ፈልግ

የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አራት አዳዲስ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አራት አዳዲስ የእግዚአብሔር አገልጋዮች  

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ለአራት የእግዚአብሔር አገልጋዮች የክብር ማዕረግን አጎናጸፈች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የስመተ ቅድስና ጉዳይ የሚከታተል ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑትን ካርዲናል አንጀሎ አማቶን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት፣ ከምዕመናን ወገን የሆኑ አራቱ ልጆች፣ የቤተ ክርስቲያን የክብር ማዕረግ ስም እንደጸደቀላቸው አረጋግጠውላቸዋል።

ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ለአራት የእግዚአብሔር አገልጋዮች የክብር ማዕረግን አጎናጸፈች

የቤተ ክርስቲያን የክብር ማዕረግ የተሰጣቸው አራቱ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ ጆርጆ ላ ፒራ፣ ፔትሮ ዲ ቪታለ፣ ኣለሲያ ጎንዛሌስ ባሮስ እና ካርሎ አኩቲስ ናቸው። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር የስመተ ቅድስና ጉዳይ የሚከታተል ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የሆኑትን ካርዲናል አንጀሎ አማቶን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት፣ ከምዕመናን ወገን የሆኑ አራቱ ልጆች፣ የቤተ ክርስቲያን የክብር ማዕረግ ስም እንደጸደቀላቸው አረጋግጠውላቸዋል።

የዚህ ዜና አዘጋጅ ዮሐንስ መኰንን

በታሕሳስ ወር 1896 ዓ. ም. የደቡብ ኢጣሊያ ግዛት በሆነችዉ በሲሲሊያ ደሴት የተወለደው ጆርጆ ላ ፒራ፣ ከትውልድ አካባቢው ርቆ ወደ መካከለኛው ሰሜን ኢጣሊያ ክፍለ ሀገር ከተማ ወደ ሆነው ወደ ፍሎረንስ በመሄድ፣ ከ1943 እስከ 1949 ዓ. ም. እና ከ1953 እስከ 1957 ዓ. ም. ድረስ የከተማው ከንቲቫ በመሆን፣ ሁለት ጊዜ እንዳገለገለ ከሕይወት ታሪኩ ለማወቅ ተችሏል። በወቅቱ የዚህ ወጣት ቀዳሚ ተልዕኮ የነበረውም ለአካባቢው ነዋሪዎች የክርስትና እምነት መንፈሳዊ ጸጋዎችን ማካፈል፣ ዕለታዊ ቁሳቁሶችን ማቅረብ፣ መጠለያን እና የሥራ ዕድሎችን ማዘጋጀት እንደነበር ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ ጆርጆ ላ ፒራ የዩኒቨርሲቲ መምህር እና የክርስቲያን ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር አባል እንደነበር ታውቋል። ወጣቱ በእነዚህ የሥራ አመታት ባሳየው የሕይወት ምስክርነት፣ የእምነት ጽናት ያለው የጸሎት እና የሰላም ሰው እንደነበር ታውቋል። ወጣት ጆርጆ ላ ፒራ በ1943 ዓ. ም. ወደ ሩሲያ በመሄድ፣ ከስታሊን ጋር ስለ ኮሪያ ሰላም የተወያየ፣ በ1956 ዓ. ም. ወደ ሰሜን አሜሪካ በመሄድ፣ የሕጻናት መብት ሲረቀቅ፣ በሕግ አውጪዎች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ መገኘቱ እና በ1957 ዓ. ም. በወቅቱ የቻይና ኮሚኒስት መሪ ከነበሩት ከሆ ቺ ሚን ጋር ስለ ቬትናም ሰላም መነጋገሩ ታውቋል። ወጣት ጆርጆ ላ ፒራ በሥራ ዘመኑ በዶሜኒካን መነኩሴዎች ገዳም ውስጥ የድህነት ሕይወት የኖረ፣ ከሃያላን መሪዎች ጋር ስለ ደሆች እድገት አጥብቆ የተከራከረ እንደነበር ከሕይወት ታሪኩ ለማወቅ ተችሏል። ወጣቱ ሕዝባዊ አገልግሎቱን ሲያበረክት በኖረባት የኢጣሊያ ከተማ በሆነችው በፍሎረስ፣ በጥቅምት ወር 1970 ዓ. ም. ማረፉ ታውቋል።

ሌላው የእግዚአብሔር አገልጋይ እና በ15 ዓመት ዕድሜ ያረፈው ካርሎ አኩቲስ፣ ወላጆቹ ለሥራ ፍለጋ በሄዱበት በሎንደን፣ ሚያዝያ 25 ቀን 1983 ዓ. ም. የተወለደ ሲሆን ቀጥሎም ወደ ሰሜን ኢጣሊያ ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ሚላን በመምጣት የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ሲከታተል ሳለ፣ ለክርስትና እምነቱ ባሳየዉ ጥልቅ ፍቅር ይታወቃል። ይህ ሕጻን በዚህ ዕድሜው በኢንተር ኔት ድረ ገጽ አማካይነት ለምዕመናን የወንጌል አገልግሎት ያዳርስ እንደነበር እና የቅዱስ ቁርባንን ተዓምራት ይመሰክር እንደነበር ታውቋል። በሕይወት በኖረባቸው ዓመታት ወደ ሰማያዊው ክብር የሚያደርሰው ብቸኛው መንገድ ቅዱስ ቁርባን እንደሆነ የገለጸ፣ እንዲሁም በሰዎች ስም የሚቀርብ የመቁጠሪያ ጸሎትን ያዘወትር እንደነበር ታውቋል። ሕጻኑ በአጥንቶቹ መቅኔ ውስጥ ባልተስተካከለ መልኩ በብዛት በመራባት በሚፈጠረው ካንሰር ምክንያት፣ ጥቅምት 2 ቀን 1999 ዓ. ም. ማረፉ ታውቋል።

በሚያዝያ 23 ቀን 1963 ዓ. ም. በስፔን ዋና ከተማ በማድሪድ የተወለደችው ሕጻን ኣለሲያ ጎንዛሌስ ባሮስ፣ ባደረባት የካንሰር ሕመም ስትሰቃይ ቆይታ፣ ህዳር 26 ቀን 1978 ዓ. ም. ማረፏ ታውቋል። ሕጻኗ በሕመም ወቅት የሚሰማትን ጥልቅ ስቃይ ለማስታገስ በጸሎት እንዲያግዟት ለቤተ ክርስቲያን፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና ለሌሎች ሰዎች አደራ ትላቸው እንደነበር ታውቋል።

በከባድ የሆድ ሕመም ይሰቃይ የነበረ ወጣት ፔትሮ ዲ ቪታለ፣ በደቡብ ኢጣሊያ ክፍለ ሀገር በሆነችው በሲሲሊያ ደሴት፣ በታሕሳስ 5 ቀን 1909 ዓ. ም. የተወለደ ሲሆን፣ በፓለርሞ ከተማ በሚገኘው የሊቀ ጳጳሳት ዘርዓ ክህነት በመግባት መንፈሳዊ ትምህርቱን ተከታትሎ እንደነበር ከሕይወት ታሪኩ ለመረዳት ተችሏል። ወጣቱ በወቅቱ በአገሩ በስፋት በሚታወቀው የካቶሊክ ተግባር በተሰኘው እንቅስቃሴ ውስጥ የታቀፈ እንደነበር የሚነገርለት ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በሦስተኛው የምዕመናን ፍራንችስካዊ ማሕበር አባል እንደነበር ታውቋል። ወጣቱ በሕይወት ዕድሜው ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ለቅዱሳት የቤተ ክርስቲያን ምስጢራት ልዩ አክብሮት እና ፍቅር እንዳደረበት በተግባር ያሳይ እንደነበር ተመስክሮለታል። በትምህርቱ ጎበዝ እና ለሰዎች በሚያሳየው የደግነት ተግባር በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ እንደነበር ታውቋል።  

09 July 2018, 13:02