ፈልግ

የዲጂታል ዘመን ጋዜጠኝነት፣ እውነትን፣ ሞያዊ ብቃትንና ሰብዓዊ ክብርን ያማከለ መሆን አለበት ተባለ።

በስነ ምግባር የታነጸ የጋዜጠኝነትን አገልግሎት ለማበርከት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የገለጿቸው ሦስት መሠረታዊ መንገዶች እነርሱም፣ የሞያው ተቀዳሚ ተግባር የሆነው እውነት፣ ሞያዊ ብቃትና ሰብዓዊ ክብር ሊኖር ይገባል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም በሚገኘው ሳንታ ክሮቼ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የተከፈተው የካቶሊካዊ ጋዜጠኞችና ሌሎችም ጭምር ያካተተ ስብሰባ የዘመናችን ሰው ራዕይ በሚለው ርዕሱ፣ የዲጂታል ዘመን ጋዜጠኝነት፣ እውነትን፣ ሞያዊ ብቃትንና ሰብዓዊ ክብርን ያማከለ መሆን አለበት ብሏል።       

የስብሰባው ተሳታፊዎች፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች፣ የሰው ልጅ በተለያዩ ማሕበራዊ ዘርፎች ሃሳቡን የሚገልጽበትን መድረክ በማመቻቸት ላይ እንዳሉ ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎ የሰው ልጅ ክርስቲያናዊ፣ ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ዕይታ ምን መምሰል ያስፈልጋል በማለት ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

በኢጣሊያ ካቶሊካዊና ካቶሊካዊ ያልሆኑ ጋዜጠኞች ህብረት ትናንት በሮም በሚገኘው ሳንታ ክሮቼ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ካካሄዱት ስብሰባ በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተገኙት ምዕመናን ባቀረቡት ሳምንታዊ ትምህርተ ክርስቶስ እንዲሁም ባሳረጉት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ ተገኝተዋል። ቅዱስነታቸው ለእነዚህ ጋዜጠኞች ሰላምታ አቅርበውላቸዋል። የጋዜጠኞችን ስብሰባ ከተካፈሉት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ፈራሮ፣ በኢጣሊያ ቴሌቪዢን የቫሌ ዳ ኦስታ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ተወካይ እንዳስታወቁት በስነ ምግባር የታነጸ የጋዜጠኝነት አገልግሎት ለማበርከት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የገለጿቸውን ሦስት መሠረታዊ መንገዶች እነርሱም፣ የሞያው ተቀዳሚ ተግባር የሆነው እውነትን መውደድ፣ ሞያዊ ብቃትና ሰብዓዊ ክብር ሊኖር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ጥልቀት ያለው መረጃን ማቅረብ ያስፈልጋል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሯቸው ሦስቱ መሠረታዊ መንገዶች በስነ ምግባር ለታነጸ የጋዜጠኝነት ሞያ ለምንገኝበት የዲጂታል ዘመን ጋዜጠኝነት እጅግ አስፈላጊ እንደሆኑ አቶ አሌሳንሮ አስረድተው በተጨማሪም በዛሬው ስብሰባቸው ሰፋ ያለ ውይይት ቢደረግባቸውም ወደ ሥራ በሚሰማሩበት ሁሉ ማስተዋል በታከለበት አኳኋን በተግባር መተርጎም እንዳለባቸው አሳስበዋል። አቶ አሌሳንድሮ በማከልም ለአንድ ሕብረተሰብ መረጃ በሚቀርብበት ጊዜ ጥልቀት ያለውና በእውነት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

የዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀምን ማወቅ፣

በኢጣሊያ የማርኬ ክፍለ ሃገር ብሔራዊ ቴሌቪዢን ተወካይ የሆኑት አቶ ቪንቼንሶ ቫራጎና በበኩላቸው፣ አንድ መረጃ ሊኖረው የሚገባ እውነትነት ምንም አያከራክርም ብለው ከዚህ በተጨማሪ ዘመኑ ያፈራቸው የመገናኛ መሣሪያዎች፣ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የአጠቃቀም ስልትና ደንብ እንዳለው ገልጸው ይህ በትክክል በተግባር ካልተቀየረ በመረጃ ልውውጥ እክሎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።

አመታዊ ስብሰባ ሊሆን ይገባል።

የካቶሊካዊ ጋዜጠኞች ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2005 ዓ. ም. በኢጣሊያ ውስጥ ግሮታማረ በተባለ አካባቢ፣ በኢጣሊያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ተነሳሽነት የተጀመረ እንደሆነ የማህበሩ መስራች አቶ ሲሞነ ኢንቺኮ ገልጸዋል። ዘንድሮ በሮም በሚገኘው ሳንታ ክሮቼ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደው የካቶሊካዊ ጋዜጠኞች ስብሰባ አምስተኛ ዙር መሆኑንም አክለው ገልጸዋል። ይህን ዓመታዊ ካቶሊካዊና ካቶሊካዊ ያልሆኑ ጋዜጠኞች ስብሰባን ከአምስት ዓመት በፊት እንዲጀምሩ ያነሳሳቸው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኩል በቀረበው ማሳሰቢያ እንደነበር አቶ ሲሞነ ኢንቺሶ አስታውቀዋል። በማከልም እንደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሃሳብና ምኞት መሠረት በካቶሊካዊው ዓለም የሚገኙትን የማህበራዊ መገናኛ ተቋማትን የበለጠ ለማሳደግ በማለት ካቶሊካዊ ጋዜጠኞች ተደራጅተው የጀመሩት ማህበር እንደሆነ አስረድተዋል።

በየዓመቱ አዳዲስ ውሳኔዎችን እናስተላልፋለን ያሉት የማህበሩ መስራች አቶ ሲሞነ ኢንቺኮ እንደገለጹት የዘንድሮ ስብሰባቸውን በሮም ለማድረግ ያነሳሳቸውን አብይ ምክንያት ሲገልጹ በቅድሚያ በጋዜጣዊ ሞያቸው ቤተክርስቲያንን ለማገልገል ድጋፍና ሃይል ለሆናቸው እግዚአብሔር ምስጋናቸውን ለማቅረብ እንደሆነ አስረድተው በመቀጠልም ይህን አገልግሎት ለቤተክርስቲያን እንድናበረክት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አደራ ማለታቸውን አስታውሰው ይህን አገልግሎታቸውን ፍሬያማ ለማድረግና ትክክለኛውን የጋዜጠኝነት ሞያን የተከተለ እንዲሆን ለማድረግ ግልጽነትና እውነትን ከሚከተሉ የመረጃ ምንጮች ጋር በመተባበር ለሕዝቡ ፍትሃዊ ዜናን ወይም መረጃን ለመቅረብ እንደሆነ ገልጸዋል።   

13 September 2018, 18:05