ፈልግ

2018.08.17 Linda Ghisoni 2018.08.17 Linda Ghisoni 

በአይርላንድ የሚካሄደውን የቤተሰብ ጉባኤ በማስመልከት ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጡ።

የቤተሰብ ቀንን ለማክበር ወደ አይርላንድ ከሚጓዙ የቤተሰብ አባላት ጋር የቫቲካን ዜና አገልግሎት ተወካይ ጋዜጠኛ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ቃለ ምልልስ አድርጓል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን ከነሐሴ 15 እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ. ም. የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤን አስመልክቶ የቫቲካን ዜና አገልግሎት፣ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ከወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ ጋር ቃለ ምልልስ ማደረጉ ታውቋል።

ዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን ከዛሬ ነሐሴ 15 እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ. ም. ድረስ ይካሄዳል። ወደ ጉባኤው የሚመጡትን እንግዶች አቀባበልንና የጉባኤዉን ይዘት በተመለከተ የቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ የሆነው አሌሳንድሮ ጂሶቲ ጉባኤውን ለሚካፈሉ አባላት አንዳንድ ጥያቄዎችን አቅርቦላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከነሐሴ 15 እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ. ም. ድረስ፣ ለዘጠነኛ ጊዜ በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ለሚካፈሉ ወላጆች፣ ልጆችና የዕድሜ ባለ ጸጋዎች፣ “ቤተሰብ ለዛሬው ዓለማችንም መልካም ዜና ሆኖ ይቀጥላል ወይ?” በማለት ጥያቄን አቅርበው፣ የበኩላቸውን መልስ ሲሰጡ፣ አዎ! ቤተሰብ ለዛሬው ዓለማችንም መልካም ዜና ሆኖ ይቆያል በማለት በመጋቢት ወር በላኩት መልዕክታቸው ላይ ገልጸዋል። ቅዱስነታችን በማከልም ይህ አዎንታዊ መልስ፣ በእግዚአብሔር እቅድ ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ለሆኑት ለብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ፋረል በላኩት በዚህ መልዕክታቸው እንደገለጹት በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊል የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ከፍቅር የሚገኝ ደስታ በተሰኘው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ውስጥ የቀረቡትን የአስተምህሮ ሃሳቦችን በጋራ በመመልከት ለማሳደግ ጥሩ አጋጣሚን እንደሚያመቻች ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ከጳጳሳት ሲኖዶስ ማግሥት የወጣው እና “የቤተሰብ መልካም ዜና ለዓለም ሁሉ ደስታ ነው” በማለት የሚታወቀው ሰነድም በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ላይ ዋና መንደርደሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ታውቋል። አንባቢዎች በቤተሰብ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያሉ መንፈሳዊ ትምህርቶችን እንዲያገኙ ለማድረግ ተብሎ የተዘጋጀ “www.worldmeeting2018” የተሰኘ የማህበራዊ ድረ ገጽ አድራሻ ይፋ ሆኗል። በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን በሚካሄደው ዘጠነኛው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ከ500 ሺህ አባላት እንደሚገኙ ይጠበቃል።

የዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤን ሲካፈሉ በአይርላንድ ዋና ከተማ በዳብሊን የሚካሄደው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁለተኛ ሲሆን ከዚህ በፊት በሰሜን አሜርካ፣ በፊላደልፊያ ከተማ የመጀመሪያቸውን ተካፍለው እንደነበር ይታወሳል። ከ116 አገሮች የመጡት የጉባኤው ተካፋዮች የሚገኙበትና ዛሬ ነሐሴ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስዋዕተ ቅዳሴ የሚከፈተውን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ የመላው አይርላንድ ሀገረ ስብከቶች ምእመናንም በያሉበት ሆነው በጸሎት እንደሚተባበሩ ታውቋል። ከነሐሴ 16 ቀን እስከ ነሐሴ 18 ቀን ድረስ በሚቆየው ሐዋርያዊ ጉባኤ ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች፣ ውይይቶች እና ምስክርነቶች የሚቀርቡ ሲሆን ከወላጆቻቸው ጋር ለመጡት ሕጻናት የመዝናኛ ጊዜም እንደተያዘላቸው ከመርሃ ግብሩ ለማወቅ ተችሏል። ከጉባኤው አዘጋጆች ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው፣ በአይርላንድ ቤተ ሰብ መካከል ትልቅ ስፍራ የሚሰጣት እና “ኤሪን” በመባል የምትታወቅ በግ በአሻንጉሊት መልክ ተሰርታ በመቅረብ ሕጻናትን እንደምታዝናና  ገልጸው ዋና ዓላማውም እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ የተከበርንና ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠን ለማስገንዘብ ነው ተብሏል። ቅዳሜ ነሐሴ 19 ቀን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስና መላው የጉባኤው ተካፋዮች የሚሳተፉበት የቤተሰብ ፌስቲባል በዳብሊን ከተማ ውስጥ በሚገኘው በኮርክ መናፈሻ ላይ እንደሚከበር እና በነጋታው፣ እሁድ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ. ም. ከ500 ሺህ ሰው በላይ እንደሚገኝ በሚጠበቀው በፎኒክስ መናፈሻ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚያሳርጉት መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚጠናቀቅ ከመርሃ ግብሩ ለማወቅ ተችሏል።

ጉባኤው ለአይርላንድ ቤተክርስትያን ታላቅ የሥራ ድርሻን ያስረክባል፣

ከአርባ አመታት ወዲህ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አይር ላንዲን ሲጎበኙ ለአገሩ ሕዝብ ታልቅ ደስታን የሚያጎናጽፍ ነው። ከአርባ ዓመታት በፊት በ1971 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በአይርላንድ ማድረጋቸው ይታወሳል። በውቅቱ የተደረገውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ሁለተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያስተባብሩ 10 ሺህ ሰዎች በአገልግሎት ላይ መሰማራታቸው ይታወሳል። የዳብሊን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ዲያርሙድ ማርቲን እንደገለጹት፣ የአይርላንድ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተሰጣት አደራ፣ በተለይም ይህን የመሰለ ታላቅ ዓለም አቀፍ ጉባኤን ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን በአዲሱ ዘመን በአይርላንድ ሕብረተ ሰብ ውስጥ የቤተሰብ አስፈላጊነትን እንድታውቅ አግዟታል ብለዋል።

በርካታ የውይይት ርዕሶች፥ ከእምነት እስከ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣

የዘንድሮን ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ሐዋርያዊ ጉባኤን ለመካፈል ከ37 ሽህ በላይ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል፣ ዕድሜአቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑት 6 ሺህ ወጣቶች፣ በዚህ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤ ላይ በቀረበው “የፍቅር ሐሴት” በተሰኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕድንን በሚገባ እንዲረዱት የሚያስችሉ መልዕክቶችን ተቀብለዋል። ከእነዚህም መካከል እምነትን ለሌሎች መመስከርና ማስተላለፍ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም በቤተሰብ ዘንድ እና በወላጆች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች በልጆች ስነ ልቦና ውስጥ የሚፈጥረው ተጽዕኖ የሚሉ ይገኙባቸዋል። ከእነዚህ ርዕሶች በተጨማሪ የሴቶች ሚና በብሔራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ቁምስናዎች ለግብረ ሰዶማዊያን የሚያደርጉት አቀባበል፣ ዘላቂ እድገትን ለማምጣት የቤተሰብ አስተዋጽዖ፣ ከድህነት ለመውጣት የትምህርት ቤቶችና የማሰልጠኛ ተቋማት ሚና የሚሉ ርዕሶችም ተካተዋል። በርካታ ወስባዊ ጥቃቶች እንደሚፈጸምባት የምትታወቅ አይርላንድ፣ በነሐሴ 18 ቀን በሚደረገው የውይይት መድረክ ላይ ሕጻናትን ከዚህ ድርጊት ለመታደግ የሚወሰድ እርማጃ፣ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ሰዎችን ሁኔታ የሚመለከቱ ውይይቶች በስፋት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

ክርስቲያናዊ ቤተሰቦች የወንጌል ሕያው ምስክሮች ናቸው፣

የቫቲካን ዜና አገልግሎት፣ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ከሆኑት ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ ወይዘሮዋ ሊንዳ እንደገለጹት፣ ክርስቲያናዊ ቤተሰቦች የወንጌል ሕያው ምስክሮች መሆናቸውን አስረድተው “ከፍቅር የሚገኝ ሐሴት” የተሰኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ዘንድሮ በሚደረገው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ቤተሰብን አስመልክቶ ሰፋ ያሉ ጠቃሚ ሃሳቦችን እንደሚያስጨብጥ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። የቫቲካን ዜና አገልግሎት ተወካይ የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ለወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ ባቀረቡት ቃለ መጠይቅ፣ ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ጉባኤን የሚካፈሉት እንደ ቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ እና እንደ ባለትዳር በመሆን እንደሆነ ገልጸው፣ የጉባኤውን ዝግጅት በመምራትና በማስተባበር ሰፊ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል። ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ በምክትል ዋና ጸሐፊነት የሚመሩት፣ በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጽሕፈት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ካቋቋሟቸው አዳዲስ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች መካከል አንዱ እንደሆነ ታውቋል። የቫቲካን ዜና አገልግሎት ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ክርስቲያናዊ ቤተሰብን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በፍቅር የሚገኝ ሐሴት በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን እይታ በማለት የጀመሩት ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ፣ እንደ ልጆች እናትና እንደ ቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሰራተኛ በመሆን፣ በአይርላንድ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ የቤተ ሰብ ጉባኤን በመካፈሌ ሁለት ትርጉም ይሰጠኛል ብለዋል። እንደ ቤተሰብ አባልነቴ፣ እንደማንኛውም የጉባኤው ተካፋይ ሆኜ ስለምገኝ በጉባኤው የሚቀርቡ ሃሳቦችን ለማዳመጥ፣ ሃሳቤን ከሌሎች የቤተሰብ ክፍሎች ጋር ለመጋራት እና ከዚህ በፊት የነበረኝን እውቀት ለማሳደግ ይረዳኛል ብለዋል። በማከልም በጉባኤው በሚቀርቡ የመወያያ ርዕሶች አማካይነት ቤተሰብ ለእያንዳንዳችን የተሰጠ የእግዚአብሔር ስጦታ መሆኑን እንድናውቅ ስለሚያደርጉን ይህን ስጦታ የበለጠ አውቀን፣ ይህን ስጦታ በእንክብካቤ ጠብቀን እንድንይዝ የሚያግዘንን ሃይል እንደምንቀበል ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል። ይህ በመሆኑ ወይዘሮ ሊንዳ ጊሾኒ በማከልም የቤተሰብ ሕይወት፣ ሕይወቱን ለሚካፈሉት በቤተክርስቲያንም ሆነ በዓለም ሁሉ የውበትና የደስታ ምንጭ እንዲሆን በእግዚአብሔር የተባረከ ስፍራ እንደሆነ እገነዘባለሁ ብለዋል። በማከልም የቤተሰብ ሕይወት በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረግ ውሕደት እና በእግዚአብሔር የተባረከ ስጦታ መሆኑን አውቀን የምንኖር ከሆነ፣ መልካም ፍሬን የምናይበት፣ በልጆቻችንም የምንባረክበት መሆኑን ተገንዝበን በእውነት ከኖርንበት፣ የጋብቻ ጥሪ በፍቅር የተመሠረተ በመሆኑ ይህን የፍቅር ጥሪን በዕለታዊ ኑሮአችን አማካይነት ለሌሎችም መመስከር እንችላለን ብለዋል።  

21 August 2018, 09:30