ፈልግ

2018.08.08 Berhaneyesus Demerew Souraphiel, C.M./ Arci Vescovo di Addis Ababa-Etiopia 2018.08.08 Berhaneyesus Demerew Souraphiel, C.M./ Arci Vescovo di Addis Ababa-Etiopia 

ብጹዕ ካዲናል ብርሃነየሱስ የዘመን መለወጫን አስመልክተው የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ።

እግዚአብሔር አባታችን ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ፍጥረቶች በመፍጠር በዘመን ውስጥ ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲሰጡ ወቅቶችን እንዲፈራፈቁ በማድረግ ለ2011 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ያደረሰን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ የ2011 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን በማስመልከት ለመላው ምዕመናን ያስተላለፉት መልዕክት፤

“በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

“ቀኑንና ለሊቱን የፈጠርህ፣ ፀሐይንና ጨረቃን በየቦታቸው ያፀናህ አንተ ነህ፣ ለምድር ዳርቻን ወሰንህ፣ ክረምትና በጋ እንዲፈራረቁ አደረግህ ፡፡” (መዝ. 74፡ 16-17)

  ብፁዐን ጳጳሳት

ክቡራን ካህናትና፤ ገዳማውያን/ዊያት

ክቡራትና ክቡራን ምዕመናን

መላው ሕዝበ እግዚአብሔር

በጎ ፍቃድ ላላቸው ሰዎች በሙሉ

ከሁሉ አስቀድሜ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንና በራሴ ስም የዓለም ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር አባታችን ሁላችሁንም በሰላምና በጤና ጠብቆ እንኳን ለ2011 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ እያልኩ እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አሸጋገረን በማለት መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ ፡፡

እግዚአብሔር አባታችን ዓለምንና በውስጧ ያሉትን ፍጥረቶች በመፍጠር በዘመን ውስጥ ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲሰጡ ወቅቶችን እንዲፈራፈቁ በማድረግ ለ2011 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ያደረሰን እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡

እኛም ከዚሁ በመነሳት አሮጌ ዓመት አልፎ አዲስ ዓመት ሲመጣ ሁላችንም አዲሱን ዓመት በደስታ ተቀብለን ዘመኑ የደስታና የፍሰሐ እንዲሆንልን በመመኘት እንኳን አደረሳችሁ እያልን መልካም ምኞታችንን እንለዋወጣለን፡፡ በዚህም ለመላው ህዝብ ሰላምና ጤና፣ ለአገራችን ሰላም፣ በምድር ላይ የተዘራው ዘር በቂ እህል እንዲያፈራልን እየተመኘን በአዲሱ ዓመት ምድር በአበቦች የምታጌጥበት፣ ሜዳዎች በሣር የሚሸፈኑበትና እንሰሳትም ምግባቸውን የሚያገኙበት፣ በአጠቃላይ የእግዚአብሔርን በረከት የምንቀበልበትና የምናይበት፣ የዝናቡ ወራት አልፎ ፀሐይ የሚወጣበት ጊዜ ስለሆነ በእነዚህ ሁሉ ድንቅ የእግዚአብሔር ሥራዎች ምስጋና በማቅረብ በደስታ የምናከብረው በዓል ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላካችንን እኛ የእሱ ፍጡራን በብዙ መንገድ ልናውቀው እንችላለን፤ ከሁሉም በላይ የምናውቀው በሥነ ፍጥረቱ ነው፡፡ በዚሁም በቸርነቱና ወሰን በሌለው ጥበብ በእግዚአብሔር መኀተም ታትሞ ህያውነትን ይዞ የሚጓዝ ነው፡፡ ስለዚህም በእምነትና በአድናቆት ፀሐይን፣ ዝናብን፣ አበቦችንና ሣሮችን ማየት የእግዚአብሔር ሕያውነት ለመረዳት ያግዘናል፡፡ የእርሱ ቸርነት ሁሌም አያልቅምና፤  ለዚህም ዳዊት “የእግዚአብሔር ቸርነት ጣፋጭ መሆኑን ቀምሳችሁ እወቁ ይለናል::” (መዝ. 34፡8)

እንደሚታወቀው አዲስ ዓመት ሲመጣ ሰዎች በእግዚአብሔር አምላካቸው በመታመን የተላያዩ ዕቅዶችንና ተስፋዎችን በማቀድና በመያዝ ይጀምሩታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ብዙ ገንቢ የሆኑ ዕቅዶችን በመያዝ ከአካባቢያቸው ማኀበረሰብና ከተለያዩ ክፍሎች ጋር ተባብረው መልካም የሆነ ተግባር በመፈጸም ተገቢ ከመሆኑም ሊሠሩ የታቀዱትን ተግባሮች በጥሩ ሥነ ምግባር ተግባራዊ ማድረግና መሥራት ይገባናል፡፡

”የምሕረትህን ዓመት አክሊል ትባርካለህ፣ መድረ በዳዎችም ጠልን ይጠግባሉ፡፡ የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፣ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ፡፡" (መዝ.64፡ 11-12)

በዚህ አዲስ ዓመት በአገራችን ላይ ምህረትና ይቅርታን ይዘን የአገራችን ህዝቦች በመፈቃቀርና በመዋደድ ብሎም በመከባበር ስለ ሰላምና አንድነት የበለጠ የሚሠሩበትና በእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል የተፈጠረውን የሚወዱበት የተፈናቀሉትን ወገኖችን መልሰው በመቀበልና በማቋቋም አብረው የሚኖሩበትና የሚሠሩበት እንዲሆን ቤተክርስቲያናችን አጥብቃ ትመኛለች፡፡

የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሕይወት ተሣታፊ የሆነው ሰው ሕይወቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ሃብት መሆኑን ተገንዝቦ እርሱ የሰጠውን ነፃነት ተጠቅሞ በአዕምሮውና በፈቃዱ መልካም ነገሮችን ሊሠራና ሊፈጽም ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ህሊናችንን በኃላፊነት መንፈስ ልንመራው ያስፈልጋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደምናየው ከጥንት ጀምሮ በአገራችን የተለያዩ ክፍሎች ተዋዶና ተፋቅሮ አብሮ ይኖር የነበረው ህብረተሰብ ዛሬ ብሔርን በማጣቀስ ማባረርና ማሳደድ ብዙ ጊዜና ገንዘብ የወጣበትን ንብረት ማፈራፈስ እግዚአብሔር የሚመለክበትን ቅዱስ ስፍራ ማቃጠልና ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት ማጥፋት ሰውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ተግባር ነው፡፡ ስለሆነም የአንድነት  መሠረታችንን ሳንረሣ በህግና በሥነ-ሥርዓት እየተመራን እርስ በርሳችን ተዋደንና ተከባብረን እንድንኖር አስገነዝባለሁ፡፡

ወጣቶቻችንም አሁን ያላችሁን የኢትዮጵያዊነት ፍቅርና መነቃቃት እግዚአብሔርን በመፍራትና ሰውን በማክበር መንፈስ ለአገራችሁ ዕድገትና ግንባታ ህዝባችሁን በመውደድና በማፍቀር ለጥሩ ሥራ እንድታውሉት ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ ማንኛውም የአገሪቱ ዜጋ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች የመኖርና የመሥራት መብታቸውን አክብሮ በማስከበር በአንድነት መንፈስ በመሥራት ሰላምንና ፍቅርን አጥብቃችሁ በመያዝ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካም ተግባር ብቻ በመፈጸም ለአገር አንድነት ተባብራችሁ በመቆም ከልዩነት ይልቅ አንድነትን በማጠንከር፣ ጥላቻንና ሞትን እንድትጠሉ አደራ ማለት እወዳለሁ፡፤

መንግስትም የሁሉም የአገሪቱ ህዝቦች ኃላፊነት ያለበት መሆኑ የሚታወቀው ህዝቡን በፍቅር የሚያስተባበርና የሚያስተሣሥር ነገር በመሥራት ለአገር ልዕልናና ለዜጎች ሕይወት በፅናት በመቆም ህግና ሥርዓትን በሚገባ ማስከበር ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ሰዎች በአገራቸው የሚዘረፉ፣ የሚሰደዱና፣ የሚገደሉ መሆኑ ቀርቶ ሊሰማም እንደማይገባ አውቆ ለአገሪቱ መረጋጋትና ገጽታም መሥራት እንደሚኖርበት ማስገንዘብ እንፈልጋለን፡፡ እግዚአብሔር ለመሪዎቻችንና ለመንግስታችን የጥበብ ጸጋውን ይስጥልን፡፡

የሁሉም የእምነት ተቋማት ለምዕመናኖቻችውና ለተከታዮቻቸው መሠረታዊ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ተጠቅመው ስለ ሰው ደኅንነት፣ ስለ ሰላም፣ አብሮ ስለመኖር፣ ስለ ፍቅርና ስለ እግዚአብሔር መልካምነት በማስተማር የሰዎችን ኅሊና ማነጽ እንደሚኖርባቸው ከዚህም በላይ ደግሞ መገሰጽና ማስተማር እንደሚገባቸው ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡

በዚህ በዓል ላይ የእኛ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በችግር ላይ ለሚገኙ አቅመደካሞች፤ የጎዳና ተዳዳሪዎች፤ የአልጋ ቁራኛ ለሆኑ ሕሙማን እንዲሁም ለተፈናቀሉና ለተቸገሩ ወገኖች ሁሉ ርኀራኄያችንንና እርዳታችንን  በመለገስ ከእነርሱ ጋር በመሆንም በዓላችንን በደስታ አብረን እንድናከብር አደራ ማለት እወዳለሁ፡፡

በዚህ አዲሰ ዓመት ለተማሪዎች በሙሉ መልዕክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ ምክንያቱም መስከረም ወር ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ ስለሆነ በአዲስ ተስፋና በጽኑ ዓላማ ትምህርት  ቤት ገብታችሁ ትምህርታችሁን  በርትታችሁ  እንድትማሩ ወላጆቻችሁንና መምህራኖቻችሁን እያከበራችሁ የልፋታችሁ፣የስራችሁን መልካም ውጤት እንድታገኙ ለራሳችሁም ሆነ ለቤተሰብ እንዲሁም ለሐገር ኩራትና መልካም ዜጋ መሆን እንድትችሉ አባታዊ መልዕክቴን አስተላልፍላችኃለሁ፡፡

በመጨረሻም ከአገር ውጪ የምትገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ በተለያዩ ሥራዎች ከቤተሰብና ከዘመድ ርቃችሁ የመትገኙ ወገኖቻችን፣ በየቤቱና በየሆስፒታል ለምትገኙ ህሙማን፣ በማረሚያ ቤት ለምትገኙ የህግ ታራሚዎች፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር የምትተጉትን የፖሊስና የፍረድ ቤት አባላትን፣ የአገርን ዳርድንበር ለማስከበር በተለያዩ ግንባር ላይ ያላችሁ የመከላከያ ሠራዊት አባለት፣ በሰደት ላይ ለምትገኙ ወገኖች፣ ለሁላችሁም ቅዱስ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለ2011 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል አደረሳችሁ በማለት ዘመኑ የፍቅር፣የይቅርታ፣የሰላም፣የበረከትና የብልጽግና ይሁንልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያ አገራችንንና ዘመናችንን በሙላት ይባርክልን”።

+ ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት

10 September 2018, 17:35