ፈልግ

EGYPT LIBYA CHRISTIANS EXECUTED AFTERMATH EGYPT LIBYA CHRISTIANS EXECUTED AFTERMATH 

አንድ የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ ተገድለው መገኘታቸው ተሰማ።

ጳጳሱ ግንባራቸው ላይ በጽኑ መቁሰላቸውን ፖሊስ አረጋግጧል። ይሁንና የብጹዕ አቡነ አንባ ኤፒፋኒዮስ አሟሟት በተመለከተ ግልጽ የሆነ ማስረጃ እስካሁን እንዳልተገኘ ሲነገር፣ መንግሥት የአሟሟታቸውን መንስኤ የማጣራት ሥራውን እያከናወነ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በግብጽ የታላቁ ዳይር አቡ ማቃር የቅዱስ ማርቆስ ገዳም አበምኔት የሆኑት ብጹዕ አቡነ አንባ ኤፒፋኒዮስ ከትናንት በስትያ ጠዋት በገዳማቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ታውቋል። ጳጳሱ ግንባራቸው ላይ በጽኑ መቁሰላቸውን ፖሊስ አረጋግጧል። ይሁንና የብጹዕ አቡነ አንባ ኤፒፋኒዮስ አሟሟት በተመለከተ ግልጽ የሆነ ማስረጃ እስካሁን እንዳልተገኘ ሲነገር፣ መንግሥት የአሟሟታቸውን መንስኤ የማጣራት ሥራውን እያከናወነ መሆኑ ታውቋል። የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ ጳጳሱ ሲያገለግሉ በቆዩበት በታላቁ ዳይር አቡ ማቃር ቅዱስ ማርቆስ ገዳም ውስጥ ብጹዓን ጳጳሳት እና ምዕመናን በተገኙበት በትላንትናው ዕለት ጸሎተ ፍትሐት ሥነ ሥርዓት ማከናወኗ ታውቋል።

የ64 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት ብጹዕ አቡነ አንባ ኤፒፋኒዮስ፣ በ1976 ዓ. ም. በዋዲ ናትሩን ግዛት ውስጥ በሚገኘው በቅዱስ ማቃሪዮስ ገዳም በመግባት መንፈሳዊ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፣ በ1994 ዓ. ም. ማዕረገ ክህነትን ተቀብለዋል። ብጹዕ አቡነ ኤፒፋኒዮስ ብዙ የምርምር ሥራዎችን ያካሄዱ ምሁር እንደነበሩ ፊደስ የዜና ማዕከል ገልጿል። ብጹዕ አቡነ ኤፒፋኒዮስ ካቀረቧቸው ሥራዎች መካከል በርካታ የትርጉም ሥራዎቻቸው የሚጠቀሱ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ከግሪክ ቋንቋ ወደ አረበኛ ቋንቋ ተርጉመው እንዳቀረቡ ታውቋል። ብጹዕ አቡነ ኤፒፋኒዮስ በ2004 ዓ. ም. በሮም በተካሄደው 10ኛው ዓለም አቀፍ የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ስነ ጥበብ ጉባኤ ተካፋይ እንደነበሩ ታውቋል። ጥር 26 ቀን 2005 ዓ. ም. አንድ መቶ የሚሆኑ የቅዱስ ማቃሪዮስ ገዳም መነኮሳት፣ አቡነ ኤፒፋኒዮስን በአብላጫ ድምጽ መርጠዋቸው የገዳማቸው አበምኔት አድርገዋቸው እንደ ነበር ታውቋል።

ብጹዕ ኤፒፋኒዮስ የማታ አል መስኪን ሐዋርያ፣ መንፈሳዊ አባት፣ የቅርብ ዓመታት የግብጽ ኮፕት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ታዋቂ ተንታኝ እንደነበሩ ሲነገር ከዚህም በተጨማሪ ከመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መነኮሳት ማህበራት ጋር የጠበቀ መንፈሳዊ ግንኙነትን እንደነበራቸው ታውቋል።

የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ፣ ብጹዕ ወቅዱስ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ታዋድሮስ ሁለተኛ የብጹዕ አቡነ አንባ ኤፒፋኒዮስን የአሟሟት ሁኔታ የሚከታተል እና መረጃን የሚያቀርብ የልዑካን ቡድን፣ ጳጳሱ ወደ ተገደሉበት ወደ ታላቁ ዳይር አቡ ማቃር የቅዱስ ማርቆስ ገዳም መላካቸው ታውቋል።                        

 

02 August 2018, 14:31