ፈልግ

2018.08.25-26 Viaggio apostolico in Irlanda, incontro mondiale con le famiglie a Dublino 2018.08.25-26 Viaggio apostolico in Irlanda, incontro mondiale con le famiglie a Dublino 

የአይርላንድ ምእመናን የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን መምጣት በናፍቆት ይጠባበቃሉ።

ከ116 አገሮች የመጡ የስብሰባ ተካፋዮችም ከአይርላንድ ምዕመናን ጋር በመሆን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መምጣት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባን በማስተናገድ ላይ ያለች አይርላንድ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መምጣት በመጠባበቅ ላይ መሆኗ ታውቋል።

በአይርላናንድ ዋና ከተማ በሆነችው በዳብሊን ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል። ከ116 አገሮች የመጡ የስብሰባ ተካፋዮችም ከአይርላንድ ምዕመናን ጋር በመሆን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መምጣት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ አይርላንድ የሚያደርጉት ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት 23ኛቸው እንደሆነ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤተሰብን በማስመልከት በቲዊተር የግል የማሕበራዊ መገናኛ በኩል በላኩል መልዕክት እንደገለጹት፣ ቤተሰብ የሕይወት መስረት፣ ፍቅርን የምንማርበትና የምንቀበልበት፣ የእግዚአብሔርም ምስጢር እንዲገለጽ ዕድል የተሰጠበት ቦታ ነው ማለታቸው ታውቋል።

ከ116 አግሮች የመጡ ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ ተካፋዮችን በማስተናገድ ላይ ያለች የዳብሊን ከተማ ባሁኑ ወቅት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መምጣት በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች። የስብሰባው ተካፋዮች በእነዚህ ቀናት ውስጥ በሚያካሂዷችው ውይይቶች፣ አውደ ጣናቶችና የእምነት ምስክርነት በኩል በቤተሰብ ዙሪያ የሚነሱ ርዕሠ ጉዳዮችን በጥልቀት በመመልከት ላይ መሆናቸው ታውቋል።

ቤተሰብ የአዲስ ሕይወት ስጦታ ነው፣

በአይርላንድ፣ የአርማግ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ አቡነ ማርቲን፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመጥቀስ ባሰሙት ንግግራቸው፣ ቤተሰብ የአዲስ ሕይወት ስጦታ እንደሆነ ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳሳ ማርቲን በማከልም ምዕመናን ገና በጽንጽ ደረጃ ያላሉትን ሕጻናት ነፍስ ለማዳን የሚያደርጉት ጥረትና የሚያሰሙት ድምጽ እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መልዕክት ያስታወሱት ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ አቡነ ማርቲን በንግግራቸው ወጣቶች በማይጠቅም ጎጂ ባሕል ባህል ውስጥ ገብተው   እንደሚገኙ አስረድተዋል።

የሕይወት አድን ልኡክነት፣

ወጣቶች ስለ ሰው ልጅ አፈጣጠር ባጠቃላይ ስለ ሰው ነፍስ ሊኖራቸው የሚገባውን ግንዛቤ በሚያሳንሱ ዓለማዊ አስተሳሰቦች ተውጠው መገኘታቸውን አስታውሰው የመላው አይርላንድ ምዕመናን፣ ስለ ሰው ልጅ ሕይወትና ስለ ቤተሰብ መልካም ዜና አብሳሪነት በተሰማራንበት የሥራ ዘርፍና የሕይወት አቅጣጫ ምስክርነትን ለመስጠት ተጠርተናል ብለዋል።

ቤተሰብ የሚገኝበትን ሁኔታ በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል፣

በሰሜን አሜርካ የኒውዮርክ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ዮሴፍ ቶቢን እንዳሉት፣ የጋብቻ ሕይወት ትርጉም የጊዜውን ተጨባጭ ሁኔታን ባላገናዘቡ የስነ መልኮት አስተሳሰብ መለወጥ ሳይሆን ቤተሰብ በተግባር እየኖረበት ያለውን የጊዜውን ሁኔታ ያገናዘበ መሆን አለበት ብለው ይህ ካልሆነ የዛሬው ቤተሰብ የኑሮ ሁኔታና ፍላጎታቸውን ማወቅ አንችልም ብለዋል።

የተቃራኒ ጾታዎች ግንኙነት የሚገኝ ደስታ፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን፣ ከፍቅር የሚገኝ ደስታ የተሰኘውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን የጠቀሱት፣ በሰሜን አሜርካ የቺካጎ ሊቀ ጳጳሳ ብጹዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች፣ ወሲባዊ ግንኙነት የስጋን ምኞትና ደስታ ለማርካት ብቻ የሚፈጸም ሳይሆን ሁለቱ ተቃራኒ ጾታዎች አንዱ የሌላውን የማይገረሰስ መንፈሳዊ ክብርን የጠበቀ መሆን ያስፈልጋል ብለዋል። የሁለት ተቃራኒ ጾታዎች የፍቅር ግንኙነት ከግል ፍላጎት እርካታ የወጣ መሆን አለበት ያሉት የቺካጎ ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ብሌዝ፣ ይህ ግንኙነትም ወደር የማይገኝለት ውብ የሆነ ክብር እና ውበት ነው ብለዋል። በሁለቱ ተቃራኒ ጾታዎች መካከል የሚደረግ ግንኙነት ለጋብቻ ሕይወት አጅግ አስፋአላጊ ከመሆኑ በላይ በመካከላቸው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመጠገን ወደ ስምምነት ለመድረስ ያግዛል ብለዋል። የሁለት ተቃራኒ ጾታዎች ግንኙነት በምንልበት ጊዜ፣ በወሲባዊ ምስሎች የሚታይ ጾታዊ ግንኙነት ከሁለቱ ተቃራኒ ጾታዎች በኩል በሚመነጭ ፍላጎት የሚደረግ ባለመሆኑ አንዱ ለሌላው የሚያሳየው የፍቅር ዝንባሌ የለበትም ብለዋል።

በችግር ውስጥ ያሉትን ባለትዳሮች መርዳት ያስፈልጋል፣

ለጋብቻ ሕይወት ጠንቅ በሆኑ ችግሮች ውስጥ የሚገኙትን የቤተሰብ ክፍሎችን ወደ ስምምነትና ወደ ፍቅር ሕይወት ለመመለስ የሚያግዙ የተለያዩ ዘዴዎችን የጠቆሙት የሰሜን አሜርካ እና የካናዳ የቤተሰብ ተወካዮች እንደገለጹት የጋብቻ ሕይወት አንድ ሂደት እንደመሆኑ ዘላቂነት እንዲኖረው አስፈላጊው እንክብካቤ እየተሰጠው ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደግ ይገባል ብለዋል። በመሆኑም ባልና ሚስት ለጋብቻ ሕይወት ማደግ በጋራ በመጣር እያንዳንዱ የበኩሉን አስተዋጽዖን ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በባልና በሚስት መካከል የሚታይ ፍቅር፣

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ጳጳሳዊ ተቋም ምክትል ዋና ጸሀፊ የሆኑት ክቡር አባ ሆሴ ግራናዶስ በባልና በሚስት መካከል ሊኖር ስለሚገባው ፍቅር ሲያስረዱ፣ በባልና በሚስት መካከል ያለውን ፍቅር ቋም፣ ጥልቅና ፍሬያማ ለማድረግ ከተፈለገ የሚሰጠው ቦታና አክብሮት ሰፊ መሆን አለበት ብለዋል። ባለትዳሮች ከእግዚ አብሔር ዘንድ ለሚያገኙት እርዳታ እርግጠኞች እንዲሆኑ ቤተክርስቲያን የምትሰጠውን ዕለታዊ ሐዋርያዊ አገልግሎት ማቁረጥ የለባትም ብለዋል። በቤተክርስቲያን ምስጢራት አማካይነት ጋብቻን መመሥረት ማለት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሠረታት ቤተክርስቲያን የማያቋርጥ ፍቅር እንዳሳያት፣ በጋብቻም ውስጥ የማያቁርጥ ፍቅር ሊኖር ይገባል ብለዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ባሳያት የምህረት መንገድ፣ ቤተክርስቲያንም ለተጎዳው ወይም ለቆሰለው ፍቅር ምሕረትን በመስጠት እንዲፈወስ ታደርጋለች ብለዋል።

ቤተሰብ እና ሥራ፣

በአይርላንድ በመካሄድ ላይ ላለው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ስብሰባ መልዕክታቸውን ካቀረቡት መካከል፣ ብጹዕ ካርዲናል ፒተር ኮዱዎ ታርክሰን፣ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ እድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ መሆናቸውን የገለጸው ሲር የዜና አገልግሎት እንደገለጸው፣ የማምረቻ ተቋማትን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ታርክሰን የማምረቻ ተቋማት ቀዳሚ ተልዕኮ ለቤተሰብ አባላት የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ ለቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ሕብረተሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት ትልቅ እገዛን እንደሚያደር አስረድተዋል። ቤተሰብም ይህን ዕድል በመጠቀም ለተወለዱት ልጆችና ወደፊትም ለሚመጣው ትውልድ አገልግሎት እንዲሆን በማለት በተጨማሪም በቤተሰብ መካከል ያለው ፍቅርና ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ ትልቅ ሃላፊነት አለበት ብለዋል።

ቤተሰባዊ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ሚና፣

በቬና የጉትማን ባንክ ዋና ዳይረክተር የሆኑት አቶ ጎርዲያን ጉደኑስ በቤተሰብ የሚተዳደሩ ሕዝባዊ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን በማስታወስ ባቀረቡት ገለጻቸው እንዳስረዱት ቤተሰባዊ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ማሕበራዊ እድገትን በማምጣት የሚጫወቱት ሚና ሰፊ እንደሆነ ገልጸው ባሁኑ ጊዜ በቤተሰብ የሚተዳደሩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት 60 ከመቶ የሚሆነውን የዓለም የሰራተኛ ሃይል እንደሚያስተዳድ ጠቁመው ይህም ከጠቅላላው የዓለም ምርት መጠን 70 ከመቶ እንደሚሸፍን ገልጸዋል።  በቬና የጉትማን ባንክ ዋና ዳይረክተር የሆኑት አቶ ጎርዲያን ጉደኑስ በማከልም የሥራ ዕድልን በማመቻቸት ላይ የሚገኙ ቤተሰቦችን የተጠሩበትን ዓላማ ክብር በሚገባ እንዲያውቁ ቤተክርስቲያን እንድትረዳቸው ያስፈልጋል ብለዋል።        

24 August 2018, 16:10