ፈልግ

madonna Fatima - Gmg Panama 2019 madonna Fatima - Gmg Panama 2019 

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሐውልት ወደ ፓናማ ይጓዛል።

በፓናማ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ እንዲገኝ የተወሰነበት ምክንያት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ እርሳቸው ላስጀመሩት ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በሚሰጡት አክብሮት የተነሳ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሚቀጥለው ዓመት በፓናማ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ፣ የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሐውልት እንደሚቀርብ ታውቋል። ወደ ፓናማ የሚወሰደው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሐውልት ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ከሚከበርባቸው ቀናት መካከል በሁለቱ ማለትም ቅዳሜና እሁድ ዕለት በይፋ እንደሚታይ ታውቋል።

በሚቀጥለው ዓመት በፓናማ የሚከበረው የመላው ዓለም ወጣቶች በዓል ከጥር 14 እስከ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ. ም. ድረስ እንደሆነ ይታወቃል። እ. አ. አ. ከ2000 ዓመት ወዲህ የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሐውልት አሁን ከሚገኝበት ከፖርቱካል አገር ወደ ሌላ አገር ሲወሰድ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ታውቋል። ብጹዕ አቡነ ሆሴ ዶሚንጎ ኡሎአ መንዴታ፣ ሲር ለተባለ የቤተክርስቲያን ዜና አገልግሎት በሰጡት የቪዲዮ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት በፖርቱጋል አገር፣ በፋጢማ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኝ ይህ የእመቤታችን ማርያም መንፈሳዊ ሐውልት በመጭው ዓመት በፓናማ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ ለወጣቶች እንደሚቀርብ አስታውቀዋል። በፖርቱጋል አገር የሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ማርያም መንፈሳዊ ልዩ ሐውልት፣ እህት ሉቺያ የተባሉ የደናግን ማሕበር አባል ባቀረቡት ሃሳብ ተቀርጾ ሲያበቃ በ1939 ዓ. ም. ደግሞ ዘውድ እንዲደፋ የተደረገ መሆኑ ታውቋል። ይህ የእመቤታችን ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሐውልት እስከ ዛሬ ድረስ ወደ 64 አገሮች የተወሰደ ሲሆን በኋላም ወደነበርበት ወደ ፖርቱጋል ተመልሶ በቋሚነት እንዲቀመጥ መደረጉ ታውቋል። ከብዙ ዓመታት በኋላ በሚቀጥለው ዓመት የመካከለኛው ላቲን አሜርካ አገር በሆነው በፓናማ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ እንዲገኝ የተወሰነበት ምክንያት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ እርሳቸው ላስጀመሩት ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን በሚሰጡት አክብሮት የተነሳ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም በተጨማሪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚሰጡት ጥልቅ አክብሮት በፓናማ ምዕመናን ዘንድም በመኖሩ ነው ተብሏል።

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሐውልት ወደ ፓናማ ከደረሰ በኋላ በሉርድ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በክብር እንደሚቀመጥና ቀጥሎም በፐርዶን ፓርክ በሚገኝ የማድረ ተሬዛ ማሕበር ጸሎት ቤት ውስጥ በክብር እንደሚቀመጥ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ሥፍራም ዓለም አቀፍ የውጣቶች ቀን በሚከበርባቸው ቀናት ውስጥ የተለያዩ ዝግጅቶች የሚቀርቡበትና የበዓሉ መክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚያሳርጉበት ቦታ እንደሆነ ታውቋል። ቅዳሜ ጥር 18 ቀን 2011 ዓ. ም. በሚከናወነው የዋዜማ ስነ ስርዓትና እሁድ ጥር 19 ቀን በሚቀርበው የበዓሉ መዝጊያ መሰዋዕተ ቅዳሴ ስነ ስርዓት ላይ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ሐውልት በይፋ እንደሚወጣ ከበዓሉ መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።           

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፓናማው የዓለም ወጣቶች በዓል ላይ እንደሚገኙ በኢንተርኔት ድረ ገጽ በተዘጋጀላቸው የመመዝገቢያ ቅጽ ላይ አስቀድመው ስማቸውን በማስፈር ያሳወቁ መሆናቸው ይታወቃል።

በየሦስት ዓመት የሚከበረው የመላው ዓለም ወጣቶች በዓል፣ ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትና ከዓለም ዙሪያ ከሚሰበሰቡ ወጣቶች ጋር የሚገናኙበትና የሚተዋወቁበት ተናፋቂ በዓል እንደሆነ ይታወቃል። ከመላው ዓለም የሚመጡ ወጣቶች የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ኩላዊነትን በግልጽ የሚያዩበትና እምነታቸውን የሚመሰክሩበት ምቹ አጋጣሚ እንደሆነም ይታወቃል።

29 August 2018, 16:21