማገልገል በመሆኑ፣ ይህን መጽሐፍ ለመጻፍ ስነሳ ለሌሎች ምን ጠቃሚ ነገር ማድረግ እችላለሁ? በተለይም በማሕበረሰቡ መካከል በችግር ላይ ለወደቁት ስደተኛ ወጣት ልጃገረዶች ምን ልረዳቸው እችላለሁ? ብዬ በመነሳት ይህን መጽሐፍ ለማዘጋጀት በቃሁ ብለዋል።

የእግዚአብሔርን ቃል ወደየ ጎዳናዎች መውሰድ፤

የማሕበራችን መስራች የሆኑን የእናት ክለሊያ መርሎኒ ስም የድርጅታችን መጠሪያ እንዲሆን በማድረግ ስደተኛ ወጣት ልጃገረዶችን የመርዳት ተልዕኮን የጀመርነው በ2007 ዓ. ም. ነበር። በመጀመሪያ ለእነዚህ ስደተኛ ወጣት ልጃገረዶች በወንጌል የታገዙ መንፈሳዊ ጽሑፎችን እናነብላቸው ነበር። መልዕክቱን በሚነበብላቸው ጊዜ ብዙዎቹ እያለቀሱ ልባቸውን የበለጠ ይከፍቱ እንደነበርና ለቅሶአቸውም የመረረ እንደነበር የገለጹት እህት ካርላ ከአንድ ዓመት የአገልግሎት ጊዜ በኋላ ተረጂ ወጣት ሴቶች በቋሚነት የሚኖሩበትን መኖሪያ ቤት ለመክፈት መቻላቸውን ገልጸዋል። ባሁኑ ጊዜ በማዕከሉ ውስጥ እርሳቸውንና ሌላ ረዳት ወጣት ልጃገረድን ጨምሮ ሰባት ሴቶች፣ ሁሉም ቋሚ ሥራ ያላቸውና በሚያገኙት ወርሃዊ ደሞዝ የቤት ኪራይ ከፍለው የመኖር አቅም እንዳላቸው ገልጸዋል።

መዳን የሚገኘው ኢየሱስን ክርስቶስን ወደ ልባችን ስንቀበል ነው፤

እህት ካርላ እንደገለጹት የብዙ ወጣት ልጃገረዶች ሕይወት ከሐዘን ወደ ደስታ፣ ከባርነት ወደ ነጻነት ሲቀየር መመልከታቸውን ተናግረው ይህን ማየት እጅግ ደስ እንዳሰኛቸው አስረድተዋል። እህት ካርላ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ወጣቶቹ እምነት ይኑራቸው አይኑራቸው ጠይቀን አናውቅም፤ ነገርግን ሕይወታችንን በምን መልኩ እንደምንኖር በቅርብ ሆነው ስለሚመለከቱ በተለይም ጸሎት የኑሮአችን ቀዳሚ ተግባር እንደሆነ በየቀኑ ይመለከቱ ነበር ብለዋል። በዚህም የተነሳ ከመካከላቸው ምስጢረ ጥምቀትን ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ እንዳሉ ተናግረው ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ልባችን ውስጥ ስናስገባ መዳን እንችላለን ብለዋል።

የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ውበት፤

እህት ካርላ ቨንዲቲ በመጨረሻም፣ ገዳማዊ በመሆኔ ከእነዚህ ወጣቶች ሴቶች የምለይበት መንገድ አለ፤ ነገር ግን በጀመርኩት የአገልግሎት መንገድ የበለጠ ለመረዳት የቻልኩት ነገር ቢኖር፣ ጸሎት የአንድን ሰው ሕይወት ሙሉ በሙሉ ሊለውጥ መቻሉን ነው ብለዋል። ብዙ ችግር ሊያጋጥም ይችላል፤ ቢሆንም ፍቅር ከሁሉ በላይ ስለሆነ እነዚህን ችግሮች ለማሸነፍ የሚያስችል ሃይል ከጸሎት እናገኛለን ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ “ቤቶቻችሁን ለተቸገሩትና ማደሪያ ላጡት ሰዎች ክፍት አድርጉ ብለው ባቀረቡት መልዕክታቸው፣ እነሆ ዛሬ የመልካም ሥራ ውጤት በማየት ላይ እንገኛለን ብለዋል።                    

05 September 2018, 09:44