ፈልግ

ማሪያምን የተመለከቱ ዐራቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አንቀጸ-እምነቶች በአጭሩ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን የተመለከቱ ዐራቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን

አንቀጸ-እምነቶች

አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃይለጊዮርጊስ-ቫቲካን

እንደ አገራችን ሥርዓተ አምልኮና መንፈሳዊ ልማድ በእመቤታችን በኩል እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስለገለጠው ተስፋና በእርስዋም ጸጋ መሞላት ላደረገልን ቸርነት በተለየ ሁኔታ በየዓመቱ ለ16 ቀናት የሚዘለቀወን ጾምና ምህለላ የምናደርግበት የፍልሰታ ዘመን ላይ እንገኛለን። እግዚአብሔር አብ በእርሱ ለኖሩት ሁሉ ሊያደርግላቸው ቃል የገባውን እውነታ እርሱ በፈቀደው መልኩ በእመቤታችን የተገበረበትን ጸጋ እናወድሳለን፤ ለእኛም ይሆንልን ዘንድ “ሰአሊ ለነ ማርያም ኀበ ወልደኪ ኄር መድኃኔ ዓለም” /ማርያም ሆይ! ቸር፣ የሰው ልጆች ሁሉ አዳኝ ወደ ሆነው ልጅሽ ለምኝልን/ በማለት የእናትነት አማላጅነቷን እንማጠናለን (ፍልሰታ ማሪያም፡ Ethiocist.org. Online)።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እመቤታችን ቅድስት ደንግል ማሪያም በደኅንነት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አስትዋጾ በእግዚኣብሔር እንደተሰጣት ታምናለች፣ ታስተምራለችም። በዚሁ ምክንያት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ካላት አክብሮት እና ፍቅር በመነሳት በቤተ ክርስቲያኗ የእመነት ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት ውስጥ ማሪያምን የተመለከተ 4 ዶግማዎች ወይም አንቀጸ-እምነት የማይሻር የማይለወጥ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውስጥ እንዲካተቱ አድርጋላች። እነዚህ ማሪያምን የተመለከቱ ዶግማ ወይም ደግሞ የማይሻር የማይለወት አንቀጸ-እምነት የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው።

1.     ማሪያም የእግዚኣብሔር እናት ናት

ማሪያም ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ጸንሳ በመውለዱዋ የተነሳ እግዛኢብሔር የሆነው የኢየሱስ እናት በመሆኑዋ የተነሳ “የእግዚኣብሔር እናት ናት” ተብላ ትጠራላች። ይህም ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት (የማይለወጥ የማይሻር የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ) እ.አ.አ. በ431 ዓ.ም በተደረገው የኤፌሶን ጉባሄ ከጸደቀ በኋላ እስከ ዛሬ ቀን ድረስ ቤተ ክርስቲያን ይህንን አስተምህሮ በማስተማርና በመጠበቅ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ያላትን አክብሮት በመግልጽ ላይ ተገኛለች።

2. ማሪያም ለዘለዓለም ድንግል ናት

ማሪያም ኢየሱስን ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ እና እኛ በተወለድንበት መንገድ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ጸንሳ በመውለዱዋ የተነሳ ለዘለዓለም ድንግል ሆና ትኖራለች የሚለውና እ.አ.አ በ649 ዓ.ም. በላቴራን ጉባሄ የጸደቀው ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት ነው።

3. ማሪያም ያለ አዳም ኃጢኣት የተጸነሰች ናት

በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ማሪያም ያለ አዳም ኃጢኣት የተጸነሰች ናት የሚለው ነው። በዚህም በማይለወጥ እና በማይሻር አንቀጸ-እምነት አስተምህሮ ማሪያም ቀደም ሲልም ቢሆን በእግዚኣብሔር የማዳን እቅድ ውስጥ በመኖሩዋ የተነሳ የእርሱ ማለትም የእግዚኣብሔር ልጅ ማደሪያ ትሆን ዘንድ አስቀድሞ ስለመረጣት እኛ ሁላችን ከአዳም የወረስነውን እና በጥምቀታችን ቀን ከሚደመሰሰው ኃጢኣት ነጻ ሆና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያ እንድትወለደ እግዚኣብሔር በማድረጉ የተነሳ እመቤታችን “ካለአዳም ኃጢያት ተጸንሳ የተወልደች ነች” የሚለው ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት እ.አ.አ በ1854 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮ 9ኛ ጸድቆ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት የማይሻር የማይለወጥ አስተምህሮ እንዲሆን ተደርጉዋል።

4. ማሪያም በሥጋ እና በነብስ ወደ ሰማይ ፈልሳለች

በአራተኛ እና በመጨረሻ ደረጃ የምናገኘው ደግሞ ከ6ኛ ክፍለ ዘመን አንስቶ እስከ ዛሬው ቀን ደረስ በምስራቃዊያን የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናትም ጭምር እየተከበረ የሚገኘው “ማሪያም በሥጋ እና በነፍስ ወደ ሰማይ ወጣች” የሚለውና በአሁኑ ጊዜ እኛ በጾም እና በጸሎት ለ16 ቀናት ያህል እየዘከርነው የምንገኘው የፍልሰታ ጾም የሚያስታውሰን ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት ምንም እንኳን ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እየተከበረ፣ እየተዘከረ የሚገኝ ክብረ በዓል ቢሆንም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ዶግማ ወይም አንቀጸ-እምነት የማይለወጥ የማይሻር አስተምህሮ ተደርጎ በሕግ ውስጥ የሰፈረው ግን እ.አ.አ በ1950 ዓ.ም. በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ ከጸደቀ በኋላ ነው። 

ኢየሱስ ወደ እዚህ ምድር መቶ ተስቃይቶ ተሰቅሎ መሞቱን እና በሦስተኛው ቀን ከሙታን መነሳቱን በሚዘከርበት የእርገት ቀን መካከል እና ማሪያም ወደ ሰማይ የፈለሰችበት ቀን እና ሁኔታ  ግን የተለያዩ እንደ ሆነ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጠንቅቀን እንድንረዳ አደራ ትለናለች። የእግዚኣብሔር ልጅ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣  ሞትን ድል ነስቶ ወደ ሰማይ የወጣው በመለኮታዊ ኃይሉ አማካይነት ሲሆን ነገር ግን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያ ወደ ሰማይ የፈለሰቺው በእግዚኣብሔር መለኮታዊ ኃይል እንደ ሆነ ልብ ሊባል ይገባል።

ምንጭ

 የካቶሊክ ቤት ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ

 የሲታዊያን መነኩሳት ድረ ገጽ (www.etiocist.org)

 

07 August 2018, 11:44