ፈልግ

Giappone – Bomba atomica – Hiroshima - Nagasaki Giappone – Bomba atomica – Hiroshima - Nagasaki 

ከ73 ዓመታት በፊት ሁለቱ የጃፓን ከተሞች በአቶሚክ ቦምብ መውደማቸው መታወሱ ተገለጸ።

ከ73 ዓመታት በፊት ሁለቱ የጃፓን ከተሞች ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ በአቶሚክ ቦምብ መውደማቸውን እንዲሁም የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ በአንድ ወቅት አስታውሰው ነበር። ዛሬም ቢሆን ይህ አሳዛኝ ክስተት በሌሎች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ይዘከራል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከ73 ዓመታት በፊት ሁለቱ የጃፓን ከተሞች ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ በአቶሚክ ቦምብ መውደማቸውን እንዲሁም የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ በአንድ ወቅት አስታውሰው ነበር። ዛሬም ቢሆን ይህ አሳዛኝ ክስተት በሌሎች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ይዘከራል።

“ሁለቱ የጃፓን ከተሞች፣ ሂሮሺማ እና ናጋሳኪ በኒውክሊያር መሣሪያ ጥቃት የወደሙ የመጀመሪያ ከተሞች ናቸው። ጦርነት ያስከተለው ጉዳት ስለሆነ በዚያ ጦርነት የተሳተፉት ወይም በጊዜው የሆነውን የተመለከቱት ዛሬም በሕይወት አሉና የጦርነትን አስከፊነት ያስታውሱታል።” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ በ1973 ዓ. ም. ጃፓንን በመጎብኘት በሂሮሺማ “የሰላም መታሰቢያ” በተባለ ቦታ ላይ ተገኝተው፣ በሁለቱ ከተሞች ጦርነት ያስከተለውን አሳዛኝ ጥፋት አስመልክተው ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል። በሁለቱ የጃፓን ከተሞች ማለትም በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ  በሐምሌ 30 እና ነሐሴ 3 ቀን 1937 ዓ. ም. በተፈጸመው የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደተገደሉ እና ይህ ጥቃት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ እንደሆነ ይታወሳል።

ለሰላም የሚደረግ ጥረት መረሳት የለበትም፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ በወቅቱ በሂሮሺማ ባሰሙት ንግግራቸው እንደገለጹት የጦርነትን አስከፊነት ማስታወስ መልካም የሚሆነው በቀጣይ ዓመታት ጦርነት እንዳይደገም ለሰላም በርትተን እንድንሠራ እና በሰው ልጅ ዘንድ እምነታችንን ለማደስ፣ መልካምን ለማድረግ ያለውን ችሎታ እንዲያሳይ፣ ነጻነቱን በመጠቀም ትክክለኛ እና ፍትሐዊ የሆነውን መንገድ እንዲመርጥ ስለሚያደርግ ነው ብለዋል። የጦርነት አስከፊነት መታወስ ያለበት በሰዎች ሁሉ ዘንድ በተለይም በምድር ላይ ያሉትን ነፍሳት በሚወዱ እና በሚንከባከቡ ሰዎች ዘንድ፣ መንግሥትም ሰላምን ለማንገሥ አስፈላጊውን ትኩረት እንዲሰጥ በማለት በሚያሰሙት ድምጽ አማካይነት ስለ ሆነ ነው ብለዋል። በዓለማችን ለሚፈጸሙት ክፋቶች በሙሉ የመጨረሻ ግባቸው ሰላም መሆን አለበት። ሰላም እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ ብዙ ስቃይን ማለፍ አለበት። ከመጣ በኋላም ጥበቃ እና እንክብካቤ ያስፈልገዋል ብለዋል።

ጦርነት የሁል ጊዜ ስጋት ነው፤

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ፣ በ1973 ዓ. ም. ጃፓንን ሂሮሺማ “የሰላም መታሰቢያ” ሥፍራ ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግራቸው፣ የጦርነትን አስከፊነት ማስታወስ መልካም የሚሆነው ጦርነት የበለጠ ጥፋትን ስለሚያስከትል ብቻ ሳይሆን የጦር መሣሪያ ማምረት በተለይም አቶሚክ የጦር መሣሪያዎችን የሚያመርቱ አገሮች አሁንም ስላሉ፣ ከማምረትም አልፎ ተርፎ ሌሎች አገሮችንም የዚህ ጦር መሣሪያ ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ ብሎም ለጦርነት እንዲዘጋጁ በማደፋፈር፣ ባልታወቀ ሥፍራ እና ባልታወቀ ጊዜ ጥፋትን ሊያስከትል ስለሚችል ነው ብለዋል።

ስለ ሕይወት የሚጨነቁ ሰዎች እንዲያስቡበት፤

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ የተደረጉትን ሁለቱ ጦርነቶች ያስከተሉትን ጥፋት በማስታወስ፣ ሚያዚያ 24 ቀን 2002 ዓ. ም.  ወደ ሰሜን ኢጣሊያ ከተማ ወደ ሆነችው ቶሪኖ ባደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ባሰሙት ንግግር እንደገለጹት፣  በጊዜያችን ያንዣበበው የጦርነት ስጋት በምድራችን ላይ ለነፍሳት የሚጨነቁ ሰዎችንና በተለይም እኛ ክርስቲያኖች የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ስላለብን በሚገባ እንድናስብበት ይጋብዘናል ብለዋል።

የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አቤቱታዎች፤

እንደ ቀደምት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሁሉ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም የተሰማቸውን ስጋት በመግለጽ የኒውክሊየር የጦር መሣሪያዎች ትጥቅ እንዲፈታ በማለት ተደጋጋሚ አቤቱታዎችን አሰምተዋል። እሁድ ነሐሴ 3 ቀን 2007 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከምዕመናን ጋር ካሳረጉት የብስራተ ገብርኤል ጸሎት በኋላ ባሰሙት ንግግር እንደገለጹት፣ ከ70 ዓመታት በፊት በሂሮሺማ እና በናጋሳኪ አስከፊ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃቶች ተካሂደዋል። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ይህ አሳዛኝ ክስተት አሁንም ድረስ ስጋትንና  ተቃውሞን እያስነሳ ይገኛል።  የሂሮሺማ እና የናጋሳኪ አስከፊ የአቶሚክ ቦምብ ጥቃቶች፣ የሰው ልጅ ሳይንሳዊ እድገትን ወደ ተሳሳት አቅጣጫ በማዞር ጥፋትን ማስከተሉ፣ የጦርነት አስከፊነት እና የኒውክሌር የጦር መሣሪያዎች ምን ያህል የሰውን ሕይወት በጅምላ የሚያጠፋ መሆኑ የታየበት ትልቅ የማስጠንቀቂያ ምልክት ነበር ብለዋል።  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ህዳር 23 ቀን 2010 ዓ. ም.  ወደ ባንግላዲሽ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት ባሰሙት ንግግር፣ የኒውክሊየር የጦር መሣሪያዎች ባለቤት መሆን የሰው ልጅን በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ጥፋት ስለሚያመራ ነው በማለት የተሰማቸውን ስጋት ገልጸዋል።

ከስቃይ ባሻገር የሰላም ተስፋም አለ፤

የኒውክሊየር የጦር መሣሪያዎች ካስከተሉት ከበርካታ የሕይወት መጥፋት በኋላ በዓለማችን የሰላም ተስፋም አለ። በ1973 ዓ. ም. ወደ ጃፓን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ፣ ጃፓን የጦርነት ጥቃት የተፈጸመባትን ሂሮሺማን የሰላም መታሰቢያ ቦታ ማድረጓን በማስታወስ ባሰሙት ንግግር፣ ጦርነት ያወደማትን የሂሮሺማ ከተማ የሰላም መታሰቢያ እንድትሆን የጃፓን ባለስልጣናት የወሰዱትን ውሳኔ ሳላደንቅ ማለፍ የለብኝም ብለው፣ በዚህም ምክንያት መላው የጃፓን ሕዝብ ለሰላም ያለውን ተስፋ የገለጸበት፣ የሰው ልጅ ጦርነት የማካሄድ ብቃት ካለው ሰላምንም የማንገሥ ብቃት እንዳለው መገንዘባቸውን አስታውሰው፣ በእግዚአብሔር ለሚያምኑት በሙሉ ፍቅር በቃል ብቻ የሚገልጽ ሳይሆን እግዚአብሔር ራሱ ወደሚሰጠን እውነተኛ ሰላም የሚያደርሰን መንገድ ነው ብለዋል።       

 

09 August 2018, 15:54