ፈልግ

KENYA-RELIGION-CHRISTMAS KENYA-RELIGION-CHRISTMAS 

በኬንያ ለማሳይ ጎሳ የሚያገለግል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሬዲዮ ጣቢያ ተከፈተ።

በኬንያ የንጎንግ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከት ነዋሪ ለሆነው ለማሳይ ጎሳ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሬዲዮ ጣቢያ መከፈቱን ፊደስ የዜና ምንጭ ገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኬንያ የንጎንግ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሀገረ ስብከት ነዋሪ ለሆነው ለማሳይ ጎሳ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሬዲዮ ጣቢያ መከፈቱን ፊደስ የዜና ምንጭ ገልጿል። ሬዲዮ ጣቢያው ለሀገረ ስብከቱ ነዋሪዎች የሚያቀርበውን አገልግሎት በሁለት ቋንቋዎች ማለትም በኪስዋሂሊ እና በማሳይ ቋንቋዎች እንደሚያሰራጭ ታውቋል።

በኬንያ ንጎንግ ሀገረ ስብከት የተከፈተው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሬዲዮ ጣቢያ “ኦሶቱዋ ራዲዮ ካቶሊክ” የሚል መጠሪያ ስም ያለው ሲሆን ለነዋሪዎቹ የየዕለቱን ዜናንና ማሕበረሰብ ነክ ዝግጅቶችን እንደሚያቀርብ ፊደስ የዜና ተቋም ገልጿል። በንጎንግ ሀገረ ስብከት የተከፈተው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሬዲዮ ጣቢያ፣ የኬንያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ከሁለት ሺህ ስምንት እስከ ሁለት ሺህ አስራ ሁለት ዓ. ም. ድረስ ለመክፈት ካቀዷቸው 20 የሬዲዮ ጣቢያዎች መካከል አንዱ መሆኑ ታውቋል።

የወንጌልን የምስራች ለማዳረስ የሚረዳ ነው፣

በዚህ አዲስ ካቶሊካዊ ሬዲዮ ጣቢያ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት፣ የኬንያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት የሆኑት ብጹዕ አቡነ ጆን ኦባላ ኦዋ፣ በሀገረ ስብከቱ አዲስ ሬዲዮ ጣቢያ የመክፈቱን አስፈላጊነት ሲያስረዱ፣ የሀገረ ስብከቱ ነዋሪዎች መንፈሳዊና ማሕበራዊ ትምህርቶችን የሚቀስሙበት፣ ግብረ ገብን በመማር ሙስናን፣ ዘረኝነትንና ስግብግብነትን የሚዋጉበትን መንገድ የሚቀስሙበት፣ በተጨማሪም ልዩ ልዩ ጎሳዎች በመካከላቸው በእውነተኛ ፍቅር ላይ የተመሠረተ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት ግንኙነት እንዲያድግ ለማገዝ መሆኑን አስረድተዋል።  የኬንያ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት ብጹዕ አቡነ ጆን ኦባላ ኦዋ በማከልም የክርስቲያን ማሕበረሰብና እርዳታ ለጋሽ አገሮች፣ አዲስ የተከፈተው ሬዲዮ ጣቢያ በዘላቂነት አገልግሎቱ በርካታ ቁጥር ያለውን አድማጭ መድረስ እንዲችል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ለማሳይ ብሔረሰብ ትልቅ ጥቅም ነው፣

በሀገረ ስብከቱ የመንግሥት ተወካይ የሆኑት ክቡር አቶ ሳሙኤል ቱናይ፣ የክልሉ ነዋሪዎች የሆኑ የማሳይ ብሔረሰብ አባላት ከተከፈተላቸው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ሬዲዮ ጣቢያ ሰፊ አገልግሎት እንደሚያገኙ ገልጸው፣ በተለይም የግል የንግድ ተቋማት ገበያቸውን ለማስተዋወቅ መልካም መንገድ እንደሚሆናቸው አስረድተዋል። የመንግሥት ተወካዩ ሬዲዮ ጣቢያው ስሙ “ኦሶቱዋ ራዲዮ ካቶሊክ” የሚል መጠሪያ እንዳለውና በማሳይ ቋንቋ “ኦሶቱዋ” ማለት ሰላም ማለት እንደሆነ ገልጸው በሌላ ተጨማሪ ትርጉሙ “ኦሶቱዋ” ማለት ኪዳን፣ የብሉይ ወይም የአዲስ ኪዳን የሚል ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል። ቃሉ በሌላ ተጨማሪ ትርጉሙ እናትና ልጅ የሚገናኙበት እንብርት ማለት እንደሆነም አክለው ገልጸዋል።            

28 August 2018, 16:46