ፈልግ

Vatican News
ብጹዕ ካርዲናል ኦስቫልዶ ግራሲያስ - ሕንድ   ብጹዕ ካርዲናል ኦስቫልዶ ግራሲያስ - ሕንድ  

ካርዲናል ግራሲያስ፣ የሕንድ መንግሥት የምስጢር ንስሐን ስርዓት ለማስቀረት ያቀረበውን ሃሳብ አወገዙ።

የሕንድ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት፣ መንግሥታቸው የምስጢር ንስሐን ስርዓት ለማስቀረት ያቀረበውን ሃሳብ አውግዘው ተግባራዊ እንደማያደርገው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። በዚህ የቤተ ክርስቲያን ምስጢር አማካይነት ብዙዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያደጉበትና ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትን እና ሰላምን ያገኙበት ነው ብለዋል።

የዚህ ዜና አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሕንድ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤትን በመወከል ባቀረቡት አስተያየት፣ የሕንድ መንግሥት ብሔራዊ ምክር ቤት የምስጢር ንስሐን ስርዓት ለማስቀረት ያቀረበውን ሃሳብ አውግዘዋል። መንግሥትም ሃሳቡን ተግባራዊ እንደማያደርገው ያላቸውን እምነት ገልጸው በቀሳውስቱ የሚፈጸሙት ወሲባዊ ጥቃቶች ካሉ  ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በሃገሪቱ የሚፈጸሙትን ወሲባዊ ጥቃቶች ለመከላከል መንግስትም ሆነ ቤተ ክርስቲያን ጠንካራ እርምጃ መውሰድ አለበት። ጥቃቱን በሚፈጽሙት ላይ ከበድ ያለ ቅጣት ይጣልባቸው። ነገርግን መንግሥት የምስጢር ንስሐን ስርዓት ለማስቀረት ያቀረበው ሃሳብ ሊታመን የማይቻል ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ፣ የሕንድ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ናቸው። በሕንድ መንግሥት ብሔራዊ ምክር ቤት የሴቶች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት የምስጢር ንስሐን ስርዓት ለማስቀረት ያቀረበው ሃሳብ ጉዳዩን ወደ ከፋ አቅጣጫ ሊወስደው ይችላል ብለዋል።

በመንግስት ብሔራዊ ምክር ቤት የሴቶች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ሬካ ሻርማ እንደገለጹት ካህናት ራሳቸው ጥቃቱ የደረሰባቸውን ሴቶች በማስተባበር የተደበቁ ምስጢሮችን እንዲያወጡ ማድረግ ይችላሉ ብለዋል። ይሁንና የሕንድ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ እንደገለጹት በቅርቡ በፑንጃብ እና በከራላ ግዛቶች ተፈጽመዋል የተባሉ ወሲባዊ ጥቃቶችን በማስመልከት የተመሠረቱ ክሶች፣ በፑንጃብ የጃላንዳር ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ፍራንኮ ሙላካል፣ በ2006 ዓ. ም. እና በ2008 ዓ. ም. መካከል ባሉት ጊዜያት ውስጥ በአንዲት መነኩሴ የተመሠረተባቸውን የሐሰት ክስ በድጋሚ ለመቀስቀስ የተደረገ ደባ ነው ብለዋል። እንደዚሁም በከራላ ሃገረ ስብከት ውስጥ ሓዋርያዊ አገልግሎት ሲያበረክቱ የቆዩ አራት ካህናት በሚያገለግሉበት ቁምስና ተመሳሳይ ወንጀል ሳይፈጽሙ አልቀረም የሚለውን ጥርጣሬ ለማጉላት የተደረገ ነው ብለዋል። ይህም ቢሆን እውነት እንደሆነ ለማረጋገጥ ጉዳዩ ወደ ሕግ ዘንድ ቀርቦ የማጣራት ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ ገልጸዋል።

የሕንድ መንግሥት ብሔራዊ ምክር ቤት፣ የምስጢር ንስሐን ስርዓት ለማስቀረት ያቀረበውን ሃሳብ፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ምስጢራት ትርጉም ካለማወቅ የተነሳ ብቻ ሳይሆን፣ የሕንድ መንግሥት ብሔራዊ ምክር ባለስጣናትም ስለማይቀበሉት ድጋፍ አያገኝም ብለዋል። ለማንኛውም ጉዳዩ እንዲጣራ የተደረገ በመሆኑ እውነት ሊሰወር አይችልም ብለዋል። የሕንድ መንግሥት ብሔራዊ ምክር ቤት ያቀረበውን አስተያየት ያወገዙት የሕንድ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ምክር ቤት ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ፣ በቤተ ክርስቲያናቸው የተቃጣው ተግባር በሕንድ ሕገ መንግሥት ውስጥ የተቀመጠውን የሐይማኖትን ነጻነት ይጋፋል ብለዋል። ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ በማከልም መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ፣ በሕንድ የሴቶችን ጉዳይ አስመልክቶ የሚነሱትን በርካታ ጥያቄዎችን ለመመለስና ችግሮችን ለማስወገድ፣ በተለይም የሴቶችን ኑሮ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ፣ የትምህርትና የስልጠና ዕድሎችን በማመቻቸት፣ ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመከላከል ጥረት ቢያደርግ ይሻል ነበር ብለዋል።

የምስጢር ንስሐን ስርዓት ለማስቀረት መንግሥት ያቀረበው ሃሳብ ስለ ቤተ ክርስቲያን ምስጢራት ትርጉም አስፈላጊነት ካለማወቅ የተነሳ ነው ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ግራሲያስ፣ በዚህ የቤተ ክርስቲያን ምስጢር አማካይነት ብዙዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያደጉበትና ከእግዚአብሔር ዘንድ ምሕረትንና ሰላምን ያገኙበት ነው ብለው የሕንድ መንግሥት ያቀረበው ሃሳብ ተገቢ እና ትክክለኛ አለመሆኑን በሂደት ይረዳዋል ብለዋል።    

04 August 2018, 15:40